ኢንስቲትዩቱ የተመናመኑ የእንስሳት ዝርያዎችን ከመጥፋት ለመታደግ እየሠራ ነው

 -የቁንዱዶ ፈረሶችና የሻኮ ዳልጋ ከብቶች ቁጥርን መጨመር ተችሏል

አዲስ አበባ፡- የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን እንስሳት በመለየት እና የወንድ አባላዘር ሰብስቦ በማሰራጨት የተመናመኑ የእንስሳት ዝርያዎችን ከመጥፋት አደጋ ለመታደግ እየሠራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በተሠራው ሥራም የቁንዱዶ ፈረሶችና የሻኮ ዳልጋ ከብቶች ቁጥርን መጨመር መቻሉን ተጠቁሟል።

በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተስፉ ፈከንሳ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የሻኮ ዳልጋ ከብቶች አራት ሺህ ብቻ ቀርተው የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸው የነበረ ሲሆን፤ የወንድ አባላዘር በመሰብሰብ መልሶ በማሰራጨት በተሠራው የማባዛት ሥራ አሁን ላይ ቁጥራቸው ወደ ስምንት ሺህ ከፍ ማለት ችሏል።

ቁንዱዶ ፈረስ በአፍሪካ አሕጉር በኢትዮጵያ እና ናሚቢያ የሚኖር የዱር ፈረስ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህም የፈረስ ዝርያ ስድስት ብቻ በመቅረቱ የመጥፋት አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር አስታውሰው፤ በተሠራው ሥራ አሁን 43 ማድረስ መቻሉን ጠቅሰው፤ ነገር ግን አሁንም ቁጥሩ ዝቅተኛ ስለሆነ ቀጣይ ሥራዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

ረግረጋማ ቦታዎችን እና ዱሮችን በመጠበቅ እንስሳትን መጠበቅ ይቻላል የሚሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ በርካታ እንስሳትን ባሉበት ቦታዎች የማኅበራዊ ጥበቃ ባንክ በማቋቋም ለመጠበቅ ተችሏል። ምንም እንኳን ቦታዎቹ 24 ቢሆኑም በእነዚህ ቦታዎች  በሺዎች የሚቆጠሩ የእንስሳት ዝርያዎች መጠበቃቸውን አስረድተዋል።

እንስሳቱ ለመመናመናቸው ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ተፈጥሮ ነው ያሉት ተስፉ (ዶ/ር)፤ ጫካ ሲመነጠር ምግባቸው እንዲሁም መጠለያቸው ስለሚጠፋ የዱር እንስሳት ይጠፋሉ፤ ስለሆነም ተፈጥሮ እንዲመናመን የሚያደርገው ሰው ነው ብለዋል።

በኢንስቲትዩት የሚሠሩ ሥራዎች በ10 ዓመት ታቅደው በየዓመቱ ተከፋፍለው እንደሚሠሩም አስረድተዋል። ከዚህ አንጻር በዘንድሮ ዓመት 5ሺህ የወንድ አባላዘር ለመሰብሰብ እና ሁለት የባሕሪ ትንተና ማለትም የናሙናዎቹን የይዘት ጥናት ለማድረግ የታቀደ ሲሆን በበጀት ዓመቱ የታቀዱ እቅዶች ሙሉ በሙሉ መሳካታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የዘረመል ጥናት ለማድረግ የተመቻቸ ቤተ ሙከራ ባለመኖሩ፤ አዳዲስ ዝርያዎችን ከማግኘት አንፃር ከውጭ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሠራ ጠቅሰው፤ በዚህ ሂደትም በተለይ በዱር እንስሳት በርካታ አዳዲስ እንስሳት እየተገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። በዘንድሮ ዓመት ስድስት የጀርባ አጥንት የሌላቸውን አዳዲስ ዝርያዎች ማስመዝገብ እንደተቻለም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የእሳት እራት እና ቢራቢሮን ጨምሮ በአጠቃላይ የጀርባ አጥንት የሌላቸው ዝርያዎች 2ሺህ 438 ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ 664 የሚሆኑት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የብዝኃ ሕይወት ከእያንዳንዱ የሰዎች እንቅስቃሴ ጋር  የተያያዘ ነው የሚሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ እያንዳንዱ እንስሳት በተገቢው ሁኔታ መጠበቅ ይኖርበታል ብለዋል። ለዚህም በቀጣይ ከክልሎች፤ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ከምርምር አካላት ጋር በቅንጅት የመሥራት ሃሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You