የዓለምን ኢኮኖሚ በበላይነት የተቆናጠጠችውን ልዕለ ኃያሏ አገር አሜሪካን ባልታሰበና ባልተጠበቀ መልኩ ብቅ ብለው ዓለምን ሲያነጋግሩ አሜሪካዊያንን ሲያነታርኩ የቆዩ መሪዋን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመረጠችው እ.አ.አ በ2016 ነበር።
ፕሬዚዳንቱ ያኔ የይምረጡኝ ዘመቻ ቅስቀሳ ሲጀምሩ ያቀርቡት የነበረው ሀሳብ በዓለም መገናኛ ብዙኃን መብጠልጠል ጀመረ። ሰውዬው ወይ ፍንክች አቋሜ የማያወላዳና ፅኑ ነው በማለት ሞገቱ። ‹‹አሜሪካዊያን አሜሪካዊያን ናቸውና ጅምር ላይ ልክ ኖት›› ያሉ ውስን ተከታዮችን አፈሩ። እውን ጤነኛ ሰው ይሄን ያደርጋል? በብዙዎች የተሰጠባቸው ትችት ነበር። የሰው ልጆችን በቀለምና በእምነት ከፍሎ ‹‹ከዚህች ምድር ርቀው መሄድ አለባቸው። ታላቅዋ አሜሪካ ለእነርሱ የሚሆን ቦታ የላትም። እናንተ አሜሪካንን የምታሳንሱ ናችሁ።›› ማለታቸው በእርግጥም ‹‹እኚህ ሰው ለአሜሪካም ሆነ ለተቀረው ዓለም አይበጁም።›› አሰኝቷቸው ነበር።
ደጋፊዎቻቸው ግን ‹‹አዎ ልክ ናቸው›› በማለት ይከተሉዋቸው ጀመር። በቁጥርም በረከቱ፤ እኛም የእርሳቸውን ሀሳብ እንደግፋለን ባዮች በዙ። ትራምፕ በአጃቢዎቻቸው በየቅስቀሳ አደባባዩ ደምቀውና ገነው ታዩ። እናም የምርጫው ወቅት እየቀረበ ሲሄድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኋን ስለእርሳቸው በስፋት ማውራትን ያዙ። ሰውዬው ከሚያቀርቡት ጥቁርና ሙስሊም ጠል ንግግራቸው ጋር አያይዘው ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› የሚለው መርህ መሰል መፈክራቸው ብዙ አሜሪካዊያንን አማለላቸው።
በተለይ ከብዙ የእስልምና እምነት ተከታይ አገራት ለመጡ ሙስሊሞችና ጥቁሮች ‹‹ፊት አልሰጥም እነርሱ ለአሜሪካን አይበጁም ድምፃችሁን ከሰጣችሁኝ የመጀመሪያ ተግባሬ ከዚህች ተስፋይቱ ምድር እነርሱን ማባረር ነው።›› በማለት በግልፅና በድፍረት በየምርጫ ቅስቀሳቸው ለደጋፊዎቻቸው መንገሩን ቀጠሉበት። ለአሜሪካና ለአሜሪካዊያን ይበጃል ያሉትን ሀሳብ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመናገር ‹‹እኔን ምረጡኝ!›› በሚል ፉከራ በምረጡኝ ዘመቻቸው ላይ ደጋግመው አሰሙ።
ከምርጫው መካሄድ ቀደም ብሎ መገናኛ ብዙኋኑ ስለ ትራምፕ ብዙ ቢሉም ያነሱት ለየት ያለ ሀሳብ ዓለምን ከማነጋገር ባለፈ ይመረጣሉ የሚል ግምት አልነበራቸውም። ምን አልባትም በወቅቱ ለፕሬዚዳንትነት ትልቅ ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩት ሂላሪ ክሊንተን የቅርብ ተፎካካሪ ሆነው ይቀርባሉ የሚለው ግምት በአንዳንዶቹ ተሰጥቶ ነበር።
እ.አ.አ በ2016 በኃያሏ አገር በተካሄደው ምርጫ ባልተጠበቀ ሁኔታ የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መጡ። ምንም እንኳን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ይፎክሩበት የነበረው ሙስሊም ጠል የሆነና ጥቁሮችን ያገለለ መርሀቸው ከምርጫው በኋላ ረገብ ቢያደርጉትም፤ ሰውዬው ከመመረጣቸው ማግስት አንስቶ በየዕለቱ መነጋገሪያ በመሆን የዓለም መገናኛ ብዙኋን ትኩረት ሆነው ቀጥለዋል።
ሰውዬው ያሻቸውን ተናጋሪ የሚፈልጉትን አድራጊ ናቸው። ለዚያውም ስሜት የተቀላቀለበት ውሳኔና ብዙዎችን ‹‹እኚህ ሰው ምን ነካቸው?›› ማስባላቸው ተለምዷል። በዚህም በአገሪቱ በትልልቅ ስልጣን ላይ የነበሩ ሰዎች ከዚህ ሰው ጋር አንሰራም ብለው በይፋ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።
ይህ እንዳለ ሆኖ ሰውዬው እስከ አሁን በቆዩበት የስልጣን ዘመናቸው የአሜሪካ ኢኮኖሚ እንዳይንገታገት በማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል። የስራ እድሎችን በመፍጠር ብዙ ሰርተዋል ቢባልም እጀ ረጅም የሆነችው አገር በየአቅጣጫው የዘረጋችው እጆችዋን በወጉ ተጠቅማ የአሜሪካንን ጥቅም በማስጠበቁ በኩል ፕሬዚዳንቱ ነጥብ ማስጣላቸው ይነገራል።
ነገር ግን አነጋጋሪው ሰው በድጋሚ ሀያልዋን አገር ‹‹አሜሪካን ለመምራት ዝግጁ ነኝ፤ በቀጣይ ዓመት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 ለፕሬዚዳንትነት በድጋሚ እወዳደራለሁ።›› ማለታቸውን ተከትሎ ዓለም የቆዩበትን መዘርዘርና መፃኢ ቆይታቸውን መተንበይ ተያይዞታል። የሪፐብሊካኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር በፍሎሪዳ ግዛት ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ለ2020 ምርጫ ዝግጁ እንደሆኑና ዳግም እንዲመረጡ ጠይቀዋል።
በምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ እና በባለቤታቸው ቀዳማይ እመቤት ሜላንያ ትራምፕ ታጅበው በ2016ቱ ምርጫ ወቅት በትንሽ የድምፅ ልዩነት ባሸነፉበት ግዛት ፍሎሪዳ የተገኙትና የምርጫ ቅስቀሳቸውን ከወዲሁ የጀመሩት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ዘወትር እንደሚያደርጉት ፓርቲያቸው ሪፐብሊካን የሚቀናቀነው ዲሞክራቶችን ‹‹እነርሱ አገር ሊበታትኑ የተዘጋጁ ናቸው›› በማለት አጥላልተዋል።
በዚህ ቅስቀሳቸው ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የፕሬዚዳንቱ አድናቂዎች ተገኝተው ድጋፋቸውን የሰጡ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የአሜሪካንን ጠንካራ የምጣኔ ሀብት ግንባታ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ፤ ህገ ወጥ ስደተኞችን ከአገራቸው እንደሚያባርሩና አገራቸውን በተለያየ መስክ የሚገዳደሩ አገራት ድል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በዚህም በ2020 ምርጫው ፕሬዚዳንቱ ስደተኞችን ከአሜሪካ ጠራርጎ ማስወጣት ዋነኛ አጀንዳቸው እንደሆነ ቢናገሩም፤ የትራምፕ አስተዳደር ግን ድንበር አቋርጠው ወደ አገሪቱ ሊገቡ የሚችሉ ጥገኝነት ጠያቂዎች ሊገቡ የሚችሉበትን በር ቢዘጋ የሚቀበሏቸውን ስደተኞች ቁጥር እንደሚቀንስ በተደጋጋሚ ሲያሳውቅ ቢቆይም፤ የስደተኞችን ጉዳይ ፈር ማስያዝ የሆነለት አይመስልም። ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ድንበር አቋርጠው ወደ ልዕለ ኃያሏ በገፍ እየገቡ ይገኛል። መግባት ያቃታቸው በርካቶች ደግሞ ድንበር ላይ ተከማችተዋል።
ይህን ያስተዋሉ ዴሞክራቶች ታዲያ ድንበር ላይ የስደተኞች ሰብአዊ መብት እየተጣሰ ነው በሚል የትራምፕን አስተዳደር ከፉኛ ይተቻሉ፣ ሪፐብሊካኑ በአንፃሩ ዲሞክራቶቹ የትራምፕን አጀንዳ ለመቀበል ዳተኛ መሆናቸው ለዚህ ቀውስ መባባስ ሁነኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ስለመሆኑ ይሞግታሉ።
በመሆኑም ሁሌም ከስደተኞች አናት ላይ የማይወርደው የዶላንድ ትራም አስተዳደር ቀጣይነት ላለው የስደተኞች ቀውስ ምላሽ የሚሰጥ አዲስ መመሪያ በያዝነው ሳምንት ሰኞ ዕለት ይፋ አድርጓል።
ከዚህ ቀደም የልዕለ ኃያሏን ድንበር ተሻግረው የገቡ ስደተኞች ወደ መጡበት አገር ወዲያውኑ እንዲመለሱ የሚደረገው፤ ከአሜሪካ ድንበር በ160 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ውስጥ ሲገኙና አሜሪካ ከገቡ ከሁለት ሳምንት በታች የሆናቸው ከሆኑ ብቻ ነበር። እንዲሁም በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ የሚገኙ ስደተኞች ወይንም ከሁለት ሳምንት በላይ የሆናቸው ግለሰቦች ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ተመርቶ ሕጋዊ ውክልና የማግኘት መብታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩ ይደረግ ነበር።
አሁን ላይ የወጣው አዲሱ ሕግ ግን ማንኛውም ስደተኛ በየትኛውም የአገሪቱ ስፍራ ቢገኝ በቁጥጥር ስር ከዋለ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳዩ ሳይታይና ስደተኛው ጠበቃ አቁሞ መብቱን ሳይጠይቅ በቀጥታ ወደ መጣበት እንዲመለስ ይደረጋል ተብሏል። በአዲሱ ደንብ መሰረትም ህጋዊ የመኖሪያ ማስረጃ የሌለው ማንኛውም ስደተኛና በተከታታይ ለሁለት ዓመት አሜሪካ ውስጥ እንደነበር በመረጃ ማረጋገጥ ያልቻለ ግለሰብ ወደ መጣበት አገር እንዲመለስ ይደረጋልም ተብሏል። ነገር ግን ጥገኝነት ለመጠየቅ የሚያበቃ ምክንያት ያላቸው ስደተኞች፤ የጥገኝነት ጉዳያቸውን የሚከታተል ባለሙያ የማናገር መብት አላቸው ተብሏል።
ፖሊሲው ለዜጎች ይፋ ተደርጎ በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች በአፋጣኝ ተግባራዊ መሆን የሚጀምር ሲሆን፤ የተለያዩ አካላት ፖሊሲው ላይ ያላቸውን አስተያየት እየተናገሩ ይገኛሉ። ከነዚህ መካከል የአገር ውስጥ ደህንነት መሥሪያ ቤቱ ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ ኬቨን ማክአሌናን፤ ‹‹ይህ ለውጥ በድንበር አካባቢ ያለብንን ጫና የሚያቃልልና ስደተኞችን ለመቆጣጠር አቅም የሚፈጥር ነው›› ሲሉ አሞካሽተውታል። አክለውም ‹‹መመሪያው ቀጣይነት ላለው የስደተኞች ቀውስ ምላሽ የሚሰጥ ነው›› ብለውታል።
የአሜሪካ የስደተኞች ጉዳይ ላይ ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎች በበኩላቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለ2020 ምርጫ ስደተኞችን መቆጣጠርን ቁልፍ ጉዳይ ለማድረግ መወሰናቸውን ያሳያል ያሉ ሲሆን፤ በአንጻሩ አሜሪካን ሲቪል ሊበርቲስ ዩኒየን የተባለ የመብት ተሟጋች ድርጅት ፖሊሲውን በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስዶ ለመሟገት ማሰቡን ተናግሯል።
ሰኞ ዕለት ፖሊሲው በተዋወቀ በሰዓታት ውስጥ የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ‹‹ይሄንን የትራምፕ እቅድ ለማስቆም በፍጥነት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደን ክስ እንመሰርታለን›› ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል። ድርጅቱ አክሎም ‹‹በአሜሪካ ለረዥም ጊዜ የቆዩ ስደተኞች በትራፊክ ደህንነት ጥሰት ፍርድ ቤት ከሚቀርቡ ሰዎች ያነሰ በፍርድ ቤት የመከራከር እድል አላቸው›› ሲሉም ምሬታቸውን ገልፀዋል።
የአሜሪካ የስደተኞች ፖሊሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥብቅ እየሆነ እየመጣ መሆኑን የሚያስረዱ አካላት ደግሞ፤ አገሪቱ በደቡብ በኩል ከሜክሲኮ ጋር በሚያዋስናት አካባቢ በግንብ ለመዝጋት የምታደርገውን እንደተጨማሪ በመጥቀስ ጉዳዩን አሳሳቢ ብለውታል።
በተጨማሪም የሲቪልና ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ፕሬዚዳንት ቫኒታ ጉፕታ፤ የፕሬዝዳንት ትራምፕን እቅድ የስደተኞች ጉዳይ የሚያየውን ተቋም ‹‹ወረቀታችሁን አሳዩን ወደሚል ፈርጣማ ኃይል እየቀየሩት ነው›› ያሉ ሲሆን፤ ሌላኛው የሕግ ባለሙያ የሆኑት ጃኪ ስቲቨንስ በበኩላቸው ወደመጣችሁበት አገር ተብለው ከሚመለሱ ሰዎች መካከል የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው እንደሚገኙበት ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 19/2011
ሶሎሞን በየነ