ቁጭት የተቋጨበት የዓባይ ግድብ

ዜና ሐተታ

‹‹ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፤ የዓባይን ልጅ ውሃ ጠማው›› የሚሉትና ሌሎችም በዓባይ ወንዝ ላይ የተነገሩ አባባሎች ወንዙ ለሀገሬው ሰው ጥቅም እየሰጠ አለመሆኑን የሚያሳዩ የቁጭት አገላለጾች ናቸው። ዓባይ ዛሬ ኢትዮጵያውያን ተባብረን በገነባነው የዓባይ ግድብ አማካኝነት ከቤቱ አድሯል፤ አፈራችንን እያጋዘ ላይጨርስ፤ ጉሮሮአችንን እና መሬታችንን ሊያረሰርስ፤ ለማገዶ ሲጨፈጨፍ የኖረውን ደን ሊታደግ፤ ኢንዱስትሪዎቻችንን ሊያነቃቃ፣ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ እና ለሌሎች ተግባራት ዝግጁ ሆኗል።

የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ከሚወስኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች አንዱ ነው። ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር እያደረገች ባለችው ጉዞ ውስጥ እስከ አሁን የድህነትን አከርካሪ ለመምታት ያስችላሉ ብላ ከታጠቀቻቸው ታላላቅ መሣሪያዎቿ ግንባር ቀደሙ ነው። የዓባይ ግድብ ለፍጻሜ መብቃት የመብራት ኃይልን ከማመንጨትም በላይ ለሀገራችን ፈርጀ ብዙ ትርጉም ያለው ነው።

የዓባይ ግድብ ያለምንም የውጭ ርዳታም ሆነ ብድር፤ አካባቢያዊና ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎችን ተቋቁሞ በራስ አቅም ለዚህ መብቃቱ የዚህ ትውልድ ሌላኛው የዓድዋ ድል ተደርጎ የሚታይ ነው። ከሊቅ እስከ ደቂቅ በእኔነት እና በመተባበር መንፈስ ሁሉም የድርሻውን ጠጠር ወርውሮ ለፍጻሜ ያበቃው መሆኑም ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ታላቅ ገድል ነው።

ይህን ሃሳብ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ የሸዋጌጥ አበራ ያጠናክሩልናል። ወይዘሮ የሸዋጌጥ ላለፉት 14 ዓመታት ለህዳሴው ግድብ ቦንድ በመግዛት እና በየትምህርት ቤቱ በተማሪ ልጆቻቸው በኩል በሚሰበሰበው መዋጮ ላይ ሲሳተፉ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

የዓባይ ወንዝ መነሻው ለሆነችው ኢትዮጵያ ምንም ጥቅም ሳይሰጥ መኖሩ ይቆጫቸው እንደነበር ይገልጻሉ፤ ኢትዮጵያውያን ለሕይወት ሁሉ ምንጭ የሆነውን የውሃ ሀብት ይዘው ማልማት ባለመቻላቸው ብቻ ወደ ሰው ሀገር ሲሰደዱ መኖራቸውንም እንዲሁ ያስረዳሉ።

ግብፅ ከእኛ ሀገር ባገኘችው ውሃ በእርሻ፣ በኤሌክትሪክ አቅርቦት እና በቱሪዝም ላይ በመሥራቷ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ለመኖር ወደእዛች ሀገር ይሰደዳሉ ያሉት ወይዘሮዋ፤ ነገር ግን ይህንን ታሪክ ሊያስቀር የሚችለው የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ መቃረቡ ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ። ግድቡ ለኢትዮጵያ አዲስ የብልፅግና ጉዞ መደላድል የሚፈጥር እንደሚሆንም ተስፋ ማድረጋቸውን ያስረዳሉ።

ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታምራት በቀለ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጀመር የነበረውን የሕዝቡን ደስታ እንደዚህ ያስታውሱታል ‹‹ያኔ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ነበርኩ። በየትምህርት ቤቱ፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን እና በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሳይቀር የሕዝቡ ደስታ እና ተስፋ ይታይ ነበር። አሁን ተስፋው እውን ሆኖ በአካል የሚጨበጥበት ጊዜ ላይ መድረሱ ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮብኛል›› ይላሉ።

የሰላም ዋንጫ በመባል የሚታወቀው የህዳሴው ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫ በተለያዩ ክልሎች እና ተቋማት እየተዘዋወረ ኢትዮጵያውያንን ለአንድ ግብ ሲያሰባሰብ ቆይቷል። በቅርቡም በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የአንድ ዓመት ቆይታውን ጨርሶ ወደ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ተላልፏል።

በዕለቱ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊና የአዲስ አበባ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ህዳሴ ግድብ ቅድመ አያቶቻችን ኢትዮጵያን በደማቸው እንዳጸኗት ሁሉ የአሁኑ ትውልድ ሀገሩን በላቡ የሚያለማበት የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የተናገሩት።

በ2010ዓ.ም መጀመሪያ ሰሞን ወላጅ አባታቸውን ግድቡን ለማስጎብኘት ሲወስዷቸው አባታቸው የተናገሩትን አቶ ጃንጥራር እንዲህ ያስታውሳሉ። ‹‹የእድሜ ባለፀጋ የሆነውን ወላጅ አባቴን ቦታው ድረስ ይዤው ስሄድ ይሄንን ግድብ እንደታሰበው የምትጨርሱት ከሆነ ዕድለኛ ትውልድ ናችሁ፤ ዳግማዊ ላሊበላን አቁማችኋል ማለት ነው አለኝ››። የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም በሁሉም ዜጎች የፋይናንስ ምንጭ ድጋፍና ትብብር የተገነባ የኢትዮጵያ የማንሰራራት መገለጫና የይቻላል ማሳያ ሆኗል ነው ያሉት።

ከተማ አስተዳደሩም ለፕሮጀክቱ ግንባታ እስከ አሁን  ከ6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የሚያስታውሱት ምክትል ከንቲባው፤ የኢትዮጵያ የፀጥታ መዋቅር የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በሚገነባበት ስፍራ የአካባቢውን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ታሪክ የማይዘነጋው ዐሻራ እያሳረፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርኸ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ህዳሴ ግድብን በሀገራችን ወግና ባህል እንደ ሀገር ልንሞሽረው ወራት ቀርተውታል። ለግድቡ እዚህ ደረጃ መድረስ መላው ኢትዮጵያዊ በሞራሉ፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ በዕውቀቱ እና በሕዝብ ለሕዝብ (ፐብሊክ) ዲፕሎማሲ ረገድ ያደረገው ርብርብ በታሪክ ማኅደር በትልቅ ስፍራ ተመዝግቦ በትውልድ የሚዘከር ሕያው ድል ነው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግድብን ከመገንባት ባለፈ የቁጠባ ባህላችንን በማሳደግ፤ የሀገራችንን ገፅታ በመገንባት፤ የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና በማላበስ የተመፅዋችነትና አንችልምን መንፈስ በመስበር፤ በምትኩ ከተባበርን ያቀድነውን ማሳካት እንደምንችል ያሳየን፤ የአንድነታችንና ጽናታችን ማሳያ የሆነ፤ የዚህ ትውልድ አዲስ ትርክት ሆኖ የተመዘገበ የዘመናችን ዓድዋ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቦ ለግድቡ ግንባታ ውሏል። ግድባችን በመላው ሕዝባችንና በመንግሥት ቁርጠኛ አቋም ለዚህ ደረጃ በመብቃቱ ኩራት ይሰማናልም ብለዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ዓመታት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ያደረግን ቢሆንም አቅማችንን አሟጠን ደግፈናል ማለት እንደማይቻል የገለጹት አረጋዊ (ዶ/ር)፤ አንዳንዱ ምንም ከሌለው ላይ ከዕለት ጉርሱ ከዓመት ልብሱ ቆጥቦ ድጋፍ ያደረገ እንዳለ ሁሉ፤ ተጨማሪ ድጋፍና ዐሻራ ማስቀመጥ የሚገባው የኅብረተሰብ ክፍል እንዳለም ጠቁመዋል።

የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የህዳሴ ግድብ የመሠረት-ድንጋይ ከተቀመጠበት ዕለት ጀምሮ የፀጥታና ሰላም ሥራዎችን ሠርተዋል። ምንም እንኳን አካባቢው ጠረፋማ ቢሆንም የተመቻቸ ሁኔታ ባልነበረበት ወቅት ጫካ መንጥሮ የሣር ጎጆ በመቀለስ አስቸጋሪውን የአየር ፀባይ ተቋቁሞ የግድቡን ሥራ እውን የሚያደርጉ የግድቡ ሠራተኞችና ባለሙያዎችን ደኅንነት እንዲሁም ፕሮጀክቱን 7 ቀን 24 ሰዓት ያለአንዳች ችግር እንዲሠራ የራሳቸውን ድርሻ ተወጥተዋል። ሁሉም በየዘርፉ ባደረገው ትብብር እና ርብርብም የዘመናት ቁጭት ሊቋጭ የክረምቱን መገባደድ ይጠብቃል።

በመክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You