በጋምቤላ ክልል በመኸር እርሻ 178 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን ታቅዷል

ጋምቤላ፦ በጋምቤላ ክልል በመኸር እርሻ 178 ሺህ ሄክታር በሰብል በመሸፈን አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ እርሻ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ። ማዳበሪያ የመጠቀም ግንዛቤ ችግር መኖሩን ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉኣል ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በመኸር እርሻ 178 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በዝግጅት ሥራዎቹም በተለያዩ የኩታገጠም ኢንሺየቲቮችን በማቀናጀት እየተሠራ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ኡጁሉ፤ አሁን ላይ በክልሉ የግብአት ተደራሽነት ውስንነት መኖሩን አመልክተዋል።

ከአፈር ማዳበሪያ ጋር በተያያዘ ክልሉ በእዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 60 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ የሚያገኝበት የኮታ ሥርዓት ውስጥ መታቀፉንም አስታውቀዋል። የክልሉ ኮታ በቀጥታ ከጅቡቲ ወደብ ወደ ክልሉ እየደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከእዚህ ጋር ተያይዞ የሰብል ማዳበሪያ የመጠቀም ግንዛቤ ችግር መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህም ስርጭቱ ላይ ተግዳሮት እንደሆነ አመልክተዋል። እስካሁን 38 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ ገብቶ ለተወሰኑ አርሶ አደሮች መከፋፈሉን ገልጸዋል።

የማዳበሪያ እና ሌሎች የግብርና ግብአት አቅርቦቶችን ለማሳደግ በግል አልሚዎች እና በአርሶ አደሮች ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ የዘር ብዜትን በተመለከተ በክልሉ ዘር አባዢ ድርጅት አለመኖሩን፤ የቴክኖሎጂ እና የፋይናንስ ተደራሽነትና ውስንነት ችግሮች መኖራቸውንም አስታውቀዋል።

ክልሉ ሩዝ ለማምረት ምቹ መሆኑን ጠቁመው፤ ሩዝ በክልሉ በትኩረት ለማምረት ከተለዩ አስር የሰብል ዓይነቶች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል። በክልሉ በቅድሚያነት በቆሎ፣ ሩዝ፣ አኩሪ አተር፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ስንዴ እና የዓሳ እርባታ፣ እንስሳት እርባታ፣ የዶሮ እርባታ እና መኖ ልማት ተለይተው በትኩረት እየተሠራባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You