ወጣቶች የአፍሪካ የወደፊት ተስፋዎችና የዕድገት አቅሞች እንደሆኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፡ወጣቶቻችን ጥንካሬዎቻችን፣ የወደፊት ተስፋዎቻችን እና የአኅጉራችን የዕድገት አቅሞች ናቸው ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ ሲከፈት እንዳሉት፤ አፍሪካ የወጣቶች፣ የእምቅ ተፈጥሮ ሀብት እና የመለወጥ ሕልም ያላት አኅጉር ናት። ወጣቶቻችን ጥንካሬዎቻችን፣ የወደፊት ተስፋዎቻችን እና የአኅጉራችን የዕድገት አቅሞች ናቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ፓን-አፍሪካዊ ተልዕኮ በቁርጠኝነት እየሠራች እንደሆነ አመልክተው፤ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራን ዋነኛ የትኩረት ማዕከል አድርጋ እየሠራች ትገኛለች። አፍሪካ የወጣቶች፣ የእምቅ ተፈጥሮ ሀብት እና የመለወጥ ሕልም ያላት አኅጉር ናት ብለዋል።

በአፍሪካ በርካታ የኃይል ተስፋ የሆኑ ወጣቶች እንዳሉ ገልጸው፤ ይህንን ኃይል ለመጠቀም በፓን አፍሪካ አንድነት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ወጣቶች በሁሉም ዘርፎች ላይ ወደኋላ እንዳይቀሩ እና ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ኢንቨስት ማድረግና ማበረታታት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

አፍሪካን የሚያስተሳስሩ መሠረተ ልማት አካታችነትን የሚያረጋግጡ ሥርዓቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸው፤ ለዚህ ደግሞ የወጣቱን ኃይል መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በተለይም በገጠር አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግብርና እሴት ሠንሠለት እየገነባች መሆኑን አመልክተው፤ ግብርናን ከማዘመን አንጻርም ከታችኛው ክላስተር ጀምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂ እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ተግባራዊ ማድረግ በጀመረችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም አቅምን እየገነባች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል፤ ለዚህ ስኬት ደግሞ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም የአፍሪካን ትብብር የሚያጠናክር እና ወጣቶች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርግ አመላካች ፎረም ነው ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐመድ አሊ የሱፍ በፎረሙ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፤ በአፍሪካ ግብርና ከ60 በመቶ በላይ የኑሮ ሁኔታን እንደ ዋና ፕሮግራም በመደገፍ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።

ከግብርና ባለፈም ሌሎች ዘርፎች ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ የሚያበረክቱትን አስተዋፅዖ እንዲያሳድጉ በትብብር መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል።

የአፍሪካ አኅጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ፣ ትልልቅና አነስተኛ የንግድ ተቋማት ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ የሥራ መስኮችን፣ ቴክኖሎጂን፣ በወጣቶች የሚሠሩ ፈጠራዎችን ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ጠቁመው፤ በአኅጉራችን ድህነትን የማጥፋት ግብ እውን ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ጥረት ላይ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል ብለዋል።

እ.ኤ.አ በ2050 የአፍሪካ ሕዝብ ቁጥር አሁን ካለበት በ60 በመቶ በመጨመር 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ገልጸው፤ ከሕዝብ ብዛቱ ጋር ተመጣጣኝ የሥራ ዕድል እንዲኖር መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ለማሳደግ የምታደርገው ሽግግር አስደናቂ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ፤ አሁን ላይ ከጤፍ ምርት አልፋ በቆሎ እና ሰንዴ በስፋት በማምረት ከሀገር አልፎ ወደውጭ እየላከች መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያን የምርቶች ኤግዚቢሽንን መጎብኘታቸውን ገልጸው፤ በጉብኝቱ የተመለከትኩት የምርቶች ጥራት በጣም አስደናቂ ነው ብለዋል።

ሄርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You