
አዲስ አበባ፡- የመንግሥት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ሥራ ላይ ያዋለው አዲሱ የግዢ አሠራር ለበርካታ ዓመታት የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና አደጋ የሚያስከትሉ ኬሚካሎችን በወቅቱ ለማስወገድ የሚያግዝ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት አንስቲትዩት የግዢ ቡድን መሪ አቶ ጌታነህ የማነብርሃን ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የመንግሥት ግዢ እና ዕቃ ማስወገድ አገልግሎት የዘረጋውና ከወረቀት ንክኪ የጸዳው የዲጂታል አሠራር በተለይም የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎችን በወቅቱ ለማስወገድ በእጅጉ የሚረዳ ነው።
ተቋማት እንደ መኪና እና መሰል ያገለገሉ እቃዎች እንዲወገዱላቸው ለመንግሥት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጥያቄ ሲያቀርቡ አብዛኞቹ ሰነድ ስላላቸው በወረቀት ላይ በሰፈረው መረጃ መሠረት እንዲወገዱ ይደረጋል።
ይሁንና እንደ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ያሉ የምርምር ተቋማት ሰነድን መሠረት አድርገው ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎችን ለማስወገድ ይቸገራሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ ኬሚካሎች እንደ ሌሎች ያገለገሉ ዕቃዎች እና መኪኖች የራሳቸው ሰነድ እና ዶክሜንት የላቸውም፤ በዚህም በተደጋጋሚ እንዲወገዱ ቢጠየቅም አስፈላጊው መረጃ ተሟልቶ ስለማይገኝ ለረጅም ጊዜ ተከማችተው ይገኛሉ። በዚህም በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
በየተቋሙ ያለው የኬሚካል ክምችት በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአግባቡ ካልተወገደ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ አስረድተዋል።
ኬሚካሎች የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃ መሆኑን የሚመረምሩ ብቁ ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉም ጠቁመዋል። በምርምር ማዕከላት እና በዩኒቨርሲቲዎች እስከ አሁን ድረስ የኬሚካል ጉዳይ መፍትሔ እንዳላገኘ የጠቆሙት አቶ ጌታነህ፤ አዲሱ የዲጂታል አሠራር ኬሚካሎች የተመረቱበትን፣ አገልግሎት መስጠት የሚያበቁበትን እና አጠቃቀማቸውን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃዎችን መዝግቦ ስለሚይዝ ጉዳት ሳያደርሱ በወቅቱ ለማስወገድ እንደሚያገለግል ጠቁመዋል።
የገቢዎች እና ጉምሩክ ባለ ስልጣንም ከግዢ አገልግሎት ጋር በመሆን የሚገቡትን ኬሚካሎች የቆይታ ጊዜ በአግባቡ መዝግቦ ቢያስገባ በወቅቱ ለማስወገድ ይረዳል ሲሉ ገልጸዋል።
ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች የሚያስከትሉት አደጋ ከባድ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌታነህ፤ ኬሚካሎች የሚሠሩበት ውሁድ በግልፅ ስለማይታወቅና በብዛትም የሚገቡት ከውጭ ሀገር በመሆኑ ሙሉ መረጃዎቻቸውን መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ከውጭ ገበያ የምናስመጣቸውን ኬሚካሎች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ቢደረግ ደግሞ ወጪ ከመቀነስና የቆይታ ጊዜያቸው በግልፅ እንዲታወቅ ለማድረግ ይጠቅማል ይላሉ።
በዋናነት የማስወገድ አሠራሩ በትኩረት እንዲሠራ ባለሙያዎችን ማፍራት ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፤ ከግዢ ጋር ተያይዞ የወጣው አሠራር ተጠናክሮ ቢቀጥል እና በኦዲት ላይ ሲስተሙ ቢዘረጋ ክፍተቱ ይሞላል ሲሉ አስረድተዋል።
የመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ አስማረ ይገዙ በበኩላቸው፤ ጥያቄው ተገቢ እና ትክክለኛ ነው። ይሁን እንጂ ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት ያገለገሉ ንብረቶችን እና መኪኖች ከማስወገድ ጋር ብቻ የተያያዘ በመሆኑ የኬሚካል አወጋገድ በተመለከተ፤ በጉዳዩ ላይ ዕውቀት እና ጥናት ተደርጎ በመንግሥት በኩል መፍትሔ እንዲሰጠው ይደረጋል ብለዋል።
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም