
አዲስ አበባ፡- እንደ ሀገር በሆስፒታል ከሚሞቱ ሰዎች አምስት ነጥብ አራት በመቶው በመኪና አደጋ ምክንያት መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የመንገድ ደህንነት እና መድህን ፈንድ አገልግሎት የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከሲቪክ ማህበራት ጋር ሰሞኑን ውይይት ባደረገበት ወቅት፤ በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢልባቡር ቡኖ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት ፤ የጥናት መረጃዎች እንደሚያሳዩት እንደ ሀገር በሆስፒታል ከሚሞቱ ሰዎች አምስት ነጥብ አራት በመቶ በመኪና አደጋ ምክንያት የሚሞቱ ናቸው።
ከተላላፊ እና ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ቀጥሎ በገዳይነት የመኪና አደጋን ጨምሮ አደጋ በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠ መሆኑን ያነሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ እ አ አ 2021 የዓለም ጤና ድርጅት ያጠናው ጥናት እንደሚያሳየው በአፍሪካ ከመቶ ሺህ ሰዎች 28 ሰዎች በመኪና አደጋ ይሞታሉ።
እንደሀገር ከ130 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ያለ ቢሆንም፤ ያለው የመኪና ቁጥር አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን እንኳን አይሞላም ያሉት ኢልባቡር (ዶ/ር)፤ ይህም ሆኖ ግን በመኪና አደጋ በየዓመቱ የሚደርሰው አደጋ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው። እየሞተ ያለው አምራች የሆነው ዜጋ መሆኑ ደግሞ አሳሳቢ ነው ብለዋል።
በዘውዲቱ ሆስፒታል በተደረገ ጥናት ሆስፒታል ገብተው ከሚታከሙ ሰዎች ስምንት በመቶው በመኪና አደጋ ምክንያት ድንገተኛ ክፍል የሚገቡት ናቸው። በተመሳሳይ ጥቁር አንበሳ 36 በመቶ ነው ያሉት ዶክተሩ ፤ አንዳንድ ቦታዎች ላይ አሀዙ 48 በመቶ እንደሚደርስ አስታውቀዋል ። የድንገተኛ ህክምና የሚያገኙት ከሰባት እስከ 10 በመቶ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የግልና የመንግሥትን ጨምሮ በኢትዮጵያ 22 ሺህ የጤና ተቋማት አሉ። ካለው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ሲታይ ዝቅተኛ መሆኑን በማንሳት፤ በመኪና አደጋ ሆስፒታል የሚገባ ሰው ቁጥር እየጨመረ በሄደ ቁጥር ጫናው እየሰፋ ይሄዳል ብለዋል።
የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ ሀሰን በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የ2017 ዓ.ም የዘጠኝ ወር መረጃ ሲታይ የተከሰተው የመኪና አደጋ እና የሞት ምጣኔ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የጨመረበት ሁኔታ መኖሩን አስታውቀዋል።
በዚህም በዘንድሮ ዓመት በዘጠኝ ወር የተከሰተው የመኪና አደጋ ከባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ አራት በመቶ ጭማሪ አለው። ይህም በቁጥር 489 ሲሆን፤ የሞት ቁጥርም በ474 መጨመሩን አመልክተዋል።
በዘንድሮ ዓመት ባልተለመደ መልኩ በመኪና አደጋ በጅምላ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ጠቁመው፤ በዚህ ዓመት የትግራይ ክልልን መረጃ መካተቱ ቁጥሩን ከፍ እንዳደረገው አስታውቀዋል።
ከዚህ በፊት ለአገልግሎቱ ሪፖርት የሚደረገው በዋና ዋና መንገዶች ብቻ የተከሰተ አደጋ ነበር ፤ አሁን ሁሉም ሪፖርት እንዲደረግ አሠራር መዘርጋቱ ለቁጥሩ ከፍ ማለት ሌላው ምክንያት እንደሆነም አመልክተዋል።
በአደጋ መከሰት ከንግድ መኪኖች ቀጥሎ ሲቪክ ማህበራት ሁለተኛውን ደረጃ እንደሚይዙ በመግለጽ፤ ችግሩን ለመቀነስ በግንዛቤ፤ በሠብዓዊ ድጋፍ የሲቪክ ማህበራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም