
–ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የቀድሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ አወንታዊ መልስ እስኪያገኝ የሚዘጋ ፋይል ስላልሆነ የተጀመረው ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ የባሕር በር ጥያቄ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የቀድሞ የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ገለፁ።
ወይዘሮ ኬሪያ ለወጋሕታ ጋዜጣ እንደገለፁት፣ የባሕር በር ጥያቄው ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛትና የኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር ያለ የባሕር በር መኖር ስለማትችል ጥያቄዋ አወንታዊ መልስ እስከሚያገኝ ድረስ የሚዘጋ ፋይል አይደለም።
የባሕር በር ጥያቄ አወንታዊ መልስ ሳያገኝ የሚቀለበስ ወይም ሊዘጋ የሚችል ፋይል አይደለም ሲባል ጥያቄው አሁን ባይመለስም የቀጣዩ ትውልድ የቤት ሥራ የሚሆን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ላይ ጥያቄ ማንሳትዋ ፍትሃዊ፣ ሕጋዊ እና ትክክለኛ መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ኬሪያ፤ ይህ ጥያቄ መዘግየቱ ካልሆነ በስተቀር በአሁኑ ጊዜ እንደ ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ፣ ፍትሃዊ እና መብት ነው፤ ስለዚህ ፍትሃዊ መልስ እስከሚያገኝ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበት ሁሉንም ሰላማዊ መንገዶች መጠቀም አለባት፤ ምክንያቱም ከጂኦግራፊ፣ ታሪክ፣ ኢኮኖሚ እና ከሌሎች ጉዳዮች አንፃር የባሕር በር የማግኘት መብት አላት፤ ከእዚህ መነሻነት ጉዳዩን በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጠናከረ ጥረት ያስፈልጋታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ዲፕሎማሲያዊ ትግሏን ማጠናከር አለባት ማለት ዲፕሎማሲያዊ ትግል ከሃይል አማራጭ የተሻለ እና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ነው ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፣ የተጀመረውም ዲፕሎማሲያዊ ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
እንደ ወይዘሮ ኬሪያ ገለጻ፣ በቀጣናው ያለው መሠረታዊ ልዩነት ከባሕር በር ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው፤ ይህ ማለት ከተፈጥሮ ሀብት ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር የተገናኘ ነው፤ አንዳንዶቹ ሀገራት ትንሽ የሕዝብ ቁጥር ይዘው ትልቅ የባሕር በር አላቸው፤ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ የባሕር በር የላትም፤ ይህ ደሞ በጣም ጎጂ ነው፤ ይህ ጥያቄ ከተመለሰ ከኢትዮጵያም አልፎ ለአካባቢው ጭምር የሚጠቅም በመሆኑ አወንታዊ ምላሽ ሊያገኝ ይገባልም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት በአጋጣሚ ሳይሆን በታሪካዊ ስህተት ነው ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥያቄው ተገቢ ስለሆነ ከቀጣናው ሀገሮች ጋር አለመግባባት ሊኖር አይገባም ብለዋል።
ይህንን ጥያቄ ተከትሎ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት አለመግባባት ውስጥ ሊገቡ አይገባም ሲባል ጥያቄው ፍትሃዊ እና ተገቢ ከመሆን በተጨማሪ ለአካባቢው የጋራ ሰላምና ልማት ወሳኝ በመሆኑ በአዎንታ መቀበል ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።
በቀጣናው የጋራ እድገትና ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት አለባት ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከተመለሰ ለራሷ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የተረጋጋ ኢኮኖሚ፣ ሰላምና ደህንነት እንዲሰፍን አጋዥ ነው ብለዋል።
ማንንም ሳይጎዳ በቀጣናው ሀገራት ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን ከመፍጠሩ በተጨማሪ በእነዚህ ሀገሮች መካከል ሰላም እና ወንድማማችነት እንዲጠናከር ያደርጋል። በመሆኑም የባሕር በር ባለቤትነት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሀገራትንም ጭምር ተጠቃሚ ስለሚያደርግ አወንታዊ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።
በመኣርግ ገ/እግዚኣብሄር
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም