የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ 30 ሺህ 444 የመምህራን መኖሪያ ቤት ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ፡በ2018 በጀት ዓመት እና ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› የሚል መሪ ሃሳብ ባለው የክረምት የዜግነት አገልግሎት 30 ሺህ 444 የመምህራን መኖሪያ ቤት ሊገነባ መሆኑን የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የትምህርት እንቅስቃሴ ከዛሬ ጀምሮ ይጀመራል ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ለገጠር መምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሕዝብ ተሳትፎም ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል ብለዋል።

በባለፈው የ2017 በጀት ዓመት 10 ሺህ 181 የመምህራን መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን አውስተው፤ ለመምህራን መኖሪያ ቤት ግንባታ ኅብረተሰቡ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አስተላልፈዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ በ2018 በጀት ዓመት ሁለት ሺህ 853 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች፣ 170 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ 1 ሺህ 577 የቅድመ መደበኛ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች፣ 460 ዲጂታል ፓርክ ይገነባል።

በበጀት ዓመቱ 361 ትምህርት ቤቶችን ሞዴል በማድረግ በትምህርት ቤቶች መካከል ጤናማ ፉክክር እንዲፈጠር ይደረጋል ብለዋል። የበጀት ዓመቱ ትምህርት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ በክልሉ መንግሥት ዕቅድ መያዙን የገለጹት ኃላፊው፤ ባለፈው ዓመት ተይዞ የነበረው በጀት 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻል በአዲሱ በጀት ዓመት 66 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተያዘ ተናግረዋል።

የትምህርት ዕቅዶችን ለማሳካት የመንግሥት በጀት ብቻውን በቂ ስለማይሆን ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ማንኛውም ግለሰብ በቻለው አቅም ድጋፍ እንዲያደርግ ይሠራል ብለዋል። ለትምህርት የተያዘውን በጀት ከፍ ለማድረግ ያስገደደበት ምክንያትም የሁሉም ነገር መሠረት ትምህርት መሆኑ በመንግሥት ስለታመነበት መሆኑን ጠቁመዋል።

‹‹20 ሺህ 340 መምህራን ለክረምት ሥልጠና ተዘጋጅተዋል›› ያሉት ቶላ በሪሶ(ዶ/ር)፤ የመምህራንን አቅም ለማሳደግ በየዘርፉ ሥልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል። በአጠቃላይም ከ52 ሺህ እስከ 60 ሺህ የሚሆኑ መምህራን ሥልጠና እንደሚወስዱ አመልክተዋል።

እንደ ትምህርት ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ ክፍል ባሉ ተማሪዎች የመጻፍና የማንበብ ችግር ተስተውሏል። የበጀት ዓመቱ ዋና ትኩረትም ለመምህራን ሥልጠና በመስጠት እስከ 5ኛ ክፍል ድረስ ማንበብና መጻፍ የማይችል ተማሪ እንዳይኖር ማድረግ ነው ብለዋል።

‹‹ማንበብና መጻፍ አለመቻል የትምህርት ድህነት ይባላል›› ያሉት ኃላፊው፤ ተማሪዎችን እንደየደረጃቸው ፊደል መለየት፣ ቃላት መለየት፣ አንቀጽ መለየት፣ ምንባብ መለየት እና በአጠቃላይ አንብቦ የመረዳት አቅማቸው ላይ በቂ ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

አምስተኛ ክፍል የደረሰ ተማሪ አንብቦ የመረዳት አቅሙን የጨረሰ መሆን አለበት ያሉት ኃላፊው፤ ለዚህም ለመምህራኑ ሥልጠና እንደሚሰጥ እና ለተማሪዎች የክረምት የማበረታቻ ትምህርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በዲጂታል ፓርክ ግንባታ ባለፈው በጀት ዓመት በአንድ ቢሮ ውስጥ 20 ኮምፒውተር እንዲኖር ተደርጓል፤ በተያዘው በጀት ዓመት ቁጥሩንና አይነቱን በመጨመር ተማሪዎች ከመደበኛው የክፍል ውስጥ ትምህርት በተጨማሪ የኮምፒውተር ትምህርት እንዲማሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

ዘመኑ የቴክኖሎጂ እንደመሆኑ ተማሪዎች ዘመኑን የሚመጥን ክፍሎች እንዲኖራቸው ታስቦ የተዘጋጀ ስለሆነ ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራበታል ብለዋል። ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› በሚለው የክረምት የዜግነት አገልግሎት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል አቅሙ በሚፈቅደው ልክ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You