
ዜና ትንታኔ
የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት በጀት አንድ ነጥብ ዘጠኝ ትሪሊዮን ብር ሆኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡
ከ2018 በጀት አንድ ነጥብ ሁለት ትሪሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 415 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ፣ 315 ቢሊዮን ብር ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንዲሁም 14 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ ድጋፍ የሚውል ነው ተብሏል።
የበጀቱን መግለጫ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደተናገሩት፤ ከበጀቱ አንድ ትሪሊዮን ብር ወይም 73 በመቶውን ከታክስ ገቢ፣ 236 ቢሊዮን ብር ከልማት አጋሮች፣ ቀሪውን ደግሞ ከፕሮጀክቶች ድጋፍ እና ልዩ ልዩ ገቢዎች ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል።
በጀቱ ከጥቅል ሀገራዊ ምርት አንፃር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት ሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ እንዲሁም የተጣራ የበጀት ጉድለት አንድ በመቶ መኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን በቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ ብድር በመውሰድ ሳይሆን በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ እንደሚሸፍን መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ለመሆኑ የ2018 የፌዴራል መንግሥት በጀት ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ይናገራል? ስንል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ እንዲሁም በአፍሪካ ኅብረት የፀረ-ሙስና አማካሪ ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው የሠሩትንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በመምህርነት ያገለገሉትን የምጣኔ ሀብት ምሑር ቆስጠንጢኖስ በርሄተስፋ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑትን ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ጠይቀናል።
ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፤ በጀት መንግሥት በቀጣይ ሊሠራቸው ያሰባቸውን ዕቅድ ያሳያል። ይህም በገንዘብ የተተረጎመ ዕቅድ ሊባል ይችላል፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተደረገ የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት በየዓመቱ እያደገ መጥቷል፡፡
ለ2018 የተያዘው በጀት በውጭ ምንዛሪ መጠን ሲታይ ብዙም ከፍ ያለ አይደለም። እንዲሁም ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገባው ቁሳቁስም ጋር ሲነጻጸር የተያዘው በጀት ከፍተኛ ነው የሚባል አይደለም። ነገር ግን ለመደበኛ ወጪ፣ ለካፒታል ወጪ እና ሌሎች ወጪዎች የተያዘው በጀት የሀገሪቱን የእድገት ሁኔታ ለማስቀጠል የሚያስችል ነው ብለዋል።
መንግሥት በ2018 ረቂቅ በጀቱ አንድ ትሪሊዮን ብር ወይም 73 በመቶውን ከታክስ ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልጿል ያሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ መንግሥት ለ2018 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ ዘጠኝ ትሪሊዮን ብር መበጀቱ ገቢ የመሰብሰብ አቅሙ እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያሳይ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ታክስ በመሰብሰብ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ስትነፃጸር ገና ያልተነኩ አቅሞች እንዳሏት ገልጸዋል፤ በደርግ ዘመነ መንግሥት ገበሬው እንዳይጎዳ በሚል ታክስ በተገቢው መልኩ አይሰበስብም ነበር፤ ይህም 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ታክስ የማይከፍልበት ሁኔታ እንደነበር ይጠቁማል ነው ያሉት።
አሁን መንግሥት ታክስ የመሰብሰብ አቅሙን ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን መመልከት አለበት። በኢትዮጵያ የተጀመረው ዲጂታል ኢኮኖሚ ታክስ የመሰብሰብ አቅምን እንደሚያሳድግ አመልክተው፤ በዚህም እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ብዛት አንፃር የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በመጀመር እና ሌሎች ሕዝቡ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች ማሳደግ የሚቻልበት ሁኔታን መፍጠር አስፈላጊ ነው። በዚህም የሀገሪቱን እድገት ማስቀጠል እንደሚቻል ገልጸዋል።
መንግሥት ለ2018 በጀት ዓመት የመደበው ገንዘብ ከ2017 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ376 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አለው። ጭማሪውም ለሥራ ዕድል፣ በጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት፣ ሰብዓዊ ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የዋጋ ግሽበትን ከ30 በመቶ ወደ 14 በመቶ እና ከዚያ በታች ማውረድ እንደተቻለ ብሔራዊ ባንክ ገልጿል። ይህንንም ከሁለት በመቶ በታች ማውረድ እንደሚገባ ጠቁመው፤ ከሦስት በመቶ በላይ የዋጋ ግሽበት የሕዝቡን ኑሮ ችግር ውስጥ እንደሚከት ጠቁመዋል።
መንግሥት ለቀጣይ በጀት ዓመት ከያዘው ገንዘብ ያለአግባብ በግለሰቦች እጅ ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ በማድረግ የመንግሥት ገንዘብ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የዋጋ ግሽበት እንዳያስከትል ያደርጋል። ለዚህም የኅብረተሰቡ፣ የሚዲያውና የማኅበረሰብ አንቂዎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ እና ቀደም ሲል በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር የነበሩት ሞላ ዓለማየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለ2018 የተያዘው በጀት ከአምናው በጀት ጋር ሲነፃፀር የሠላሳ በመቶ ጭማሪ እንዳለው ገልጸው፤ ገንዘቡ የዋጋ ግሽበትን እንዳያባብስ መጠንቀቅ ይገባል ብለዋል።
በበጀቱ እንደተገለጸው ከጥቅል ሀገራዊ ምርት አንፃር ያልተጣራ የበጀት ጉድለት ሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ እንዲሁም የተጣራ የበጀት ጉድለት አንድ በመቶ መኖሩን እንደተመላከተ ገልጸው፤ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ለመሸፈን እንደሚሠራ ገልጿል። ይህም የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ይረዳል ነው ያሉት።
መንግሥታት የበጀት ጉድለት ሲኖርባቸው የግምጃ ቤት ሽያጭ ጨረታ ያወጣሉ። ይህም መንግሥት ገበያው ላይ ያለውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ይጠቀምበታል። የሰበሰበውንም ገንዘብ ዘላቂ እድገት በሚያመጡ ልማቶች ላይ ማዋል ያስችለዋል። ስለዚህ በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ የሚገኝ ገንዘብ ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረጅም ጊዜ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግሥት በረቂቅ በጀቱ አንድ ትሪሊዮን ብር ወይም 73 በመቶውን ከታክስ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል። ይህ ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ሞላ (ዶ/ር)፤ ይህንን ገንዘብ መሰብሰብ ካልተቻለ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ስለዚህ መንግሥት በጎን በኩል ሌላ አማራጭ መያዝ እንዳለበት አመልክተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በስምንት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እንደሚያድግ የኢትዮጵያ መንግሥት ተንብይዋል። ይህ እድገት በግብርና፣ በአገልግሎት እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ እንደሚሆን ይጠበቃል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በበኩሉ፤ በ2018 ኢትዮጵያ የሰባት ነጥብ አንድ በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት ታስመዘግባለች ብሏል።
ሁለቱ የምጣኔ ሀብት ምሑራን እንደሚጠቁሙት፤ የኢኮኖሚ እድገት ከሀገር ውስጥ አቅም ባለፈ የዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ተፅዕኖም አለበት። ይህ ደግሞ የሀገራትን ኢኮኖሚ ሊያሳድግ ወይም ሊጎዳ ይችላል። ኢትዮጵያ ለካፒታል በጀት የመደበችው በጀት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማምጣት ያስችላል። ነገር ግን አሁን ላይ ኢትዮጵያ በዚህን ያህል መጠን እድገት ታስመዘግባለች ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል።
የ2018 በጀት የተሟላ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን እና የ10 ዓመቱን መሪ የልማት እቅድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ገልጸዋል።
ጥብቅ የገንዘብ እና የበጀት ፖሊሲን በመከተል የመንግሥት ወጪን በሀገራዊ ገቢ ለመሸፈን ትኩረት ይደረጋል። ይህም የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እና ውጤታማ የበጀት አጠቃቀምን ለመተግበር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም