ወጣቱ በጋራ ራእይ በመመራት ለሀገር ግንባታ ቁልፍ ሚናውን ሊወጣ ይገባል

አዲስ አበባ፡- ወጣቱ ትውልድ በጋራ ራእይ በመመራት ለሀገር ግንባታ ያለውን ሚና በቁርጠኝነት ሊወጣ እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።

የሰላም ሚኒስቴር ከወጣት አደረጃጀት ጋር በመሆን “ሀገሬን እገነባለሁ፣ ኃላፊነቴንም እወጣለሁ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሀገር አቀፍ የወጣቶች የሰላም ንቅናቄ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ትናንት ሲጠናቀቅ አቶ አደም ፋራህ እንዳስታወቁት፤ የኢትዮጵያ የማደግ እድል እውን የሚሆነው ወጣቱ ዜጋ በጋራ የድርሻውን ማበርከት ሲችል ነው። ለጋራ ራእይ በመቆም ለሀገር ግንባታ የበኩሉን ድርሻ በቁርጠኝነት ሲወጣ ነው።

ኢትዮጵያ በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚው፤ በማህበራዊ እና በዲፕሎማሲያው ዘርፍ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በጊዜ የተከፋፈለ ትልቅ ህልምና ራእይ ይዛ እየሠራች መሆኑን ያመለከቱት አቶ አደም፤ መንግሥት ወጣቱ የዛሬዋን እና የነገዋን ኢትዮጵያ የሚንያንቀሳቅስ ኃይል እንደሆነ በሰፊው ስለሚረዳ፤ በሀገር እና በወጣቱ ትውልድ መካከል ያለው ውል እንዲጠናከር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።

ወጣቱ ዜጋ በሰላም እሴት ግንባታ ላይ በስፋት በመሳተፍ የሚነሱ ጥያቄዎች፤ የሕዝብ ጥያቄ ናቸው የሚለውን መለየት እና ከፀብ ጠማቂዎች እራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ አደም፤ የሚነሱ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል ።

ሀገር ለወጣቶች ማድረግ ከሚገባት ነገሮች መሀከል በዋናነት የሚጠቀሱት ማስተማር፤ በተለያዩ ዘርፍ አካታችነትን ማረጋገጥ፤ የወጣት ድምፅ እንዲሰማ ምቹ መንገድ መፍጠር እና የወጣቶችን ተስፋ የሚያለመልም ሥራ መሥራት መሆኑን አመልክተው፤ መንግሥት በእነዚህ ላይ ሲሠራ ቆይቷል፤ በቀጣይም የሚሠራ ይሆናል ብለዋል።

ሀገር ከመገንባት እንዲሁም፤ ኃላፊነት ከመወጣት አንፃር ወጣቱ ዓለምን በተረዳ መልኩ ትልቅ ራእይ ኖሮት መዘጋጀት፤ ሥራን ሳይንቅ በመሥራት ሀገርን ሊያገለግል፤ ሕግን በማክበር ለሀገር እና ለሕዝብ በመቆም መልካም ሥነምግባር ሊያዳብር ይገባልም፤ በአጠቃላይ ተግባሩ ሕብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክር ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው እንዳስታወቁት፤ ወጣቶች ዛሬ ላይ በመሥራት ነገ በሚረከቧት ሀገር ትልቅ ሚና፤ ለሀገር ግንባታ እና ለሰላም መስፈን ብርቱ ጉልበት አላቸው።

የዚህ ዘመን ወጣቶች የሕዝብ ፍቅር በመላበስ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ወደ ድል በመቀየር ጉልበታቸውን እና አቅማቸውን ለሀገር ግንባታ ብሎም ልማት ሊጠቀሙት እንደሚገባም አመልክተዋል።

እንደ ሀገር ወጣቶች ትልቁን የሕዝብ ድርሻ የሚይዙ እንደመሆናቸው፤ በማህበራዊ ትስስር እና ሀገራዊ አንድነት የሚጫወቱት ሚና ቀላል የሚባል አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት፤ በመግባባት እንዲፈቱ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ዘመናዊ ሚዲያ ጥሩ እድሎች ያሉት ቢሆንም፤ አላግባብ የወጣቱን ጊዜ በመውሰድ እንዲሁም፤ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ትልቅ ተግዳሮት እያስከተለ ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግ ወጣቱ ትውልድ በአግባቡ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ሊጠቀም እና ሀሰተኛ መረጃዎችን በሰከነ መንፈስ ሊያጣራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

ሀገራዊ የወጣት ንቅናቄ መድረኩ ላለፉት አንድ ወራት በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ሲካሄድ ቆይቶ የማጠቃለያ ውይይት ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከተሳተፉ ወጣቶች ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂደዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You