
ዜና ሀተታ
በወተት ምርቱ የሚታወቀው ሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ከ1986-1996 ዓ.ም ሰበታ ፋርም በሚል መጠሪያ የወተት ላሞች እርባታ ላይ ሲሠራ መቆየቱን ከኢንዱስትሪው ያገኘነው መረጃ ያሳያል። ከ1996 ወዲህ ደግሞ ወደ ወተት ማቀነባበሪያነት ሥራ የገባው ኢንዱስትሪው በአሁኑ ጊዜ በቀን ከ150 ሺህ ሊትር ድረስ ወተትና የወተት ተዋፅኦ የማቀነባበር አቅም እንዳለው በመረጃው ተመላክቷል።
በዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር እና ዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነት ሥርዓትን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም መረጃው ተጠቁሟል። ከኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅትም ዓለም አቀፍ የምግብ ደህንነትና ጥራት እንዲሁም የጥራት ሥራ አመራር እውቅና ሰርተፊኬት በትናንትናው ዕለት አግኝቷል፡፡
በእውቅና መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ እንዳለው መኮንን እንደገለጹት፤ ጥራት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብና ድካም ይጠይቃል። ወቅቱ የሚጠይቀውን ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች አሟልተን ወደ ገበያ መግባት አለብን። አንደኛውና ወሳኙ የተሻለ ጥራት መሆኑን ጠቁመዋል። ሁለተኛው ለሸማቹ ኅብረተሰብ በአነስተኛ ዋጋ ማቅረብ እንዲሁም ሦስተኛው በተባለው ጊዜ ለተባለው ቦታ ማድረስ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በቀደመው ጊዜ የደንበኛን ፍላጎት ማርካት የጥራት መገለጫ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ያለንበት ወቅት ደግሞ ደንበኛው ከሚፈልገው በላይ ማርካትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።ጥራት ዘላቂ መሆን አለበት የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እውቅናው ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይም ሞራል ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጥራት ባህል መሆን እንዳለበት ጠቁመው፤ ጥራትን ባህል ለማድረግ የአመራር ቁርጠኝነት፣ የመንግሥት ድጋፍ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ባለሙያ ትጋት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
መንግሥት በትልቅ ትጋት የጥራትና ተስማሚነት ምዘና ተቋምን ባይገነባ ኖሮ ኢንዱስትሪው ምርቱን በሦስተኛ ወገን ለማስፈተሽ የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ የተለያዩ ብክነቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ አስረድተዋል።
የጥራት መሠረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥት ከ8ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አውጥቶ በምግብና በግብርና ማቀነባበሪያ ብቻ ሳይሆን የትኛውንም ዘርፍ ለመፈተሽ የሚያስችል አቅም ያለው የጥራት መንደር መገንባቱን አስታውሰዋል፡፡
እውቅናው ለአግሮ ኢንዱስትሪው አንድ ርምጃ ወደፊት የሚያራምድ መሆኑንም ጠቁመዋል።የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን ፈርመናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ታሳቢ የምናደርገው የሀገር ውስጡን ንግድ ብቻ ሳይሆን ከ55 የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለንን ውድድር መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ከአንድና ከሁለት ዓመት ባላነሰ ጊዜ ውስጥ የዓለም የንግድ ድርጅት ሙሉ አባል ስለምንሆን በጥራት ተወዳዳሪ መሆን እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አቤል አንበርብር በበኩላቸው፤ የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የአይሶ 22000/2018 እንዲሁም አይሶ 9001/2015ን መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
እውቅናው የሥራውን ውጤታማነት እንደሚያሻሽል፣ የምግብ ደህንነት ችግር አደጋዎችን እንደሚቀንስ፣ ኢንዱስትሪው በሸማቹ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንደሚጨምርና ተአማኒነቱን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።
አግሮ ኢንዱስትሪው ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ስሙን ጠብቆ መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ይመር፤ እንደሀገር በጥራት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ (ስታንዳርድ) መሠረት እየሠራ ነው። የወተትና የወተት ውጤቶችን ማምረት እጅግ ሰፊና ውስብስብ መሆኑን ገልጸው፤ ኢንዱስትሪው ደረጃውን የጠበቀ ቤተ ሙከራ በማቋቋም ጥራቱን የጠበቀ ምርት ተደራሽ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
እውቅናው ለቀጣይ ሥራቸው ብርታት ሆኗቸው ከዚህ የበለጠ ለመሥራት ከወዲሁ ቃል እንደሚገቡም አስታውቀዋል።
ነፃነት አለሙ
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 16 ቀን 2017 ዓ.ም