የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ሕገወጥ ተግባራትን ለማስቀረት ማስቻሉ ተገለጸ

-በኤሌክትሮኒክስ የግዢ ሥርዓት ከ246 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተፈጸመ

አዲስ አበባ፡– የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ሕገወጥነትን ለመከላከል፣ ማጭበርበርን ለመቀነስ እና ሕገወጥ ድርድሮችን ለማስቀረት ትልቅ ሚና እያበረከተ መሆኑን የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ መሠረት መስቀሌ ባለስልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም እና በ2018 እቅድ ዙሪያ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ሲያደርግ እንደገለጹት፤ 169 የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች እና 93 ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ወደ ኤሌክትሮኒክስ የግዥ ሥርዓት ገብተዋል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ሥርዓት ሕገወጥነትን ለመከላከል፣ ማጭበርበርን ለመቀነስ እናሕገወጥ ድርድሮችን ለማስቀረት ትልቅ ሚና እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች 585 ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው ግዥዎችን በኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ለማከናወን እቅድ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ246 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተፈጽሟል፡፡ ቀሪው ደግሞ በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህ ሁሉ ግብይት ከዚህ ቀደም በነበረው ሥርዓት ቢካሄድ ለተለያዩ ሕገወጥነቶች የመጋለጥ እድሉ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፤ ያጋጠሙ ችሮችን ለመለየትም ብዙ ፍተሻና ብርበራ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ ላይ ግን ሁሉንም ሂደቶች በቀላሉ ማየት ያስችላል፡፡ ተመልሶ ማጣራት የሚፈለግ ጉዳይ ቢኖርም ሁሉንም መረጃዎች መዝግቦ ስለሚያስቀምጥ በቀላሉ በመፈተሽ ተጠያቂነትን ለማስፈን አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ 6 ሺህ 500 ድርጅቶች ዲጂታል ሥርዓቱ ውስጥ መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ በጥቅሉ የተመዘገቡ ድርጅቶችም ከ26 ሺህ በላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለስልጣኑ የአሠራር ሥርዓቱን ከተለያዩ ተቋማት ጋር የማስተሳሰርና ሕጋዊ አሠራርን የማስፈን ሥራዎች ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር ሥርዓትን ለማዘመን የሚያስችል አዋጅ ጸድቆ ወደ ሥራ ገብቷል ነው ያሉት። አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችሉ መመሪያዎችን በማስጸደቅ ወደ ሥራ የማስገባት ተግባራት መከናወናቸውንም አብራርተዋል፡፡

በቀጣይነትም ተቋማት ሥርዓቱን አሟልተው እንዲተገብሩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት፣ የተዘረጉ የአገልግሎት መስጫ ሥርዓቶች ውጤታማ እንዲሆኑ መከታተል ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ አመልክተው፤ ከደንበኞች የሚመጡ ጥቆማዎችን የማጣራትና መፍትሔ የመስጠት ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡ ክልሎች ወደዚህ ሥርዓት እንዲገቡም ይሠራል ብለዋል፡፡

በ2018 በጀት ዓመት በዓለም ባንክም ሆነ በሌሎች አካላት ድጋፎች የሚከናወኑ ግዥዎች በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ብቻ እንደሚከናወኑም ዋና ዳይሬክተሯ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You