“ተመዝነው መሻሻል ያላሳዩ 28 ትምህርት ቤቶች በመጪው ዓመት መመዝገብ አይችሉም”- አቶ ኢዘዲን ሙስባህ

 አቶ ኢዘዲን ሙስባህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ

አዲስ አበባ፡– ከጥራት አኳያ ተደጋግመው ተመዝነው መሻሻል ያላሳዩ 28 ትምህርት ቤቶች በ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብለው መመዝገብ እንደማይችሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዘዲን ሙስባህ አስታወቁ፡፡

አቶ ኢዘዲን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ ባለሥልጣኑ ትምህርት ቤ ቶች፣ በመደበኛ ዕውቅና እድሳት ላይ ቁጥጥር (ኢንስፔክሽን) ሲያደርግ በማረጋገጫ ዝርዝሩ (checklist) መሠረት ተመዝነው ከደረጃ በታች ሆነው ሲገኙ ተገቢነት ያላቸው ርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። በተደረገ ኢንስፔክሽን 28 ትምህርት ቤቶችን ከጥራት አኳያ ደጋግመው ተመዝነው መስፈርቱን ማሟላት ባለመቻላቸው ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ይሁንና መሻሻል ማሳየት ስላልቻሉ በ2018 የትምህርት ዘመን ምዝገባ ማከናወን አይችሉም።

ትምህርት ቤቶቹ፣ ያላቸው አማራጭ፤ በአዲስ መልክ ራሳቸውን አደራጅተውና ብቁ ግብዓት ፈጥረው የሚፈለገውን መስፈርት ማሟላት ነው፤ መስፈርቱን አሟልተው ከተገኙና ፈቃድ ከጠየቁ ሊያሰጣቸው የሚያስችል ዕድል መኖሩን ጠቁመው፤ ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለአብነት ያህል ሦስቱ በዚህ መንገድ ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

እንደ አቶ ኢዘዲን ገለጻ፤ ርምጃ የሚወሰደው የትምህርት ዘመኑ ከማለቁ በፊት ከሦስት ወር በፊት በደብዳቤ እንዲያውቁ ይደረጋል። የተጠቀሱት 28ቱ ትምህርት ቤቶችም በዚህ አግባብ በደብዳቤ እንዲያውቁት ተደርጓል። ለ2018 የትምህርት ዘመን ተማሪ መመዝገብ እንደማይችሉ በደብዳቤ ተገልጾላቸዋል።

በእርግጥ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በጥልቀት ስናጤን በተገቢው መንገድ በደንብ አልታየልንም፤ ሦስትና አራት ጊዜ ቢመዘንም አምስት ጊዜ ድረስ መታየት አለብን የሚል ቅሬታ አላቸው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በመሆኑም መንግሥት ቅሬታቸውን ለማዳመጥ ዝግጁ ነው። ነገር ግን የሚጨምሩትና የሚቀንሱት እስከሌለ ድረስ የሚሻለው ነገር ዕውቅናቸውን ማንሳት እና ለኅብረተሰቡ ማሳወቅ ነው። ደረጃቸውን ባልጠበቁ ትምህርት ቤቶች ትውልድን ማስተማር አግባብነት የለውም ብለዋል።

ድንገተኛ ኢንስፔክሽን በማድረግ የሥርዓተ ትምህርት ጥሰት ያደረጉ ትምህርት ቤቶች ተገኝተዋል ያሉት አቶ ኢዘዲን፣ 585 ትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃቅን ጉዳዮች፤ ነገር ግን ቀላል ግምት የማይሰጣቸው እንደ ጊዜ ማዛባት፤ ያልተፈቀዱ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ማለትም በሥርዓተ ትምህርቱ (ካሪኩለሙ) ያልገቡ መጽሐፍትን ተጨማሪ አድርጎ መጠቀም፣ የትምህርት ጥራትን የሚያጓድሉ ጉዳዮች በመሆናቸው በተደረገው ድንገተኛ ኢንስፔክሽን ወዲያውኑ እንዲታረሙ አድርገናል ብለዋል።

ኢንስፔክሽን የሚካሄደው ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ በተቀመጠለት መሠረት ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ድንገተኛ ኢንስፔክሽን ይሠራል። በዚህም ከክፍያ ጋር ተያይዞ ወደ 133 ትምህርት ቤቶች ታይተው የ2017 በጀት ዓመት የትምህርት የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓቱ ምንድን ነው? በፀደቀው አሠራር መሠረት እየሠሩ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ለመፈተሽ ሲሠራ 55 ትምህርት ቤቶች ከተባለው በላይ ጭማሪ እያስከፈሉ መሆኑን እንደደረሱበት ገልጸዋል። በዚህም የተጨመረው ገንዘብ እንዲመልሱ አደርገናል ብለዋል።

በዚህና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከአቶ ኢዘዲን ሙስባህ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በተጠየቅ ዓምዳችን ገጽ 6 እና 7 ያገኙታል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You