የስፖርት ምሁራን የዘርፉ ችግሮች እንዲፈቱ ምን አበረከቱ?

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመሥራት መፍትሔዎችን ማመላከት አንዱ ተልዕኳቸው ነው።

የሚያፈሯቸው ምሁራን ሚናም ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል። ከሳይንስ ጋር አልታረቀም ተብሎ የሚወቀሰው ለኢትዮጵያ ስፖርት እድገት መፍትሔ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከዘርፉ ምሁራን ብዙ ይጠበቃል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምሁራን እጥረት የነበረባት ቢሆንም ዛሬ ላይ እውነታው ተቃራኒ ነው። በርካታ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የስፖርት ሳይንስ ምሁራንና ባለሙያዎችን እያፈሩ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ስፖርት ዛሬም ሙሉ በሙሉ ዘርፉ ከሚፈልገው ሳይንስ ጋር ታርቋል የሚባልበት ደረጃ ላይ አይገኝም።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ይሁኑ የሚያፈሯቸው የዘርፉ ምሁራን እንደ ሀገር ስፖርቱ ያለበትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በጥናትና ምርምር በመቅረፍና በሳይንስ እንዲታገዝ በማድረግ ስር-ነቀል ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ተነግሯል። በአደባባይ ያለው እውነታም ከዚህ የራቀ አይደለም። ለዚህ ምክንያት የሆነው ችግር የቱ ጋር ነው? የሚለው ጉዳይም አከራካሪ ሆኖ ይገኛል።

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እንዲሁም በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂ፤ በጥናት የተደገፈ መረጃ ማግኘት ባይቻልም፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የባለሙያዎች ማፍሪያ እንደመሆናቸው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በስፖርቱ ላይ ያላቸው ሚና ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ “ስፖርት በመረጃና በዕውቀት ላይ ተመርኩዞ የሚሠራ እንደመሆኑ፣ በተለይም የትኛውም ስፖርታዊ ስልጠና እንደቀድሞ በልምድ ላይ ብቻ ተመስርቶ ሊሰጥ አይቻልም” የሚሉት ኢንስትራክተር አድማሱ፣ ስለዚህም አትሌቶች የሩጫ ህይወታቸው ሲያበቃ ወደ ትምህርት ተቋማት ተመልሰው በትምህርትና በስልጠና ራሳቸውን በማብቃት በአሰልጣኝነት ዘመናቸው ስፖርቱን በሳይንሳዊ እውቀት ለመደገፍ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ያስረዳሉ።

እንደ ኢንስትራክተር አድማሱ ገለጻ፤ በፕሮጀክቶች፣ ማዕከላት ክለቦችና ሌሎች ስልጠናዎች ላይ አትሌቶችን የሚያፈሩ ባለሙያዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የወጡ ምሁራን እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ይብዛም ይነስም ባለሙያዎቹ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው ለማለት ያስችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በ40 ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ኤፍሬም ከንቲባ በበኩላቸው፤ የስፖርት ሳይንስ ምሁራን መሬት ላይ ወርዶ ችግር ፈቺ መሆን ያለመሆናቸው መጠን ቢለያይም የተለያዩ ጥናቶችን ጨምሮ በዘርፉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። በተለያዩ መድረኮችም ምሁራኑ ለዘርፉ ጠቃሚ ሃሳቦችን ያነሳሉ። ነገር ግን ይህ ብቻውን ግብ ሊሆን አይችልም ይላሉ። እንዲያውም እውነታውና ምሁራኑ ጋር ያለው ሁኔታ እርስ በእርስ የሚደጋገፉ ሆነው እንዳላገኙት ይናገራሉ።

እንደ ዶክተር ኤፍሬም ሃሳብ፣ ዓለም ላይ የሚታየው የስፖርቱ ዘርፍ ለውጦች ሁሉ የሳይንስና የዘርፉ ምሁራን ውጤት ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ስፖርቱ ከሳይንሱና ከምሁራኑ ጋር ተደጋግፎ የሚሄድ ቢሆንም በኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ የማይተገበርበትን ምክንያት በትክክል ለማስቀመጥ አይቻልም። በዚህ ረገድ የሀገሪቱ ስፖርትና የምሁራኑ መንገድ ለየቅል መሆኑን ነው ዶክተር ኤፍሬም የሚሞግቱት። ያም ሆኖ ጥረቶች የሉም ማለት አይችልም። ለዚህም እሳቸውን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ምሁራን የተሳተፉባቸውን ሀገር አቀፍ የስፖርት ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማሳያነት ይጠቅሳሉ። የጥናት ውጤቶቹ ተግባራዊ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ስትራቴጂዎችን በመቀየስ ረገድ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዲሠሩ እየተደረገ ያለው ሙከራ ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ያነሳሉ።

ከዚህ ባለፈ በየጊዜው ስፖርቱን የሚቀላቀሉ የስፖርት ሳይንስ ተማሪዎች የመመረቂያ ጽሑፋቸው ማሟያ ከመሆን ባለፈ ጥልቀት እንዲኖረውና ሀገራዊ ችግሮችን ፈቺ እንዲሆኑ የማድረግ ጉዳይ ላይ ውስንነቶች መኖራቸውን ተመራማሪው አመላክተዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢንስትራክተር አድማሱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካላቸው የተማረ የሰው ኃይል፣ የጥናትና ምርምር ማዕከላት እና የተሟሉ የማዘውተሪያ ስፍራዎች አንጻር መስጠት ያለባቸውን ግልጋሎት በአግባቡ እየሰጡ የስፖርቱን ችግር በተጨባጭ ከመፍታት አኳያ ክፍተት መኖሩን ይስማማሉ። የተቋማቱ የትምህርት ሥርዓትና መሬት ላይ ያለው ክህሎት፣ ዕውቀትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሁኔታ መራራቁንም ያምኑበታል። ይህን ሁኔታ ወደፊት በማስታረቅ በንድፈ ሃሳብ ትምህርት ብቻም ሳይሆን በተጨባጭ የተማሩት መሬት ላይ ወርዶ በተግባር የሚታረቅበትን ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው ይላሉ። ከዚህም በመነሳት ተቋማቱ የትምህርት ሥርዓታቸው ከፍላጎት አንጻር የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ርምጃ መሆን እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡

የመጠቀም አለመጠቀም ጉዳይ እንጂ የዘርፉ ምሁራን ለስፖርቱ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን እንደሚሠሩ የሚናገረው በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ተባባሪ ተመራማሪ ታሪኩ ተመቸ ነው። ምሁራን ሲኖሩ ስፖርት አለ ቢባልም በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን በሚጠበቀው ልክ ምሁራኑ በተግባር የተደገፈ ሥራ እንዳያከናውኑ ሁኔታዎች እንዳልፈቀዱላቸው የሚናገረው ተባባሪ ተመራማሪው፤ ባለሙያዎች ዕውቀትና አቅም ያላቸው ቢሆንም ይህንን አውጥተው ለመጠቀም የሚያስችል ስልጠና እንዳልነበራቸው ያብራራል፡፡

“እንደሀገር የስፖርት ሳይንስ ምሁራንን መጠቀም ካልተቻለ ስፖርቱ የትም አይደርስም” የሚለው ተባባሪ ተመራማሪ፤ ምሁራን ሥራን ወደተግባር የሚቀይሩበትና አቅማቸውን የሚያጎለብት የተሳለጠ የአሠራር ሁኔታ ሊኖር እንደሚገባ ይጠቁማል፡፡ ስፖርቱን የሚመራው አካልም በሥራዎቹ ምሁራኑን ማቀፍ ካልቻለ ምሁራንን ብቻ ማፍራት ከድካም ባለፈ ውጤታማ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም ብሎ ያምናል፡፡ በተግባር ችግር ፈቺ ሊሆኑ የሚችሉ ጥናቶች ሲሠሩም ስትራቴጂ በመንደፍና ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር በመሆን መሬት ላይ የሚወርድበትን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ባይ ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚና ሌሎች ማሰልጠኛ ማዕከላት በአንጻራዊነት ምሁራንን የሚጠቀምባቸው ቢሆንም፤ እንደሀገር ግን በርካታ የምርምር ሥራዎችን ያከናወኑ ምሁራንን በማቅረብ በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን ጥረት መደረግ እንዳለበት ይመክራል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You