
– ሀገሪቱ ያልተጠቀመችው ከ150 ጊጋ ዋት በላይ የታዳሽ ኃይል አቅም አላት
አዲስ አበባ፦ በ2030 በብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ሦስት 65 በመቶ የሚሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ኢትዮጵያ ከፀሐይ ኃይል፣ ከውሃ፣ ከንፋስ እና ከከርሰ ምድር ሙቀት ያልተጠቀመችው ከ150 ጊጋ ዋት በላይ የታዳሽ ኃይል እቅም እንዳላት ገለጸ።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ዋሊ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የዜጎችን የኃይል አቅርቦትንና ተደራሽነትን ማሳደግ ለሁሉም ዘመናዊ ሕይወት መሠረት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት አብዛኛው የኃይል ምንጭ ማገዶ በመሆኑ በሴቶችና ሕጻናት ጤና ላይ የሚያስከትለውን ችግር ለመቅረፍ የራሱ በጎ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ኢትዮጵያ የዜጎቿን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ንጹህና ታዳሽ ኃይል በማልማት ላይ እንደሆነች ያመለከቱት ኃላፊው፤ የኃይል አቅርቦቱን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ለማድረግ የፖሊ የኢኮኖሚ እድገት፣ የፋብሪካ መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ፣ የመኖሪያ ቤቶች መስፋፋትን ተከትሎ ፣ ለሰባት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየውን ብሔራዊ ኤሌክትሪፍኬሽን ፕሮግራም ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አመልክተዋል።
አሁን ላይ ፕሮግራሙን የመከለስ ሥራ እየተሠራ ነው፤ በቀጣይ ዓመት ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ሦስት በሚል ማሻሻያው ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
እንደ ኢንጅነር ሱልጣን (ዶ/ር) ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከፀሐይ ኃይል፣ ከውሃ፣ ከንፋስ እና ከከርሰ ምድር ሙቀት ያልተጠቀመችው ከ150 ጊጋ ዋት በላይ የታዳሽ ኃይል እቅም ሀብት አላት። ከእዚህ ውስጥ ስድስት ነጥብ አራት ጊጋ ዋቱን ብቻ ጥቅም ላይ አውላለች።
ሀገሪቱ በዘርፉ ካላት ሀብት አምስት በመቶ እንኳ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ገልጸው፤ ታዳሽ ኃይልን አሟጦ ለመጠቀም የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ላይ ማሻሻያ ማድረግ ወሳኝ ነው። በእዚህም 65 በመቶ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
ቀሪውን ደግሞ ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ከዜጎች የአኗኗር ዘይቤ አንጻር ከዋና የኤሌክትሪክ መስመር ተጠቃሚ ማድረግ ስለማይቻል ከፀሐይ ኃይል፣ ከንፋስና በተገኘው አማራጭ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ሽፋንን 54 በመቶ ማድረስ መቻሉን ያስታወቁት ኢንጅነር ሱልጣን፤
ብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራምን ተግባራዊ ለማድረግ በትንሹ ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግም አስታውቀዋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም