“ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ብሔራዊ ጥቅሟንና የገለልተኝነት መርሕን አማክላ አቋሟን በሚገባ አንፀባርቃለች” – ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ በ17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ብሔራዊ ጥቅሟንና የገለልተኝነት መርሕን ማዕከል አድርጋ አቋሟን በሚገባ ማንፀባረቋን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

17ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ ተካሂዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው በጉባኤው ላይ ተሳትፈዋል።

ሚኒስትሩ ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሪዮ ዴጄኔሮ ያቀኑት በጉባኤው ላይ ለመሳተፍና ከሀገራት መሪዎች ጋር በመወያያት የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል። መሪዎቹ ከተወያዩባቸው ዓበይት አጀንዳዎች መካከል አካታች እና ፍትሐዊ የዓለም አስተዳደር ሥርዓት እና ሪፎርም ይገኝበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና የገለልተኝነት መርሕን መሠረት በማድረግ ዓለም ሁሉንም አካባቢ ማቀፍ እንደሚገባው እና የአፍሪካ ድምፅ በሁሉም የዓለም ተቋማት እኩል መደመጥ እንዳለበት ማንሳታቸውን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

አፍሪካ ከመደመጥ ባሻገር ተሳትፎዋ ሊያድግ እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸውን አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ለደቡብ ትብብርን ማጠናከርን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት የረጅም ጊዜ ሥልጣኔ፣ ብዝኃ ባህል እና ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላትን የባህልና የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር እና ልምድ ለመቅሰም እንደምትሠራ ተናግረዋል።

ከኢኮኖሚ እና ከፋይናንስ ጋር በተገናኘም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከብሪክስ ጋር ባላት ትብብር ተጠቃሚ እየሆነች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የብሪክስ ልማት ባንክ ዓይነት የፋይናንስ ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ኢ-ፍትሐዊ የፋይናንስ እና የብድር አቅርቦት አማራጭ መሆናቸውንና ኢትዮጵያ ከዚህ ተጠቃሚ እንደምትሆን ነው ያነሱት።

ዲጂታላይዜሽን እና ሰው ሠራሽ አስተውሎትም ሌላኛው የውይይቱ ርዕሰ ጉዳይ ነበር። ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ዓለሙ ይዞ የመጣቸውን መልካም ዕድሎች የበለጠ መጠቀም እና ስጋቶችን ለመቀነስ በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ሰፋፊ ሥራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ እና በዘርፉ ከብሪክስ ሀገራት ጋር በትብብር መሥራት እንደምትሻ ጠቅሰዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከንግግር ባለፈ በተግባር ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ሥራ እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተሳካ ተሳትፎ ማድረጓን ጠቁመዋል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You