የእንግሊዙ ታዋቂ ጋዜጣ ዘ- ጋርድያን ኢራን ሁለት የእንግሊዝን መርከቦችን ማገቷን አስነብቧል። የእንግሊዝ መርከቦች የሆርሙዝን ባሕረ ሰላጤ እንዲያስወግዱ ተመክረው የነበረ መሆኑን የገለጹት የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሀንት ናቸው። ሆኖም የኢራን እርምጃ ተቀባይነት የሌለው ነው ማለታቸውን በመዘርዘር የዘ- ጋርድያን ዘጋቢዎች ጁሊያን በርገር ከዋሽንግተን ፤ፓትሪክ ዊንቱር እና ኬቪን ራውሊንሰን ከለንደን በሰፊው ዳሰውታል። እኛም ይህን አስነበብናችሁ።
ኢራን በቅርቡ ሁለት የዘይት ጫኝ መርከቦችን (ታንከሮችን ) በሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ አግታለች። አንደኛው መርከብ በእንግሊዝ ሌላኛው በላይቤርያ የተመዘገበ ነው። ይህ ድንገተኛ ክስተት በገልፉ ያለውን ውጥረት በከፋ ሁኔታ አባብሶታል።
የአብዮታዊው ዘብ ኃይል ያገተውን የእንግሊዝ ባንዲራ የሚያውለበልብ ስቴና ኢምፔሮ የተባለ የዘይት ጫኝ መርከብ (መርከብ) ከ23 ምድብተኞቹ ጋር ወደ ወደብ መውሰዱን አስታውቋል። የኢራን ባለስልጣኖች መርከቦቹ የታገቱት ዓለም አቀፉን የማሪታይም ሕግ በመተላለፉቸው ነው ማለታቸውን ዘ- ጋርድያን ከትቦታል።
ዓርብ እገታው ተፈጽሞ ቅዳሜ ዕለት ከፊል መንግስታዊ የሆነው የኢራን ዜና ወኪል ፋርስ መርከቡ ወደ ባንዳር አባሳ ወደብ መወሰዱን ምድብተኞቹ በመርከቡ ውስጥ እንደሚገኙ የዘገበ ሲሆን በሌላም በኩል በኢራን መንግስት የሚመራው የዜና ወኪል ኢርና መርከቡ የተያዘው ከኢራን አሳ አስጋሪ ጀልባ ጋር በመጋጨቱ ነው ብለዋል።
ሁኔታውን የአሳ አስጋሪው ጀልባ ለኢራን ወደብና ማሪታይም ድርጅት ሪፖርት አድርጓል። ማሪታይም በኩሉ አብዮታዊው ዘብ ኃይል ሪፖርት ማድረጉ ተገልጾአል። የታገተው ስቴና ኢምፔሮ መርከብ ባለቤቶች በበኩላቸው መርከቡ በሆርሙዝ ባሕረሰላጤ ዓለም አቀፉን የውሀ መስመር ተከትሎ በሚያቋርጥበት ወቅት ማንነታቸው ባልታወቁ አነስተኛ ጀልባዎችና ሄሊኮፕተሮች ከበባ ተደርጎበት እንደነበር ይናገራሉ።
ሁለተኛው ሜስዳር የተባለው መርከብ የላይቤርያን ባንዲራ የሚያውለበልብና በእንግሊዝ የሚመራ ሲሆን ከሚጓዝበት መደበኛ መስመር በድንገት አቅጣጫ በመለወጥ የሳውዲ ወደብ ወደ ሆነችው ራስታኑራ አምርቷል። የኋላ መረጃዎቹ (ትራክ ሪከርድ) እንደሚያመለክቱት የአቅጣጫ ምልክት ሰጪውን ከማጥፋቱ በፊት ወደ ሰሜን አቅጣጫ በመጓዝ ወደ ኢራን ጠረፍ አምርቷል።
ሜስዳር መርከብ ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ እንደገና ምልክት ሰጪ መገናኛውን ከፍቶአል። ከፊል መንግስታዊ የሆነው የዜና ወኪል ፋርስ መርከቡ በሆርሙዝ ባሕረሰላጤ ለአጭር ጊዜ መታገቱንና ጉዞውን ለመቀጠል ከመፈቀዱ በፊት የአካባቢ አየር ንብረት ደንቦችን እንዲያከብር ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ገልጿል። በእንግሊዝ ግላስጎው መሰረቱን ያደረገው የሜሴዳር መርከብ ባለቤት የእንግሊዝ ኖርበልክ ሺፒንግ ካምፓኒ መርከቡ በታጠቁ ጠባቂዎች መከበቡን በኋላም ጉዞው እንዲቀጥል መደረጉንና የመርከቡ አባላት በሙሉ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።
መርከቦቹ ከታገቱ በኋላ ስቴና በልክና የሰሜን ማሪን ማኔጅመንት ባወጡት መግለጫ ከመርከቡ ጋር ግንኙነት ማድረግ እንዳልተቻለ ገልጸዋል። የስቴና ኢምፔሮ መርከብ ባለቤት የሆነው ካምፓኒ መርከቧ ሙሉ በሙሉ ዓለም አቀፍ የናቪጌሽንና የማሪይም ሕጎችን አሟልታ በነበረችበት ሁኔታ ነው ድርጊቱ የተፈጸመው ብሏል።
የስቴና በልክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢሪክ ሀኔል በመርከቧ ውስጥ 23 የሕንድ፤ የሩሲያ፤የላቲቪያና የፊሊፒኖ ተወላጆች እንደሚገኙ አስታውቆል። እስከአሁን የደረሰ ጉዳትን የሚያመለክት ሪፖርት አለመኖሩን ገልጿል። ዋና ስራ አስፈጻሚው የሠራተኞቻችን ደህንነት የመጀመሪያው ትኩረታችን ነው ብለዋል።
የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሀንት ‹‹እኛ በጣም ግልጽ ነን፤ ሁኔታው በፍጥነት ካልተቃለለ ከባድ መዘዝ ያስከትላል›› ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል። አክለውም ወታደራዊ አማራጮችን አንመለከትም። ሁኔታውን ለማቃለል ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን እንከተላለን። ግልጽ የምንሆነው የግድ ችግሩ መፈታት እንዳለበት ነው። ስቴና ኢምፔሮ የተከበበችው በአራት የኢራን መርከቦችና ከአናትዋ ላይ በሚሽከረከር ሄሊኮፕተር ሲሆን ሌሎች 10 የኢራን ፈጣን ጀልባዎች ደግሞ ሜስዳር መርከብን ከበዋት ነበር ብለዋል ሚኒስትሩ።
ይህ እገታ ተቀባይነት የለውም። የናቪጌሽንን (በባሕር ላይ) የመንቀሳቀስ ነጻነትን መብት ማክበር መሰረታዊ ሲሆን ሁሉም መርከቦች በአካባቢው በሰላም ደህንነታቸው ተጠብቆ መንቀሳቀስ ያለባቸው መሆኑን ሀንት ገልጸዋል። በሰሞኑ በተፈጠረው ሁኔታ ለጊዜው የእንግሊዝ መርከቦች ከአካባቢው እንዲርቁ የእንግሊዝ መንግስት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
በተፈጠረው የሆርሙዝ ባሕረሰላጤ ውጥረት ላይ ለመነጋገር የተሰበሰበው የእንግሊዝ የሚኒስትሮች ስብሰባ ካበቃ በኋላ ኢራን የወሰደችው ተቀባይት የሌለው እርምጃ ዓለም አቀፉን የባህር ላይ ደንብና ነጻነት የሚጋፋ በመሆኑ አሳስቦናል ሲል የእንግሊዝ መንግስት መግለጫ ያስረዳል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሁኔታው በፍጥነት ካልተፈታ ከባድ ሁኔታን ያስከትላል። ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅርብ ግንኙነት እያደረጉ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ ሌላ ተጨማሪ ስብሰባ ይኖራል ብሏል መግለጫው።
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በገልፉ አካባቢ የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክቶ አሜሪካ ከእንግሊዝ ጋር ትነጋገራለች ብለዋል። ኢራን ፍሮንት ፔጅ የተሰኘው የዜና ምንጭ ስማቸውን ያልጠቀሱ የሠራዊቱን ምንጮች በመግለጽ እንደዘገበው አብዮታዊው ዘብ ዓለም አቀፍ የማሪታይም ሕግን በመተላለፏ ስቴና ኢምፔሮ የተባለችውን መርከብ ማገቱን ገልጿል።
የዘይት ታንከሩ በሆርሙዝ ባሕረሰላጤ መስመሩን ሲያቋርጥ መልዕክት አስተላላፊውን በማጥፋት ኢራን ለሰጠችው ማስጠንቀቂያ ቦታ ባለመስጠቱ በአብዮታዊው ዘብ ኃይሎች መያዙን ገልጿል። የዘይት ጫኝ ታንከሮቹ የታገቱት የጀብሪላታር ባለስልጣናት የአውሮፓ ሕብረትን እገዳ በመተላለፉና ለሶርያ ነዳጅ ዘይት በመጫን ተጠርጥሮ በሮያል ማሪን የተያዘውን የኢራን ነዳጅ ዘይት ጫኝ ታንከር እገታ ማራዘማቸውን ከገለጹ ከሰዓታት በኋላ ነው። ቴህራን ቀደም ሲል የግሬስ 1 መርከብ የታገተው በዋሽንግተን ትዕዛዝ የተካሄደ ሽፍትነት ነው በሚል አጣጥላዋለች። የኢራን ፖለቲከኞች በአብዮታዊው ዘብ የሚመሩት የሀገሪቱ ኃይሎች በገልፉ አካባቢ እየጨመረ የመጣውን በመርከቦች መስመር ላይ የሚፈጸመውን መተናኮል በኃይል እንዲመክቱ ጥሪ አድርገዋል።
ስቴና ኢምፔሮ 30ሺ ቶን የጫነች ንብረትነቷ የስዊድን ሆኖ በእንግሊዝ ባንዲራ የምትንቀሳቀስ መርከብ ስትሆን ወደ ሳኡዲ አረቢያ እያመራች ነበር። የኋላ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በድንገት ዓለም አቀፉን የውሀ መስመር ለቃ ወደሰሜን አቅጣጫ ቃሺም ወደተባለችው የኢራን ደሴት እንድታመራ ተገዳለች። እዚህ ቦታ ላይ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ የጦር ሰፈር አለው።
ቀደም ሲል የኢራን አብዮታዊ ዘብ ግሬስ 1 የተባለው መርከብ ከታገተ ከ6 ቀናት በኋላ የእንግሊዝን መርከብ ለመማረክ ያልተሳካ ጥረት አድርጎ ነበር። ይሄን ጠለፋ ለማካሄድ የእንግሊዝን መርከብ አቅጣጫ ለማሳት ተሰልፈው የነበሩትን ሶስት የኢራን ወታደራዊ መርከቦች ሞንትሮስ የተባለው የእንግሊዝ የጦር መርከብ ጣልቃ በመግባት እንዲገለሉ አድርጓል።
የአሁኑ የእንግሊዝ መርከቦች በኢራን መታገት የተፈጠረው በገልፉ የነዳጅ ዘይት የውጭ ንግድ መስመር ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ውጥረት በሰፈነበት ወቅት ነው። በአካባቢው በቅርብ በሚገኙት በኢራን እንግሊዝና በአሜሪካ ወታደራዊ ኃይሎች መካከል ፍጥጫና ውጥረት ነግሷአል።
ይህ እገታ በኢራን ከመፈጸሙ አንድ ቀን በፊት የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ኃይሎች በገልፉ አካባቢ የኢራንን ድሮን መተው ጥለዋል ማለታቸውን ቴህራን አስተባብላለች። አንድ የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ ቃልአቀባይ ሁሉም ድሮኖች በሰላም ወደ ጦር ሰፈራቸው መመለሳቸውን የገለጹ ቢሆንም ትራምፕ ግን ‹‹ምንም ጥርጥር የለውም መተን ጥለነዋል›› ብለዋል።
ትራምፕ የአሜሪካው ዩኤስኤስ ቦክሰር የጦር መርከብ ያለበት አካባቢ ሰው አልባው ተሽከርካሪ በ1000 ሜትር ርቀት ውስጥ ሲጠጋ እንዲመለስ የተደረገለትን ተደጋጋሚ ጥሪ ባለመቀበሉ የመከላከል እርምጃ ወስዷል ብለዋል።
በአጠቃላይ ዓመታትን የዘለቀው የአሜሪካ እና እንግሊዝ ከኢራን ጋር ያላቸው ቅራኔ ሰሞኑን እየተሰተዋለ ካለው የመርከብ እገታ እና የሰው አልባ አውሮፕላን መመታት የአገራቱን ሰጥ አገባ አካሮታል። ይህ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ አሜሪካ እና እንግሊዝ ከኢራን ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት ወደ ከፋ ጠብ እንዳያስገባው ተፈርቷል።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 18/2011
ወንድወሰን መኮንን