
አዲስ አበባ:- በኢትዮጵያ ለግብርና ምርታማነት ወሳኝ የሆነውን የአፈር ማዳበሪያ አሁን ባለው ሁኔታ ከውጭ ሀገር እየገዙ መቀጠል አዳጋች ስለሚሆንና አርሶ አደሩንም ስለሚጎዳ ቀጣዩ ህዳሴያችን ግዙፍ ማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት ይሆናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ገለጹ፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ አሁን ቀደም ብሎ የመናገር ፍላጎት ባይኖረንም ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ማምረት ካልቻለች የበርካታ አርሶ አደርን ሕይወት የሚነካ ስለሆነና ከምግብ ጋር የሚያያዝ ጉዳይ ስለሆነ በዘላቂነት መፍትሔ ልናገኝ አንችልም በሚል ስናጠና ቆይተናል፡፡ አሁን ግን የህዳሴውን ጉዳይ የምታውቁት ስለሆነ ፊታችንን ወደ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እናዞራለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ስለፋብሪካው ግንባታ በተደረገው ጥናት ከ2 ነጥብ 5 እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈልግ ታውቋል፡፡ በጣም በርትተን ከሠራን የማዳበሪያ ፋብሪካውን በበቂ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ አቋቁሞ ለመተግበር ቢያንስ ሦስት ዓመትና ከዚያ በላይ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም ሁለተኛው ህዳሴያችን የሚሆነው ማዳበሪያ ፋብሪካውን ከተቻለ በ‹‹ጆይንት ቬንቸር›› ከግሉ ሴክተር ጋር ከዚያም ከፍ ብሎ ከተገኘ በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት፤ ካልተቻለ ግን በመንግሥት በራሱ የግድ የማዳበሪያ ፋብሪካ የኢትዮጵያን ፍላጎት ሊመልስ በሚችል መልኩ መገንባት ይኖርብናል፡፡ ምናአልባትም የሚቀጥለው ዓመት ሁነኛው ተግባራችን የሚጀምር ይሆናል ብዬ አስባለሁ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከድጎማ አንጻር ለማዳበሪያ 84 ቢሊዮን ብር ነው የምንደጉመው፡፡ በአንድ ኩንታል 3 ሺህ 700 ብር እንደጉማለን፡፡ እኛ ማዳበሪያ ስለማናመርት የማዳበሪያ ዋጋ አንወስንም፡፡ አምራቾች ዋጋ ተምነው ለእኛ ሲያቀርቡ አርሶ አደሩ እንዳይጎዳ አቅም በፈቀደ መጠን እንደጉማለን፡፡
24 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ የአፈር ማዳበሪያ የሚያስፈልገን ሲሆን በአንድ ቀን 150 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ከወደብ እናጓጉዛለን፡፡ 150 ሺ ኩንታል አፈር ጭነን ወደ ሀገር ውስጥ እናስገባለን፡፡ የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን ከወደብ 150 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ በቀን ጭነን ማምጣት ብቻ ሳይሆን ወደ እያንዳንዱ አርሶ አደርም በወታደር አጅበን እንወስዳለን ሲሉም አክለው አስረድተዋል፡፡
አምና አማራ ክልል 7 ሺ ትራክ የጭነት ተሽከርካሪን ነው መከላከያ ያጀበው፡፡ መከላከያ ለእያንዳንዱ አርሶ አደር ማዳበሪያ ለማድረስ 7 ሺ የጭነት ተሽከርካሪ አጅቦ ወስዷል፡፡ ከውጪ እንገዛለን፣ እንደጉማለን፣ ወደብ ስለሌለን ከወደብ ማጓጓዙም ሌላ ጣጣ ነው፣ ከገባ በኋላ ወደእያንዳንዱ አርሶ አደር እንዲደርስ በአጃቢ እንዳርሳለን፡፡ ይህ ሁሉ ወጪ ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ ችግር ለመገላገል በከፍተኛ ቁርጠኝነት ሁለተኛ ሕዳሴያችን የሆነውን የማዳበሪያ ፋብሪካ እነገነባለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዕቅዱን ይፋ አድርገዋል፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 12 ቀን 2017 ዓ.ም