ነገ አዲስ ቀን ነው፤ አረንጓዴው ወርቅ የሚመጣበትና ልምላሜ የሚታፈስበት ጊዜ። “ድልድዩን” ተሻግሮ “አረንጓዴው መስክ” ላይ መቦረቅን ንጹህ አየር መተንፈስን በውብ ከተማ መኖርን ማን ይጠላል ። ለዚህ ደግሞ አረንጓዴ ስፍራን መናፈቅ ብቻ ሳይሆን ለአረንጓዴው ልማት መስራት ግድ ይላል።
ሐምሌ 22 በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል በተያዘው ዕቅድ አሻራቸውን ለማሳረፍ መዘጋጀታቸውን የነገሩን ሀሌታ የአርቲስቶች ጥምረት ማህበር ፕሬዚዳንት አርቲስት መስፍን ሀይሉ ናቸው። የኪነጥበብ ባለሙያዎችም ውብና ድንቅ ስራዎቻቸውን እነሆ ሊሉን ለምለም መስክ ይሻሉና ለአረንጓዴው ልማት የአሻራ ቀን ዋነኛ ተዋናይ ሊሆኑም የችግኝ መትከያ ከአብነት አደባባይ እስከ ሜክሲኮ ያለውን ስፍራ ተረክበዋል።
ወርቅን ከአፈር ለይቶ ማውጣት ብዙ ልፋት ይጠይቃል። በእሳት መፈተንን አልፎ ዋጋውና ጌጥነቱም የዛኑ ያህል ውድ ነውና ተመራጭ ይሆናል። አረንጓዴው ወርቅም መሬት ብቻ ምሶ የሚተከል ሳይሆን ክትትልና ክብካቤን ይሻል፤ ውጤቱ ደግሞ ከሰዎች ጤና፣ ከሀገር ኢኮኖሚ ጋር ነውና ዋጋው ከምናቆለባብሰው ወርቅም ይልቃል፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አርቲስት መስፍን ብዙ ነገር ማቀዳቸውንና በነገው ዕለት የመጀመሪያ የሆነውን አገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አጫውቶናል። የአርቲስቱን የሙያ ብቃት እንዴት ለአገር ልማት ማዋል እንደሚቻል የሚያሳዩበትም እንደሆነ ነግሮናል።
ባለንበት ዘመን ዓለማችንን ስጋት ውስጥ ከከተቷት ቀውሶች አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን ማንም አይክድም። ታድያ ኢትዮጵያም የዚህ ቀውስ ሰለባ ናትና ችግሩ ሳይፈረጥም የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች። የአረንጓዴ ወርቅ ማውጣት
ተግባሯንም በክልል፣ በዞን፣ በወረዳና በቀበሌ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ እያለች የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ነው። በአገር ደረጃ ደግሞ ነገ ሁሉም ዜጋ በነቂስ ወጥቶ አሻራውን ያሳርፋል።
«ኪነጥበብ አገር ታለማለች፤ በዚያው ልክ አገር ታፈርሳለች። ስለዚህም እንደተጠቀምንባት ሁኔታ የመቀያየር አቅም አላት። በመሆኑም እንደ ማህበሩ ያንን ዋጋ ለማጉላትና ለማሳየት ብሎም ለአገር ገጽታ ግንባታ ለማዋል ይሰራል።» ሲል ማህበሩ አባላትን አዘጋጅቶ ለሀገራዊው ጥሪ ስንቅና ትጥቁን ማዘጋጀቱን ይናገራል።
እንደ አርቲስት መስፍን ገለጻ፤ አገራዊ ነገሮች ላይ መሳተፍ ግዴታ ቢሆንም በተለይ ደግሞ ችግኝ ተከላ ሲሆን የመኖርና የእስትንፋስ ጉዳይ ይታከልበታል። ለመኖር ንጹህ አየር ማግኘት ግድ ይላል። ንጹህ አየር የሚገኘው ከተፈጥሮ ብቻ ነው። ችግኝ ተከላ ላይ መሳተፍ ለኪነጥበብ ባለሙያው እንደሌላው ነዋሪ ተጠቃሚነት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ነው። ስለዚህ በህብረት የሚደረጉ ነገሮች ደግሞ ውጤታቸው ይልቃልና በዚህ ደረጃ የማህበሩ አባላት በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።
አገራችን በተለይም ከተማችን በአሁኑ ወቅት ወደ በረሃነት እየተለወጠች ነው ማለት ይቻላል። ከችግኝ ይልቅ ፎቅ የሚታይበት ቦታ ሰፍቷል። የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ተዳክመዋል ስለዚህ አረንጓዴ ልማትን የማስፋፋት በችግኝ ተከላ ላይ መሳተፍ እና እንዲጸድቅ ክትትል እና እንክብካቤ ማድረግ ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው ይህንን ስንሰራም ደስ ብሎን ነው የምናደርገው ለዚህ ደግሞ አረንጓዴ ምድርን መናፈቅ ብቻ ሳይሆን ሆኖ ማየት ለእኛ አርቲስቶች የእንጀራ ጉዳይ ያደርገዋልና እንደግለሰብም ሆነ እንደ ማህበር ችግኝ ለመትከል ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ይናገራል።
እንደ አርቲስት መስፍን ማብራሪያ፤ ችግኝ መትከል ብቻ ግብ አይደለም። መንከባከቡ ግዴታ ነው። በመሆኑም የተከሉትን ችግኝ የመንከባከብ ፕሮግራም ታቅዷል። “በ2012 ዓ.ም ትልልቅ ፌስቲቫሎችን ባዛሮችን እናዘጋጃለን፤ ይህ ደግሞ መንገድ ላይ ወይም አዳራሽ ተከራይተን እንዲሆን አንፈልግም። ተንከባክበን ያሳደግነው ቦታ ላይ እንዲታይ እንተጋለን። ይህ የሚፈጥረው ትልቅ አገራዊ ስሜትና ውበት አለው። ስለዚህ የዛሬ ሥራችን ለነገም እንዲሆን አድርገን ለመስራት ተነስተናል። እንደስማችን የመጀመሪያና ትልቁን አልመን ነው የተነሳነው” ብሏል።
አርቲስት መስፍን፤ ማህበሩ ከተቋቋመ ሰባት ወራትን አስቆጥሯል፤ ኪነጥበቡ ለአገር ልማት ምን ሰራ፣ የትስ ነው ያለው የሚለውን ለማውጣት ታስቦ የተመሰረተ መሆኑን ይናገራል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የኪነጥበብ ባለሙያው ተገቢውን ክብር ያሳጣው ምንድነው የሚለውንም ለመመርመርና መፍትሄ ለመስጠት የታሰበበት ነው። በእርግጥ ማህበሩ እስካሁን ህጋዊ እውቅና አላገኘም። ሆኖም በሂደት ላይ ይገኛል። ከዚህም 90 በመቶው ስራ መጠናቀቁን ይናገራል በቅርቡም ማህበሩ ፈቃድን በእጁ እንዲያስገባ ነው ያስታወቀው።
«ሀሌታ» ማለት የመጀመሪያ የሚለውን ትርጓሜ የሚይዝ ነው፤ የመጀመሪያና ከትልቁ ነገር የሚነሳ መሆኑን ማሳያ ማህበር ነው። በትልቅ ተነስቶ ወደ ትንሽ መውረድ አይታሰብምና ሁሌም ወደ የትላልቆች ጉዳዩች ጉዞ ያደርጋል። ለዚህ የሚያበቃ ቁጭትና እልህ የራሳቸውን ጠቃሚ ብልሀቶች ይዘው ይመጣሉና ማህበሩም ይህንን ቁጭቱን በትልቅ ድል ለመወጣት እየተጋ ይገኛል።
የኪነጥበብ ባለሙያዎች አገሪቱን በተለያየ መልኩ ማሳየት የሚችል አቅም አላቸው። አገሪቱን እንደ ባንዲራ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ለዓለም ማስተዋወቅ ይችላሉ። ሆኖም አሁን ላይ ትኩረት አድርጎ እየተሰራበት ያለው ገንዘብ ላይ ብቻ ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ታሪክና ባህል ቢኖራትም እንዳይሰራላትና እንዳይነገርላት አድርጓል። ብዙ የሰሩ ቢኖሩም ክብር አላገኙም። እናም መሰራት ያለበት እንዲሰራ፣ መከበር ያለበት እንዲከበር ማድረግ የማህበሩ ዓላማ መሆኑን ይናገራል።
ማህበራት ሲቋቋሙ አገራዊ ልማትም ሆነ ለትውልድ የሚሆን ሥራ ለመስራት ተብሎ ይገባና ከጽሁፍና ከመመሪያ የዘለለ አይሰራባቸውም። በመመሪያ ተቋቁመው በዘልማድ እንዲሰሩ እድል ይሰጣቸዋል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ታሪኳ ብዙ ነው እየተባለ ከማውራት ውጪ በተግባር እንዲታይ አልተደረገም። ይህ ችግር መፈታት ያለበት በዚህ ማህበር ነው ብለን ስለምናምን በማህበሩ ጠንካራ እቅዶችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው። ትልልቅና አገሪቱን በአንጸባራቂ ውበቷ እንድታሳይ የሚያደርግ ሥራ ይሰራልም። አሁን ከሁለት መቶ በላይ አባላት ያሉ ሲሆን፤ እነርሱም ለዚህ አላማ ግብ መምታት የበኩላቸውን ለማድረግ ራሳቸውን ዝግጁ አድርገዋል ብሏል።
ኪነጥበብ ኢትዮጵያን እንደ ስሟ ኢትዮጵያ ያደርጋታል። ለዚህ ደግሞ አንጋፋው አስተማሪ ተከታዩ ተማሪና ተግባሪ እየሆነ እንዲሰራ መታተር ግድ ነው። ምክንያቱም አሁን ላይ እየታየ ያለው ተተኪዎችን ማጎልበት ሳይሆን ማሸማቀቅ ነው። አብረዋቸው እንዲሰሩ ማበረታታትም ላይ ችግር አለ። በአወኩሽ፣ በዘመድ አዝማድ የሚሰራውና በብዛት ሥራዎችን ጠቅልሎ የመያዝ ሁኔታም ብዙ ነው። በዚህም አገር ከኪነጥበቡ እንዳትጠቀም ሆናለች። ይሄ የሚፈታው ደግሞ ይህንን አላማ አድርጎ በሚንቀሳቀሰው ማህበር አማካይነት ነው።
የኪነጥበብ ሥራ ፈተናው ብዙ ነው። ሙያተኛን እስከማግኘት ድረስ ይፈተናል። ለአብነት ተዋንያንን መርጠው የሚያቀርቡ ድርጅቶች አሉ እነዚህ ድርጅቶች ተዋንያንን ሲያቀርቡ ችግሮች ያጋጥማሉ አንዱ ለሙያተኛው የሚከፍሉት ገንዘብ አነስተኛ መሆን ነው። የተባለውን ገንዘብ ስለማያገኙ ከሙያው ይሸሻሉ። ሁለተኛው ድርጅቱ በገፍ ገንዘብ መበላቱ ነው። በዚህ መካከል እንደ ደላላ የሚያገለግሉት ብቻ ተጠቃሚ ይሆናሉ። እናም ማህበሩ እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለማስቀረት ይሰራል።
የኪነጥበብ ባለሙያው ስንፍናና ገንዘብ ወዳድነት፤ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት … ሙያው እንዳይጎላና ለአገር ግንባታ የድርሻውን እንዳይወጣ አድርጎታል የሚለው አርቲስት መስፍን፤ በተለይ ባለሙያው ታሪክን ነቅሶ ከመስራት ይልቅ ከትናንሽ ታሪክ ተነስቶ ሥራዎችን መስራትና በቀላል ገንዘብ ማካበትን እንደ ልምድ ይዞታል። በዚህም አገር ከሙያው ተጠቃሚ እንዳትሆን እድል ነፍጓል። ስለዚህ ማህበሩ ራሱን አጠናክሮ ዛሬ በአረንጓዴ ወርቅ ፍለጋው እንደተሰማራው ሁሉ ነገ ሌሎችን ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና መፍትሄ በመስጠት አገር ከሙያው ተጠቃሚ እንድትሆን ይሰራል።
የአረንጓዴ ልማቱ እንደሚያለመልመን ሁሉ ሌሎች ነገሮችም እንዲያበረቱንና ልምላሜን እንዲያጎናጽፉን ለማድረግ እንተጋለን ማሳረጊያ ሀሳቡ ነው። እኛም ያሰቡት እንዲሰምር ተመኝትን ውጤቱን በጋራ ለማየት እየናፈቅን ውይይታችንን ቋጨን ሰላም!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው