
ዜና ትንታኔ
ከትናንት በስቲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያና ምላሽ ዙሪያ የከተማዋን ነዋሪዎች አነጋግረናል፡፡ ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ኢኮኖሚን፣ የባሕር በርን፣ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካን እንዲሁም ሕዳሴው ግድብን በተመለከተ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡
አቶ ደረጀ ሲሳይ የ65 ዓመት አዛውንትና ጡረተኛ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡ ከጡረታ በፊት በመካኒክነት ሙያ ሀገሬን ሳገለግል ቆይቻለሁ የሚሉት አዛውንቱ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ምኒልክ ሆስፒታል አካባቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጡት ማብራሪያ ላይ በተለይም የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የማቋቋሙ ጉዳይ መልካም ሃሳብ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ቢመረት የተሻለ ዕድል ነው የሚሉት አዛውንቱ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚም ፋይዳ እንዳለው ያነሳሉ፡፡ በተለይም በምግብ ራስን ለመቻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ለአርሶ አደሩም ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ሰአት በጦርነት የሚፈታ ነገር የለም የሚሉት አዛውንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር በር ለማግኘት ከየትኛውም አካል ጋር ጦርነት የመግጠም ፍላጎት እንደሌላቸው ያነሱትን ሃሳብ እንደሚደግፉት ያስረዳሉ።
ወደብ ይኑረንና እንጠቀምበት ማለት ራሱን የቻለ ትልቅ ሃሳብ መሆኑን ገልፀው አንዱ ተጎድቶ ሌላው የሚጠቀምበት ሳይሆን ጥቅሙ ለጋራችን በሆነ መልኩ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
ሀገሪቱ ሌሎች ወደቦችን በመጠቀም ከፍተኛ ወጪ እያወጣች መሆኑን ጠቅሰው፤ የባሕር በር ማግኘቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውና ለወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ያስረዳሉ፡፡
ሌላኛው አስተያየቱን የሰጠን የከተማዋ ነዋሪ በጎልማሶች የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛል፡፡ አስማማው አበበ (ስሙ የተቀየረ) በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ እንደተሰማራ ይገልፃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጡት ማብራሪያ የዋጋ ንረትን ዝቅ ማድረግ ተችሏል በሚለው አልስማማም ይላል። ይህ አስተያየቱ ከየትኛውም አመለካከት የመነጨ እንዳልሆነ ጠቁሞ በተለይም በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚታየው የዋጋ ንረት ዘርፉ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ይናገራል፡፡ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ በናረ ቁጥር ግንባታዎች እየቀነሱ እንደሚሄዱም ይገልፃል፡፡
አብዛኛው በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ የተሠማራው የማህበረሰብ ክፍልም ሥራ-አጥ እየሆነ ይሄዳል የሚል ስጋት እንዳለው ያስረዳል፡፡ ከዛ ባሻገር ዛሬ በሃምሳ ብር የገዛነውን ሸቀጥ ነገ በመቶ ብር የምንገዛበት ሁኔታ ላይ ከመሆናችን አኳያ የዋጋ ንረቱ ቀንሷል ማለት አስቸጋሪ ነው የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት ዳዊት ዘንባባው ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ኢኮኖሚው ከምንጊዜውም በላይ ጤናማና ተስፋ ሰጪነት ይታይበታል ባሉት እንደሚስማማ ይገልፃል፡፡
እንደእርሱ ገለፃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሷቸው የባሕር በር ጉዳይ፣ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካው እንዲሁም ይመረቃል የተባለው የህዳሴ ግድብ ወደ ሥራ የሚገቡ ከሆነ የኢኮኖሚው ተስፋ ሰጪነት እንደማያጠራጥር ይናገራል፡፡
በተለይ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የማቋቋሙ ሃሳብ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንዳሉት ጠቁሞ አሁን ላይ ለማዳበሪያ እየወጣ ያለው ወጪ ቀላል እንዳልሆነ ያስረዳል፡፡፡ ለማዳበሪያ ድጎማ የሚወጣውን ወጪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንሳታቸውን ገልፆ ፋብሪካው ከተቋቋመ እነዚህን ወጪዎች ከማዳን ባሻገር ለብዙዎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ይጠቁማል፡፡
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባሕር በር ለማግኘት እየሄዱባቸው ስላሉት ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች መግለፃቸውን አስታውሶ የባሕር በር ለማግኘት በሚያስችላቸው መንገዶች ሁሉ ዝግጁ መሆናቸውን ማብራራታቸውን ያስረዳል፡፡
ምናልባትም የባሕር በር እየተጠየቁ ያሉ ሀገራት ምላሽ አሉታዊ ከሆነ ዲፕሎማሲያዊ መንገዱ እስከምን ድረስ ያስኬዳል በሚለው ዙሪያ ግን ጥያቄ እንዳለው ይገልፃል፡፡
ከዚያ ባሻገር ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ቢበዛ በስድስት ወራት እንደሚመረቅ መግለፃቸውን ጠቅሶ ይህ በራሱ ትልቅ ስሜት የሚፈጥር መሆኑን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ባለፈው ጊዜ ለቀሪ ሥራው ያስፈልገዋል ተብሎ ስለነበረው ገንዘብ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢሰጡበት ጥሩ እንደነበር ይገልፃል፡፡
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም