1860 ዓ.ም መቅደላ፤ … ከንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ጋር ግጭት ውስጥ የገባው የእንግሊዝ መንግሥት ንጉሰ ነገሥቱ እስር ቤት ያስገቧቸውን ዜጎቹን ለማስለቀቅ በጀኔራል ሮበርት ናፒየር የሚመራ ጦር ልኮ መቅደላ ላይ የተደረገው ጦርነት ንጉሰ ነገሥቱ ራሳቸውን እንዲያጠፉና መቅደላና አካባቢውም እንዲዘረፍ ምክንያት ሆነ። በዚህ አሳዛኝ ትዕይንት ፍፃሜ ላይ የእንግሊዝ ወታደሮች አንድ ሕፃን ልጅ አንድ ቤት ውስጥ ብቻውን ሆኖ አገኙት። የእንግሊዝ ወታደሮችም ሕፃኑን ባገኙት ጊዜ አዝነው ወደ ጦሩ አለቃ ወስደው አስረከቡት። ያ ሕፃን በኋላ ዘመናዊውን የሕክምና ትምህርት የተማረ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ለመሆን የበቃው ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ነበር።
ወርቅነህ እሸቴ የተወለደው በ1857 ዓ.ም ጎንደር አካባቢ ነው። ከመቅደላው ትዕይንት በኋላ የእንግሊዝ ወታደሮች ወደ አገራቸው ሲመለሱ የንጉሰ ነገሥቱን ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤንና የንጉሰ ነገሥቱን ልጅ ልዑል ዓለማየሁን ጨምሮ ወርቅነህ እሸቴንም ይዘው ወደ እንግሊዝ ለመሄድ ጉዞ ጀመሩ። ይሁን እንጂ ምፅዋ ወደብ ላይ ሲደርሱ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስና ወርቅነህ እሸቴ ሊለያዩ ግድ ሆነ።
ጀኔራል ናፒየር የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስን ባለቤትና ልጅ ወደ እንግሊዝ ይዞ እንዲመለስ ከእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ በደረሰው ትዕዛዝ መሰረት እቴጌ ጥሩወርቅንና ልዑል ዓለማየሁን ወደ እንግሊዝ ለመውሰድ እየተጓዙ ሳለ እቴጌዋ ታመው ሕይወታቸው አለፈ። ስለሆነም ልዑሉ ወደ እንግሊዝ ሲያቀና፤ወርቅነህ ደግሞ ኮሎኔል ቻርለስ ቻምበርሌይን ከተባሉ የጦር መኮንን ጋር በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወደነበረችው ወደ ሕንድ ሄደ።
ሕፃኑ ወርቅነህ ሕንድ ውስጥ አራት ዓመታት ያህል እንደቆየ አሳዳጊው ኮሎኔል ቻርለስ ቻምበርሌይ ኮሎኔል ማርቲን ለተባሉ ሌላ የጦር መኮንን አስረክበው ትምህርት ቤት ገብቶ ትምህርቱን እንዲቀጥል ተደረገ። ብሩህ አእምሮ የነበረው ወርቅነህ፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ፑንጃብ በምትባለው ከተማ ተከታትሎ ሲጨርስ ለዩኒቨርሲቲ የሚያበቃ ውጤት ስለነበረው በፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ለማጥናት ተመዘገበ።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ጎበዝ ተማሪ እንደነበር የሚነገርለት ይህ ሰው፣ የውስጥ ደዌና የቀዶ ጥገና ሕክምና ትምህርቱን በሚገባ አጠናቅቆ ከተመረቀ በኋላ እዚያው ሕንድ ውስጥ ሐኪም በመሆን ለሁለት ዓመታት ያህል አገለገለ። በሕንድ የሁለት ዓመት የቀዶ ጥገና ሕክምና አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ከፍተኛ የህክምና ትምህርት ለመከታታል እ.ኤ.አ በ1889 ዓ.ም ወደ እንግሊዝ አቀና። በዚያም በኤደንብራና በግላስኮው ዩኒቨርሲቲዎች በቀዶ ጥገና ሕክምና ሙያ በማዕረግ ተመረቀ። በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት ከሐኪሞች ማኅበር ‹‹የበቃ ጥቁር ሐኪም›› የሚል ሽልማት ተበረከተለት።
ይሁን እንጂ ሐኪም ወርቅነህ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በሆኑ አገራት ቢያድግና ቢማርም፤ የእንግሊዛውያንን ቋንቋ ቢናገርም እንግሊዛዊ ባለመሆኑ ለስራ መግቢያ የሚሰጠው ፈተና እርሱን ስለማይመለከት ፈተናውን እንዳይወስድ ተከለከለ። በሰማው ነገር ግራ ቢጋባም ዝምታን ባለመምረጥ ለንደን ለሚገኙ ወዳጆቹ፣ ለእንግሊዝ ባለስልጣናትና ለንግሥት ቪክቶሪያ ጭምር አቤቱታውን አቀረበ። ግን ማንም ሊረዳው አልቻለም።
ሌሎች መንገዶችን ቢሞክርም አልተሳካለትም። በዚህ መሰናክል ምክንያት እንግሊዝ ውስጥ በሙያው መስራት ባለመቻሉ ወደ ሕንድ ለመመለስ ተገደደ። ሕንድ ውስጥ ለመስራት ያቀረበው ጥያቄ ‹‹በሕክምና ዘርፍ የተሰማሩት እንግሊዛውያን በመሆናቸው እንግሊዛውያን ያልሆኑ ሰዎች በዘርፉ መሰማራት አይችሉም›› ተብሎ ጥያቄው ተቀባይነት ባለማግኘቱ በሕንድ ቅኝ ግዛት ስር ትተዳደር ወደነበረችው ወደ በርማ (ምያንማር) መሄድ እንደሚችል ተነገረው።
በርማ እንደደረሰም በርካታ ባለሙያዎች በሽታን ሸሽተው በርማን መልቀቃቸውን ሰማ። ስራው ለሕይወቱ አስጊ ቢሆንም መመለስን አልመረጠም ነበር። ለጥቂት ቀናት ያህል አብሮ እንደሰራም ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጠው። ኃላፊነቱም የማዘጋጃ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ነበር። ገና በወጣትነቱ መሰል ኃላፊነትን ማግኘቱ ቢያስደስተውም በዘርፉ ልምድ ስለሌለው ፈራ ተባ እያለ መስራት ቀጠለ። በበርማ ቆይታውም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተንቀሳቀሰ አገልግሏል።
ሐኪም ወርቅነህ በርማ ውስጥ በሕክምና ስራ ላይ ሳለ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛቷ ለማድረግ አልማ የተነሳችበት የዓድዋ ጦርነት ተከሰተ። ሐኪም ወርቅነህም ስለጉዳዩ ሲሰማ ‹‹ሀገሬን መርዳት አለብኝ›› ብሎ የሕክምና እቃዎችን ይዞ ወደ አገሩ ለመምጣት ያደረው ጥረት ሳይሳካለት ቢቀርም ስለአገሩ ማሰቡን አላቆመም ነበር።
ከበርማ የመጡ እንግዶች ‹‹ … ገና በወጣትነቱ ኃላፊነት የተሸከመና ገና በአፍላነቱ በሕክምና ሙያ የታወቀ የሀገርዎ ሰው እኛ ዘንድ አለ …›› ብለው ለንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ነገሯቸው። ንጉሰ ነገሥቱም ተደስተው ወጣቱ የሕክምና ባለሙያ በቶሎ ወደኢትዮጵያ እንዲመጣ ሀሪንግተን ለተባሉት እንግሊዛዊ ነገሯቸው። ሀሪንግተንም የንጉሰ ነገሥቱን መልዕክት ለሐኪም ወርቅነህ አስተላለፉ፤እንግሊዝ ተገናኝተው ለመመለስም ጉዞውን አመቻቹ።
ሐኪም ወርቅነህ በሕፃንነቱ የተለያትን አገሩንና ወገኑን ለማየት ከረጅምና አድካሚ ጉዞ በኋላ በታኅሳስ ወር መጨረሻ 1892 ዓ.ም አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ ቤተ-መንግሥት ደረሰ። ስሙን ሲያስተዋውቅም አሳዳጊዎቹ ባወጡለት ስም ‹‹ቻርለስ ማርቲን›› ብሎ ነበር።
ወደአገሩ ከተመለሰ በኋላም በሕይወት ካሉት ዘመዶቹ ጋር ተዋወቀ። አገሩንና ወገኑን ለማገልገል ሁለት ነገሮችን ፈለገ። አንደኛው የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥበት ስፍራ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አስተርጓሚ ነበር። ሁለቱንም አገኘ። አዲስ አበባ መሐል ከተማ ላይ ድንኳን ጣለ፤ከአስተርጓሚውም ጋር ተዋወቀ። ታመው በየቤቱ ይሰቃዩ የነበሩና ሕክምና አጥተው የሚንከራተቱ ሁሉ ወደ ሐኪም ወርቅነህ ዘንድ እየቀረቡ ነፃ የሕክምና አገልግሎት አገኙ። ወደሐኪሙ ዘንድ ከመጡት ታማሚዎች መካከል ብዙዎቹ ፈውስ በማግኘታቸውና በማገገማቸው የሐኪም ወርቅነህ ልፋት ፍሬ ማፍራት ጀመረ።
ሐኪም ወርቅነህ በ1860 ዓ.ም የተለዩትን የቅርብ ቤተሰቡን ያገኘውም አዲስ አበባ መጥቶ በሕክምና ስራ ተሰማርቶ እያገለገለ ባለበት ወቅት ነበር። ከእለታት አንድ ቀን ሐኪም ወርቅነህ በህክምና ስራው ላይ ሳለ ወደ ድንኳኑ ከሚገቡትና ከሚወጡት ሰዎች መካከል አንዲት በእድሜ የገፉ ሴት ሐኪም ወርቅነህን በጥርጣሬ እየተመላለሱ ይመለከቱታል። ሐኪም ወርቅነህም አስተርጓሚውን ጠርቶ ስለሴትየዋ ጠየቃቸው። ሴትየዋም ሲጠየቁ ‹‹ … የጠፋውን የልጅ ልጄን መስሎኝ ነው። እርግጠኛ ለመሆን እጅና እግሩን ማየት አለብኝ …›› አሉ። ሐኪም ወርቅነህም የሰውነቱን ክፍል ለማሳየት ፈቃደኛ ሆነ።
‹‹ ሰውነቴን ገልጬ ከማሳየቴ በፊት ምን ምልክት እንዳለ ንገሩኝ …›› አለ። ሴትየዋም የልጃቸው ልጅ በሦስት ዓመቱ ከመቅደላ መወሰዱንና ከኢትዮጵያ ውጪ መቆየቱን እንደሚያውቁ፣ ሐኪም ወርቅነህም ወደውጭ የሄደው በዚያው ዘመን እንደሆነ መስማታቸውና በልጃቸው ልጅ የግራ ክንድ በፊት በኩል ረጅም ጠባሳ እና በቀኝ ቅልጥሙ ላይ ደግሞ የሽታ ምልክት እንዳለው ተናገሩ። ሐኪም ወርቅነህም እጅና እግሩን ሲያሳይ ሴትየዋ እንደተናገሩት ምልክቶቹ ተገኙ። ስሙ ወርቅነህ፣ የአባቱ ስም እሸቱ፣ የእናቱ ስም ደግሞ ደስታ እንደሆነ ተነገረው። አያቱም ደስታቸውን ለሌሎች በማዳረሳቸው ዘመድ ነን ያሉ ሁሉ ከሐኪም ወርቅነህ ጋር ተዋወቁ።
ሐኪም ወርቅነህ ስራውን እያከናወነ ሳለ ‹‹ሰላይ ነው›› የሚል ወሬ ተወርቶ ወሬውም ቤተ-መንግሥት ደረሰ። በዚህ ሁሉ ችግር መሐል ከሐኪም ወርነቅህ ጎን የሆኑት ራስ መኮንን ነበሩ። ራስ መኮንን ከሐረር ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሐኪም ወርቅነህን ሊያፅናኑ ሞከሩ። ወደ ሐረር ሄዶ በሙያቸው እንዲሰራም አግባቡ። ሐኪም ወርቅነህ ግን ወደ በርማ መመለስ በመፈለጉ ንጉሰ ነገሥት የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ፈቃድ ጠየቀ። ከንጉሰ ነገሥቱ ፈቃድ እስከሚያገኝ ድረስም የሕክምና ስራውን እያከናወነ ቆየ።
ሐኪም ወርቅነህ ወደ በርማ ተመልሶም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተዘዋወረ ሰራ። በአንድ የበርማ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታልም ሜዲካል ዳይሬክተር ሆኖ ተሾሞ ነበር። በዚህ ወቅትም ከአንዲት እንግሊዛዊት ጋር ተዋውቆ ጋብቻ መሰረተ፤ወንድ ልጅም አገኙ። ልጃቸውንም ቴዎድሮስ ብለው ስም አወጡለት። ከአንድ ዓመት የበርማ ቆይታቸው በኋላም (እንግሊዛዊት ባለቤታቸውን ሳያስከትሉ) በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ። ከእንግሊዝ ለጋሲዮን ሃኪምነታቸው በተጨማሪ የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐኪም ሆነው ማገልገልም ፈለጉ። በወቅቱ ንጉሰ ነገሥቱን ሲያክሙ የነበሩት የውጭ አገር ሐኪሞች በእቴጌ ጣይቱ ዘንድ ተወዳጅ ስላልነበሩ ሐኪም ወርቅነህ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ። በነሐሴ ወር 1901 ዓ.ም ወደ ቤተ-መንግሥት ገብተው የንጉሰ ነገሥቱን ጤንነት መከታል ጀመሩ።
በዚህ ጊዜ ከሐኪም ወርቅነህ ጋር ይቀራረቡ የነበሩ መኳንንቶች ሐኪሙ ትዳር እንዲመሰርቱ ስለመከሯቸው የፊታውራሪ ጂማ ቱሉ ልጅ የሆኑትን ወይዘሮ ቀጸላወርቅ ቱሉን አገቡ። ትዳራቸውም ሰምሮ ስድስት ወንድ ልጆችና ሰባት ሴት ልጆችን አፈሩ።
የንጉሰ ነገሥቱ በፅኑ መታመምና የሕዝቡ ጭንቀት፣ ለስልጣን የሚደረገው ሽኩቻ፣ ከውጭ አገራት በመጡ ሐኪሞች መካከል ያለው አለመግባባትና ሐኪም ወርቅነህን ለማራቅ የሚሸረበው ሴራ ቤተ-መንግሥቱን እንዳይረጋጋ አደረጉት። በመጨረሻ ግን የንጉሰ ነገሥቱ ብቸኛ ሐኪም የመሆን እድል ያገኙት ሐኪም ወርቅነህ ነበሩ።
ይሁን እንጂ አሁንም ሙያዊ ተግባራቸውን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ አላገኙም። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የሚመገቡት እንቁላል፣ ወተትና አትክልት ብቻ እንዲሆን ሐኪም ወርቅነህ ትዕዛዝ ቢሰጡም እቴጌዋ ግን ‹‹ … አንተ እንደምትለው እንደፈረንጅ ሳይሆን እንደኛው ይመገባሉ … ›› ብለው ትዕዛዛቸውን ሻሩባቸው። ሐኪም ወርቅነህ ወደ ንጉሰ ነገስቱ ዘንድ ሄደው ሲያዩዋቸው ደም ብዛታቸው ከፍ ብሎ አገኙት። ንጉሰ ነገስቱ በርበሬ የበዛበት ወጥ መብላታቸውንና ጠንካራ ጠጅ መጠጣታቸውን ሲያውቁ አዘኑ። ሐኪም ወርቅነህ የሕክምናው ሕግ የሚያዝዘውን እንዲፈፀም ደጋግመው ቢያሳውቁም ሰሚ አላገኙም፤የንጉሰ ነገሥቱም ሕመም እየባሰ ሄደ። በመጨረሻም ከሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ ቆይታ በኋላ ወደ በርማ ተመለሱ።
በርማ ቆይተውም ጡረታ ወጥተው ወደ ኢትዮጵያ መጡ። እርሳቸው ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅትም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አርፈው ልጃቸው ዘውዲቱ ምኒልክ ነግሰው፤ራስ ተፈሪ መኮንን አልጋ ወራሽ ሆነው ነበር። የቤተ-ሳይዳ ሆስፒታል (የአሁኑ የካቲት 12 ሆስፒታል) አስተዳዳሪ ሆነውም ተሾሙ። ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሹም ሆኑ። የፍል ውሃ ድርጅትን በአዲስ መልክ እንዲያደራጁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው አከናውነዋል።
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ከንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር በመሆን እንግሊዝ ውስጥ ቆይተዋል። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ከተባረረ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበው አገልግለዋል። የጨርጨር አውራጃ ገዢ ሆነው ተሹመው የጭሮ (የቀድሞዋ አሰበ ተፈሪ) ከተማን በዘመናዊ ስርዓት አደራጁ። ከጨርጨር አውራጃ ገዢነታቸው ተጠርተው በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኑ። በጣና ሐይቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለመስራት ከአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር ለመነጋገር ወደ አሜሪካ በሄዱበት ወቅት ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ መቆየት እንደቻለች ለአፍሪካ-አሜሪካውያን (African-Americans) ገለፃ አድርገውላቸዋል።
ሐኪም ወርቅነህ ከሕክምና ሙያቸው በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ‹‹የዓለም ጂኦግራፊ›› መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ ጽፈዋል። በወቅቱ በውጭ አገራት ተምረው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን በውጭ ያዩትንና ለሀገር ይጠቅማል ብለው ያሰቡትን ሙያ በማስተዋወቅ ጽፈው ሌሎች እንዲያነቡት ለማድረግ ጥረዋል። ሐኪም ወርቅነህም ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የጂኦግራፊ ትምህርትና መጽሐፍ አለመኖሩን ሲያውቁ ‹‹ …የጂኦግራፊ ትምህርትና መጽሐፍ ከሌለ ስለሌላው አገር ስፋት፣ ሀብትና አቅም እንዴት ማወቅ ይቻላል…? ›› ብለው በማሰብ ጊዜ ወስደው የአማርኛ ቋንቋን በመማር በቋንቋው በ1904 ዓ.ም ‹‹የዓለም ጂኦግራፊ›› መጽሐፍን ጽፈዋል። የባሪያ ስርዓትን በግልፅ በመቃወማቸውም ከአንዳንድ ባላባቶች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው ነበር።
በሕክምና ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ባልበዙበት፣ የመታከሚያ ስፍራዎች ባልተስፋፉበትና መድኃኒቶች እንደልብ በማይገኙበት አገር በሙያቸው አገራቸውን ለማገዝና ወገናቸውን ለማገልገል ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፣ በሕክምናና በመንግሥታዊ አስተዳደር ዘርፍ ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱት … ዘመናዊ ሕክምና በኢትዮጵያ እንዲለመድ ያደረጉት ሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ጥቅምት 11 ቀን 1945 ዓ.ም አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው በየካ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን ተፈጽሟል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24/2011
አንተነህ ቸሬ