
አዲስ አበባ፡– ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሃሳብ ተነስቶ ለዓለም አቀፍ ለውጥ የሚሠራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪዮ ዲ ጄኔሮ በተካሔደው 17ኛው የብሪክስ ጉባዔ የሰላም፣ የፀጥታ እና ዓለምአቀፍ አመራር መድረክ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳሉት፤ “ብሪክስ ከጠንካራ አዲስ ሃሳብ ተነስቶ ለዓለምአቀፍ ለውጥ የሚሠራ ብርቱ ኃይል ወደመሆን ተሸጋግሯል። አዳዲስ አባላት በመጨመራቸውም የጋራ ድምፃችን የበለጠ ይጠናከራል፤ የጋራ ዓላማችን የበለጠ ይጠራል፤ አቅማችንም ይሰፋል ብለዋል፡፡
ስኬታማ ትብብርን ለማስቻል አፀፋዊ መተማመንን የሚያሳድጉ ዓለምአቀፍ ተቋማት የመኖርን አጣዳፊነት አንስተው፤ ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማት የጋራ ደኅንነትን እና ሁሉን አካታች ብልፅግናን ለማምጣት ይረዳ ዘንድ የውሳኔ አሰጣጥ መዋቅራቸው ምሉዕነት ባለው መልክ የሚሻሻልበትን ሁኔታም አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በይፋ ወደ ብሪክስ የተቀላቀለችው በ2015 ዓ.ም ሲሆን ኢኮኖሚያዊ ወዳጅነት ብቻ ሳይሆን ፍትሐዊ የሆነ፣ እኩልነት የሚሰፍንበት ብዝኃ ዋልታዊ ዓለምን ለመፍጠር ከሚተጉ ሀገራት ጋር በእኩል ደረጃ የተሰለፈችበት ስብስብ ነው ብለዋል።
እንደ ብሪክስ አባልነቷ ኢትዮጵያ እነዚህ ጥረቶች እንዲሳኩ በተለይም በዓለምአቀፍ ውሳኔ ሰጪ መድረኮች ለአዳዲስ ገበያዎች እና በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ሰፋ ያለ ውክልና በሚገኝበት ሁኔታ ላይ በንቃት አስተዋፅዖ ታደርጋለች።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የብሪክስ አባል ሀገራት የበለጠ እኩልነት እና ፍትሕ የሰፈነበት ዓለም ለማግኘት ትስስራችንን የበለጠ እናጠናክራለን። የብሪክስ መድረክ የጋራ የልማት እና ዓለምአቀፋዊ ትብብርን በማሳደግ ረገድ ጠቃሚ ሆኖ ቀጥሏል።
ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱትንና “ብሪክስ” በሚል ስያሜ የሚታወቀውን ኅብረት ኢትዮጵያ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛው የቡድኑ አባል ሀገራት ጉባኤ መቀላቀሏ ይፋ መሆኑ ይታወቃል። ብሪክስ ኢትዮጵያን ጨምሮ፥ አርጀንቲና፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያን እና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችን በአዲስ አባልነት የተቀበለ ሲሆን፤ ይህ አዲስ ጥምረት ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በምዕራቡ ዓለም ፍላጎቶችና ጥቅሞች መሠረት ሲነዳ የነበረው ዓለም አቀፍ ሥርዓት በተለይ በታዳጊ ሀገራት ልማት፣ ኢኮኖሚ፣ ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነት እና የፖሊሲ ነፃነት ላይ ዘርፈ ብዙ የሆኑ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እንደሚቀንስ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ከፍተኛ የሆነ የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድልን በማስፋት፤ የውጭ ምንዛሪ መዋዥቅን በመቀነስ፤ ጂኦፖለቲካዊ ተፅዕኖን በማሳደግ፤ የፋይናንስ ተቋማትን በማሳደግ ጉልህ ሚና ያበረክታል።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም