
አዲስ አበባ፡- ሲመች ሲመች በሰላም፤ ሳይመች ሲቀር በኃይል፤ እታገላለሁ ማለት ትክክል አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ ዴሞክራሲ የሚከበረው ሕግን ሲያከብሩ እንጂ ሕግን ጥሶ ዴሞክራሲ እንዲከበር መጠየቅ እና ሲመች በሰላም፤ ሳይመች ሲቀር በኃይል፤ እታገላለሁ ማለት ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል።
በከፊል ፖለቲካኛ -በከፊል አሸባሪ ፤ በከፊል ጋዜጠኛ – በከፊል አሸባሪ ፤ በከፊል ብልፅግና – በከፊል አሸባሪ መሆንም እንደማይቻልም ገልጸው፤ ሕጋዊነት እና ሕገ ወጥነት የሚቀላቀልበት ልክ በጣም ሰፊ ነው።ሁለት መልክ ከመያዝ ይልቅ አንዱን መምረጥ ይሻላል ነው ያሉት።
‹‹ከስጋው እጾማለሁ፤ ከመረቁ አድርጉልኝ›› የሚለውን ሀገራዊ ብሂል ለማሳያነት ጠቅሰው፤ የሚጾም ሰው ከስጋውም ከመረቁም ይጾማል እንጂ ስጋ ስጋውን እጾማለሁ መረቅ መረቁን አድርጉልኝ ማለቱ ትክክለኛ አባባል እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ አንጻር ፓርቲያቸው ራሱን እንደሚፈትሽ ጠቁመው፤ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም ውስጣችሁን ፈትሹ ብለዋል።
በመንግሥት በኩል የፖለቲካ ምህዳርን ከማስፋት አንጻር ሁለት መሠረታዊ እሳቤዎች እንዳሉ በመግለጽ፤ አንደኛው ፉክክር ሲሆን ሁለተኛው ትብብር ነው ሲሉ ተናግረዋል። ፉክክር ብቻውን ሲሆን ወደ ግጭት እና ወደ ጸብ የሚያመራና የማያግባባ ስለሚሆን መተባበር በሚገባን እየተባበርን ልንፎካከርባቸው በሚገቡ ጉዳዮችም እንፎካከራለን ሲሉ ተናግረዋል።
የብልፅግና እሳቤ በፉክክርና በትብብር መካከል ሚዛን መጠበቅ በመሆኑ አሁን ባለው አስተዳደር ከተፎካካሪ ፓርቲዎች 273 ሰዎች በተለያየ ደረጃ በአመራርነት ላይ እንዲቀመጡ ተደርጓል ብለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ አራት ሚኒስትሮች፣ አራት ገደማ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የቢሮ ኃላፊዎች እና በዞንና በወረዳ ደረጃ የተካተቱ በርካታ ሰዎች ስለመኖራቸው አመላክተዋል።
ይህም መንግሥት ለትብብር ቦታ እንዳለው ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚፈለጉ ሰዎችን እያካተቱ የተሻለች ኢትዮጵያን ከመፍጠር አኳያ የተጠቀሰው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ አንድ ታላቅ ሀገር ሆና እንደትቀጥል በመንግሥት በኩልም በተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩልም በተወሰነ ደረጃ የመተው ልምምድ ማድረግ እንደሚስፈልግም ገልጸዋል።
በዚህ ሃሳብ መነሻነትም እነዚህ አካላት የካቢኔ አባል ሆነው፤ በብዙ ጉዳዮች ላይ እየተቃረኑ ፣ እየተከራከሩ እና እየጠየቁ ላለፉት አራት ዓመታት አብሮ መሥራት እንደተቻለ ጠቅሰዋል። በጉዳዮች ላይ አለመግባባት ቢኖርም እየተጨቃጨቁም ቢሆን ኢትዮጵያን አብሮ መገንባት የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ኃይል የመጠቀም ብቸኛ ሥልጣን የተሠጠው ለተመረጠው መንግሥት በመሆኑ እርሱን አምኖ በኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት እምብዛም መለያየት ሳይኖር በትብብር መሥራት እንደሚቻልም አረጋግጠዋል።
‹‹አሁን ኃይል መጠቀም የተፈቀደው ሀገር ለሚያስተዳድረው ፓርቲ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፤ ነገ ደግሞ ስታሸንፉ የእናንተ ይሆናል፤ ያ ካልሆነ በቀር ሁላችንም እኩል በኃይል ርምጃ ለመውሰድ እየሞከርን የምናስበውን ዴሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ልናመጣ አንችልም›› ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ከዴሞክራሲ ልምምድ ችግር የተነሳ በየቦታው ውስንነቶች እንደሚኖሩ ጠቁመው፤ ለውጡን እያየን የጎደለውን እየሞላን ብንሄድ የተሻለ ሀገር ለመፍጠር ያግዛል ነው ያሉት።
ቀደም ሲል በነበረን ውይይት በዞን እና በወረዳ ደረጃ ችግር እየገጠማችሁ እንደሆነ ባነሳችሁት መሠረት ከሁሉም ክልሎች ጋር በመነጋገር ሁሉም ዞኖች እንዲያነጋግሯችሁ ተደርጎ ከሰላሳ በላይ ጉዳዮች መቀረፋቸውን ገልጸዋል።
እንዲሁም እስከ ዞን ድረስ ባለው መዋቅር የሚገጥሟችሁን ችግሮች ለመፍታት ምርጫ ቦርድ የመንግሥትን ተሳትፎ ሲጠይቅ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን እየመደበ እንዲጣራ እያደረገ ያለው ጉዳዩ እንዳይታፈን ስለምንፈልግ ጭምር ነውም ሲሉም ተናግረዋል።
በጎደለው ደግሞ እንዲህ ስንገናኝ ግብዓት እየወሰድን እያረምን ለመሄድ ነው ያለው ፍላጎት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደፓርቲ ውስጣችንንም በየጊዜው እየገመገምን እያረምን የምንሄደው ለዚሁ ነው ብለዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም