ትንፋሽ የማይሰጠው የባሕር በር ጥያቄ

ዜና ሀተታ

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እያደገ ነው። የዓለም የንግድ እንቅስቃሴ እየተለዋወጠና ስጋት እየተደቀነበት ነው። የሰላም፣ የደህንነትና የተሰሚነት ጉዳዮችም ከባሕር በር ጋር እየተሳሰሩ ነው። ከዚህ መነሻነት የባሕር በር ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን አማራጭ የሌለው የህልውና ጥያቄ ነው የሚሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎች እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ወርቅነሽ ጀማል፤ ዓለም አቀፍ ሕግጋቶች እንደሚያስቀምጡት፤ ኢትዮጵያ እንደማንኛውም በዓለም ላይ እንዳሉ ሀገራቶች በአቅራቢያዋ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች በጋራ የመጠቀም መብት እንዳላት ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የባሕር በር ቢኖራትም፤ በታሪክ አጋጣሚ በተከሰቱ ስህተቶች ምክንያት የባሕር በር አጥታለች። በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባሕር በር ልታገኝ የምትችልበት ዓለም አቀፍ አሠራሮች ስላሉ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ በትኩረት መሥራት ከሁሉም ዜጋ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በሰላማዊና በፍትሃዊነት መንገድ የባሕር በር ተጠቃሚ ልሁን የሚል ጥያቄ ማንሳቷ ወቅታዊና ተገቢ ነው የሚል ሃሳብ እንዳላቸው አመልክተው፤ በሰጥቶ መቀበል መርህና በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ተጠቃሚ ለመሆን መሥራት እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ ወርቅነሽ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ብዙ ዕቃዎችንና ሸቀጦችን ከውጭ ሀገራት የምታስገባና በርካታ ሕዝብ ካሏቸው ሀገራት አንዷ እንደመሆኗ የባሕር በር ጥያቄ አንገብጋቢ ጉዳይዋ ነው።

ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ የሚመነደገው፣ ደህንነቷ የሚረጋገጠው፤ ተሰሚነቷ የሚጨምረውና ሁለተናዊ ብልፅግናዋ የሚረጋገጠው ከሌሎች ሀገራት ጋር በንግድ፣ በልማትና በኢንቨስትመንት በትብብር ስትሠራ ነው። በተለይ በባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መተባበር ቀዳሚው ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ።

“የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን የሚያተኩረው በቅድሚያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ መሥራት ላይ ነው” ያሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ ፤ በጋራ በመሆን አካባቢውን ማልማት ከተቻለ ጠንካራ ምሥራቅ አፍሪካ፤ አለፍ ሲልም ጠንካራ አህጉር መፍጠር እንደሚቻል ይጠቁማሉ።

ወይዘሮ ወርቅነሽ እንደሚገልጹት፤ የባሕር በር የሸቀጥ ንግድ ከማሳለጥ፤ የባሕር ኃይል ከማደራጀት፤ ቴክኖሎጂዎችንም ከማምጣት፤ የሥራ እድል ከመፍጠር እና ከሌሎች በርካታ ነገሮች አንጻር ለኢትዮጵያ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።

ኢትዮጵያ በሰላማዊ አማራጭ የባሕር በር ማግኘት አለብኝ የሚል አቋም ይዛ እየሠራች መሆኑ የሚደገፍ እንቅስቃሴ ነው። ከዚህ ቀደም የባሕር በር ጥያቄ ማንሳት እንደነውር የሚታይበት ጊዜ ነበር የሚሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ ፤ ነገር ግን የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባታል ብሎ ጥያቄውን አንስቷል። ጥያቄው ለቀጣዩ ትውልድ የሚጠቅም እና አንዱ የታሪካችን አካል እንደሆነ ነው የገለጹት፡

ትውልዱ ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ የትም ቦታ ሲሄድ ለሀገሩ አምባሳደር ሆኖ የባሕር በር ለኢትዮጵያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ማስረዳት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

እያደገ ከመጣው የሕዝብ ቁጥራችን አንጻር የባሕር በር በፍትሃዊ መንገድ ማግኘት እንደ ሀገርም፤ እንደ ሕዝብም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው የሚሉት ደግሞ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎች እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ቆጭቶ ገብረኢየሱስ፤ ኢትዮጵያ የምታመርተውን ምርት ወደ ሌሎች ሀገራት ትልካለች፤ በምላሹ ደግሞ ከሌሎች ሀገራት ምርቶችን ወደ ሀገር ታስገባለች። ይህን የንግድ ልውውጥ የተሳለጠ ለማድረግ፤ ሕዝቡ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ እንዲሄድ የባሕር በር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ይላሉ።

“የባሕር በር ኢትዮጵያ በነበራት ጊዜ ሕዝቦችን በጣም ሲጠቅም የነበረ ቢሆንም፤ በአጋጣሚ የነበረንን የባሕር በር ልናጣ ችለናል”። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው ሕዝቦች ባልተነጋገሩበት ሁኔታ እንደሆነም አውስተው፤ ከዚህ ቀደም ያጣነውን የባሕር በር በሰጥቶ መቀበል መርህ ይሁን በሌላ መንገድ ከተገኘ፤ ትውልዱ የራሱን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ የሚሄድበት መልካም ዕድል መሆኑን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር ያላት ቅርበት ከ60 ኪሎ ሜትር የማይበልጥ ቢሆንም፤ ለበርካታ አስርት ዓመታት የባሕር በር ሳይኖራት ቆይታለች። አሁን ደግሞ የራሷ የሆነ የባሕር በር እንዲኖራት በሰጥቶ በመቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ እየጠየቀች ይገኛል። ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫም ፤ የኢትዮጵያን የባሕር በር የማግኘት መብት ለማስከበር ዲፕሎማሲያዊ፣ ሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገዶችን መሠረት አድርጎ የተጀመረው ሥራ በተጀመረው ግለት እንዲቀጥል የሚያስችል አቅጣጫ ተቀምጧል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You