ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብራዚል ፕሬዚዳንት እና ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መወያየታቸውን አስታወቁ

አዲስ አበባ ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ17ኛው የብሪክስ ጉባዔ አስቀድሞ ከብራዚል ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫ ጋር መወያየታቸውን አስታወቁ። ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ም በተመሳሳይ መወያየታቸውን አመለከቱ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ከትናንት በስቲያ እንዳስታወቁት 17ኛው የብሪክስ ጉባዔ አስቀድሞ ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናቺዮ ሉላ ደ ሲልቫ ጋር ተገናኝተን በሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል።

ውይይታችን በቅርብ እያደገ የመጣውን የሁለቱ ሀገሮቻችንን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ረገድ አንድ ርምጃ ወደፊት የወሰደን ነው ብለዋል። በተለያዩ ዘርፎች የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትስስሮቻችንን የበለጠ ለማጠናከር መስማማታቸውንም አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ጋር 55 ዓመታትን ባስቆጠረው የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ላይ ትናንት መወያየታቸውን አስታውቀዋል። የሀገራቱ ግንኙነት በሁኔታዎች ሁሉ እንደማይቀያየር አጋሮች (all weather strategic partners) ባለፉት ሰባት ዓመታት ትብብራችን ጉልህ ፍሬዎችን አፍርቷል ብለዋል።

ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና አይሲቲን ባካተቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ዓምዶች ላይ ትኩረታችን እንዳለ ሆኖ ሌሎች የትብብር መስኮችን ለማጠናከርና እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ሎጂስቲክስ እና ንጹሕ የኃይል ምንጮች ልማት ላይ ያለንን ዕምቅ አቅም ለመመልከትም ችለናል ብለዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You