እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር በ1888 ዓ.ም የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ የመጣው የኢጣሊያ መንግሥት ጦር በኢትዮጵያውያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቁን ተከናነበ። ጣልያኖች ዓድዋ ላይ ድል ከሆኑ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብለው ነበር። ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሻረ፤ ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀትም በግማሽ ቀነሰ፤ ከዓድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነአካቴው የአፍሪካን ምድር ለቅቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ። ይህ ሁሉ ግን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር።
ከእንግሊዝ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያሏቸውን ቅኝ ግዛቶች የምታስተዳድረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ መኖር አልቻለችም። ከዓድዋ ሽንፈት 30 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አምባገነኑ የፋሺዝም አቀንቃኝ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ራሱን እንደ ሮም የቀድሞው ንጉሥ ጁሊየስ ቄሳር በመቁጠርና “የኢጣሊያን ክብር ለዓለም አሳያለሁ” በሚል የረጅም ጊዜ ተስፋ የቅኝ ግዛት ዘመቻውን ሊያሳካ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው። ነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ኢጣሊያውያን በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የነበራቸውን ትኩረት ለማስቀየር፣ እየጨመረ ለመጣው የኢጣሊያ ህዝብ የማስፈሪያ ቦታ ለመፈለግ እንዲሁም በአውሮፓ መድረክ የከሸፈበትን የመስፋፋት ፖሊሲ ለማካካስ ቅኝ ግዛትን አማራጭ አድርጎ ተነሳ። ከሁሉም በላይ ግን ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ሙሶሊኒ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ።
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለዓርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎችና በመንግሥታቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ ‹‹ከእንግዲህ አላውቃቸውም›› አለች። ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች።
ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም። ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ። ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ከፃፉና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል አንዱ ያልተዘመረላቸው ሌተናል ጀኔራል ኃይሉ ከበደ ናቸው።
የልጅነት ጊዜ
ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ (በኋላ ሌተናል ጀኔራል) ከአባታቸው ዋግሹም ከበደ ተፈራ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ኂሩት ንጉሤ ዋግ አውራጃ ውስጥ ገረብ ቆላ በተባለ ስፍራ ተወለዱ። እንደዘመኑ የመኳንንት ልጆች በወላጆቻቸው ዘንድ አስተማሪ ተቀጥሮላቸው ትንሽ ከተማሩ በኋላ ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው አማርኛ ንባብና የሃይማኖት ትምህርት ተምረዋል። ከዚያም ወደ ሰቆጣ በመሄድ ፈረስ ግልቢያን፣ ተኩስን፣ ዒላማን፣ ሰንጠረዥ ጨዋታንና በገና መደርደሩን አሳምረው ከውነውታል። በተለይም በቅኔ ትምህርታቸው ላቅ ያሉ እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል።
የንጉሠ ነገሥቱ አማካሪ መሆን
በእድሜና በእውቀት ሲጎለምሱም በአባታቸው በዋግ ሹም ከበደ ተፈራ አማካኝነት የአስተዳደር ስርዓትን አጠኑ፤ በአደባባይ በመገኘትም በሀገሪቱ በነበረው የሸንጎ ስርዓት ተካፋይም ሆኑ። በፀበኞች መካከል ሰላምን የሚፈጥሩ፣ ትሁት እንደሆኑ ስለሚታወቅና ይህ ባህሪያቸውም በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘንድ ስለተሰማ ወደ አዲስ አበባ ሄደው መንግሥትን በምክር እንዲረዱ ንጉሠ ነገሥቱ አስጠሯቸው። በዚህም የንጉሠ ነገሥቱ አማካሪ ለመሆን በቁ። ለተወሰኑ ዓመታት በአዲስ አበባ ከቆዩ በኋላም አባታቸው ዋግሹም ከበደ በእድሜ ምክንያት ስለተዳከሙ እርሳቸውን እየረዱ ዋግን በእንደራሴነት እንዲያስተዳድሩ ተወስኖ ወደ ዋግ ተመለሱ። ደጃዝማች ኃይሉም አገሩን ማስተዳደር ጀመሩ።
የፋሺስት ወረራና የጀግንነት ተጋድሎ
ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ወደ ዋግ ተመልሰው አገር ማስተዳደር ከጀመሩ ጥቂት ጊዜያት በኋላ የፋሺስት ኢጣሊያ የወረራ ደመና በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ አንዣበበና ሰላም ደፈረሰ። ደጃዝማች ኃይሉም የመጀመሪያ ስራቸው በዋግ ግዛት ውስጥ ለውትድርና ብቁ የሆኑትን ሰዎች መመልመል፣ የውትድርና ትምህርት ማለማመድ፣ የጦር መሣሪያዎችን መሰብሰብና የተበላሹትን ማስጠገን ሆነ። ስንቅ እንዲሰናዳና አገሬውም ለጦርነቱ እንዲዘጋጅ መመሪያ አስተላለፉ። ወታደሮችን በማሰልጠን እንዲሁም የራሳቸውና ከመንግሥት የተቀበሏቸውን ጠመንጃዎች ዝግጁ በማድረግ ጦራቸው ስንቁንና ትጥቁን አደራጅቶ ለውጊያ አመቺ በሆነ ቦታ ነቅቶ እንዲጠብቅ ዘዴ በመቀየስ ጦርነቱን መጠባበቅ ጀመሩ።
ጦርነቱ እንደተጀመረም በደጃዝማች ኃይሉ ከበደ የሚመራው ጦር የአምባላጌን በር ይዞ ድንኳኑን ተከለ። በጥቅምት ወር 1928 ዓ.ም የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር አምባላጌ ላይ በሰፈረውና በተጠንቀቅ ላይ በነበረውን የዋግ ጦር ላይ ከአውሮፕላን ቦምብና የመርዝ ጭስ አፈሰሰበት፤ በአደጋውም በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሰዉ። ከዚህ በኋላ ደጃዝማች ኃይሉ ለጦራቸው እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላለፉ።
‹‹ … ድንኳናችሁን ከሰፈር አትንቀሉ፤ ምክንያቱም ጠላት ‹ድንኳኑ ሰውና ጓዝ አለበት› እያለ ቦምቡን ስለሚያፈስሰው እናንተ በየጥጉ እየሆናችሁ አምባውንና በሩን ጠብቁ።›› … ይህ ብልሃትም ከጠላት አውሮፕላን ለሚጣለው ቦምብም ሆነ ጋዝ በቂ መከላከያ ብቻ ሳይሆን አሳሳች መረጃ በማስተላለፍ አድፍጦ የማጥቂያ ስልት ሆኖ አገልግሏል።
በኅዳር ወር 1928 ዓ.ም የደጃዝማች ኃይሉ ጦር በምስራቅ አቅጣጫ የሚመጣውን የጠላት ጦር ለመከላከል እንዳመኾኒ በተባለው አካባቢ እንዲሰፍርና አካባቢውን በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ ተመድቦ ነበር። የደጃዝማች ኃይሉ ጦር ከአላጌ አካባቢ ተነስቶ ዋነኛው ጦርነት ወደሚካሄድበት ወደ እንደርታ እንዲንቀሳቀስ ሲደረግ የአምባላጌን ስትራቴጂካዊ ተራራ በር እንዲረከብና እንዲጠብቅ የተደረገው በራስ ካሣ ኃይሉ ይመራ የነበረው ጦር ነበር።
የፋሺስት ጦር ባንዳዎችን በመጠቀም ከሸዋ እስከ አላጌ በር ድረስ ያለው ዋና መንገድ የኢትዮጵያ ተዋጊ ሰራዊት የሚጓዝበት መሆኑን አወቀ። ጦሩ ዓብይ ዓዲን በቁጥጥሩ ስር በማዋሉ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ የጠላትን ጦር ለመመከት ጦራቸውን ይዘው የአምባላጌንና የእንደርታና አካባቢዎች እየጠበቁና ለቀጣይ ዘመቻዎች እየተሸጋገሩ ተንቤን ደረሱ።
በጀኔራል ደላሰምና በሌሎች ሁለት የጦር መኮንኖች የሚመራው የፋሺስት ጦር የዓብይ ዓዲን አምባ ለመያዝ ከተምቤን በሌሊት ተንቀሳቅሷል። በተጠንቀቅ ይጠባበቅ የነበረው የደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ጦር ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ አምባው በጠላት እጅ እንዳይወድቅ የሚያስችል እቅድ አወጣ። ፍልሚያው ተጀመረ። አድሮ ፆለሌ በተባለው ቦታ ላይ ከጠዋት እስከ ምሽት ከጠላት ጦር ጋር ከባድ ውጊያ ተደረገ። የጠላት ወታደሮች ሞትን ፊት ለፊት ከመቀበል ብለው ወደኋላቸው እየሸሹ ጡንቁ ወደሚባለው ወንዝ ራሳቸውን እየወረወሩ አለቁ፤ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደና ወታደሮቻቸው በድል ፎከሩ። ብዙ የጠላት ወታደሮችና የጦር መሳሪያዎችም ተማረኩ። በዚህ ጦርነት ላይ ከደጃዝማች ኃይሉ የጦር መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት እማኙ ወንዴ ለእናት አገራቸው ክብር ተሰውተዋል።
ከዚህ በኋላም ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ በመቀሌ በኩል የመጣውን ጦር እንዲከላከሉ ተወሰነ። በዚያም ጦራቸው አድፍጦ እንዲዋጋ በማድረግ በጠላት ጦር ላይ ከባድ ኪሳራ አድርሰውበታል። የፋሺስት ጦርም ወደኋላ ለማፈግፈግ ተገደደ። ከዚህ በተጨማሪም ደጃዝማች ኃይሉ በቀበርታ በኩል የሚመጣውን የጠላት ጦር እንዲከላከሉ በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት ተዋጊ ሰራዊታቸውን በየግንባሩ አሰልፈው ከፋሺስት ጦር ጋር ከባድ ውጊያ አድርገዋል።
በማይጨው ጦርነት ከጠላት ጋር የጨበጣ ውጊያ ሲያደርጉ አንገታቸው ላይ በጥይት ተመትተው የመቁሰል አደጋ ባጋጠማቸው ወቅት እንኳ ‹‹አገራችንን ምንም ቢሆን ጠላት አይገዛትም፤ ምድራችን በጠላት እግር አትረገጥም፤ በየበረሃችን እንመሽጋለን፤ እስከመጨረሻው የደም ጠብታና እስከመጨረሻው የነፃነት ጊዜ እንዋጋለን›› በማለት የትግል ቃል ኪዳናቸውን አስተጋብተው ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ አዲስ አበባ መመለስ መጀመራቸው በተነገረበት ወቅት እንኳ የደጃዝማች ኃይሉ ጦር በጠላት ጦር ላይ ድል ተቀዳጅቶ የጦር መሣሪያዎችን መማረክ ችሏል። ለዚህም
‹‹በማይጨው ጦርነት ቢቆስል አንገቱ፣
እስከደም ጠብታ ነው ቃሉ ትንቢቱ›› ተብሎ ተገጥሞላቸዋል።
ሐምሌ 1 ቀን 1928 ዓ.ም ሲልዳ በተባለው አካባቢ በተካሄደው ውጊያ የደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ጦር የፋሺስትን ጦር ዳግም ድል አደረገው። በጠላት ጦር እጅ ተይዘው የነበሩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችም በደጃዝማች ኃይሉ ጦር እጅ ወደቁ። በዚህ ጦርነት ላይ የደጃዝማች ኃይሉ ባለቤት ወይዘሮ ሸዋነሽ አብርሃ እና ልጃቸው ልጅ ወሰን ኃይሉም ተካፋዮች ነበሩ።
‹‹የሲልዳን ጦርነት ድል አድርጎ ወግቶ፣
በአንድ ቀን ፈጃቸው አምደወርቅ ገብቶ።
ሚስቲቱ ሸዋነሽ ልጁ ወሰን ኃይሉ፣
በአምደወርቁ ውጊያ ድል የተካፈሉ።›› ተብሎ የተገጠመውም ለዚህ ነው።
ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ምድር ብቻ ሳይሆን በኢጣሊያ የሚገኙት ፋሺስቶች ጭምር ስለ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ጀግንነት በሰፊው ማውራት ጀመሩ። አዲስ አበባ ከተማ ስትወረርና ስትዘረፍ ከገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት ከተዘረፉ መዛግብትና ፎቶግራፎች መካከል የደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ፎቶም አብሮ ተዘርፎ ስለነበር ‹‹የታላቁ ቄሳርና የታላቋ ኢጣሊያ ዋናው ጠላት›› ተብለው ምስላቸው በኢጣሊያ ጋዜጦች ላይ እንዲወጣ ተደረገ። የፋሺስት ባለስልጣኖችም ‹‹ዋነኛ ጠላታችን›› ያሉትን ሰው እንዴት ማስወገድ እንዳለባቸው ምክክር ጀመሩ።
ድልን በድል ላይ እየደረበ መጓዝን ልማዱ ያደረገው የደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ጦር ሐምሌ 16 ቀን 1928 ዓ.ም ዓምደወርቅ ውስጥ መሽጎ በነበረው የጠላት ጦር ላይ ውጊያ ከፍቶ ብዙ የጠላት ጦር አባላትን ገድሎና ማርኮ ድል ጨበጠ። በታኅሳሥ ወር 1929 ዓ.ም ደግሞ ደጃዝማች ኃይሉ ጦር የሞት የሽረት ውጊያ በማድረግ የፀለጌን በር ከፋሺስት ጦር ማስለቀቅ ችሏል።
የካቲት 13 ቀን 1929 ዓ.ም በዓብይ ዓዲ በተካሄደው ጦርነት የፋሺስትን የጦር አውሮፕላኖች የተቋቋመው የደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ጦር፣ ጦርነቱን አሸንፎ ዓቢይ ዓዲ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውለብልቧል። ሐምሌ 4 ቀን 1929 ዓ.ም በዓምደ ወርቅ እንዲሁም ነሐሴ 12 ቀን 1929 ዓ.ም ደግሞ ሰልዳ ላይ የተካሄዱት ጦርነቶችም የደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ጦር ተጨማሪ ድል የተቀዳጀባቸው የነፃነት ተጋድሎዎች ነበሩ። ከዚህ በተጨማሪም ድገርሻ፣ ተላላ እና ጎቶቾ ቢላ በሚባሉ አካባቢዎች ላይ ሁሉ ከጠላት ጋር ውጊያ ገጥሞ የነበረው ጦራቸው አንጸባራቂ ድሎችን ተቀዳጅቷል።
በተደጋጋሚ ሽንፈት የተከናነቡት የፋሺስት ወታደራዊ ባለስልጣናት ደጃዝማች ኃይሉን በሰው አምሳልና መጠን የተፈጠሩ እንዳልሆኑ አድርገው ይገምቱ እንደነበር ይነገራል። የደጃዝማች ኃይሉ የሽምቅ ውጊያ ከዕለት ወደ ዕለት እየተጠናከረ ሲመጣ የጠላት ወገን መሸበርና መራዱ በዛበት። ከዚያም አልፎ የእርሳቸው ስም ሲነሳ የሚሸሸው ሰው በዛ። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር መኮንኖችም ተራራ ሲያዩ ‹‹ኃይሉ ይህንን ያህላል›› ይሉ እንደነበር በታሪክ ተፅፏል። በመሆኑም የፋሺስት ጦር ኃይሉን አሰባስቦ ኃይለኛውን ሰው ደጃዝማች ኃይሉን መፈለግ ዋና ስራው ሆነ።
በመስከረም ወር 1930 ዓ.ም ወለህ በተባለው ስፍራ ላይ የጀግናው ኃይሉ ከበደ ጦር በፋሺስት ጦር ተከበበ። አይበገሬው አርበኛ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ከጠላት ወገን በተተኮሰ ጥይት ተመትተው ወደቁና ሕይወታቸው አለፈች። ፋሺስቶችም ዋነኛ ጠላታችን ያሉትን የደጃዝማች ኃይሉን አንገት ቆርጠው በሮም በጋዜጦች ላይ እንዲወጣ አደረጉ። በወለህ ጦርነት ላይ የተማረኩት ኢትዮጵያውያን ጀግኖችም በስቅላት ተገደሉ።
ከሞቱ በኋላም ፋሺስቶች ደጃዝማች ኃይሉ ከበደን እንደሚፈሯቸው ያሳዩበትን ተግባር ፈፀሙ፤ ከአንገታቸው በታች ያለውን አስከሬናቸውን በአህያ አስጭነው ወደ ገደል ወረወሩት። በኋላም የአካባቢው አርሶ አደሮች አስከሬኑን አግኝተውት በስርዓት ቀበሩት። ከፋሺስት ጦር መባረር በኋላ ደግሞ አስከሬናቸው ከተቀበረበት ወጥቶ የአያታቸው የዋግ ሹም ተፈራ እና የአባታቸው የዋግ ሹም ከበደ ተፈራ አፅም ባረፈበት በሰቆጣ ደብረ ገነት መድሃኔዓለም ቤተ-ክርስቲያን በክብር እንዲያርፍ ተደርጓል። ይህን ጀግንነታቸውን በመገንዘብም የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጀግናው ዓርበኛ፣ ከሞቱ በኋላ፣ ‹‹ሌተናል ጀኔራል›› በሚል ማዕረግ እንዲጠሩ ወስኗል።
ፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ ከሞቱ በኋላ የፈፀማቸው የለየለት የፍርሃትና የጭካኔ ድርጊቶች ኢትዮጵያውያንን ለበለጠ ትግል አነሳስቶ ነፃነታቸውን እንዲያስመልሱ ምክንያት ሆነ።
ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነፃነት ሰማዕታት !
አዲስ ዘመን ሀምሌ 17/2011
አንተነህቸሬ