“ከለውጡ ወዲህ የኦዲት ተጠያቂነት እየጨመረ መጥቷል” -ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ ዋና ኦዲተር

አዲስ አበባ፡– ከለውጡ ወዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ በኦዲት ግኝት ላይ ተጠያቂነት እየጨመረ መምጣቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ ገለጹ።

ዋና ኦዲተሯ የመሥሪያ ቤቱን የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ዝግጀት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፣ የተጠናቀቀው የ2016 እና 2017 ዓመት ውጤታማ የኦዲት ሥራዎች የተከናወኑበትና ባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ወቅት የተቀመጡትን የትኩረት አቅጣጫዎችንና ተቋማዊ እቅዶችን ከእቅድ በላይ በመፈጸም ስኬት የተመዘገበበት ነው።

የተገመገመው የሥራ ክንውን ከመጋቢት አንድ 2016 እስከ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም ያለው መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ መሠረት፣ በበጀት ዓመቱ 169 የፋይናንስ አጠቃቀም ኦዲት ለማድረግ ታቅዶ፣ በ163 ተቋማት ላይ የኦዲት ሥራ መሠራቱን ጠቁመዋል። በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት በስድስት ተቋማት ላይ ኦዲት አለመሠራቱንም ጠቅሰዋል።

በክዋኔ ኦዲት 32 አዳዲስና ስምንት የክትትል ኦዲቶችን በማከናወን ሙሉ እቅዱን መፈፀም መቻሉንም አመልክተዋል። በጸጥታ ችግር ምክንያት ባለፈው ዓመት ያልተካተቱት መቀሌ፣ አዲግራት፣ ወሎ፣ ጐንደርና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች በኦዲት ተካተዋል። በዚህ ዓመት አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ተቋማት ተካተዋል።

እንጂባራ፣ ደብረማርቆስ፣ መቅደላ አምባና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች በእቅዱ መሠረት ኦዲት እንዳልተደረጉ የጠቆሙት ዋና ኦዲተሯ፣ በኦዲት ግኝት መሠረት ክፍተት ለታየባቸው ተቋማት የማስጠንቀቂያ፣ የገንዘብ ቅጣት እና አስተዳደራዊ ርምጃ ተወስዷል።

‹‹ተጠያቂነት ሲባል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቻ የሚጠየቅ ሳይሆን በተቋማት ጭምር የሚወሰዱ ርምጃዎች አሉ። የተቋሙ ዋና ዓላማ ለተቋማት የሚበጀተው በጀት ለታለመለት ዓላማ በትክክል መዋሉን ማረጋገጥ ነው›› ብለዋል። በወኪል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በኩል እንዲከናወኑ እቅድ ከተያዘባቸው 392 የድጋፍና ድጐማ ሂሳብ ኦዲቶች መካከል 377 ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል።

‹‹በልዩ ኦዲት፣ በአካባቢ ኦዲት፣ በጾታ ኦዲት እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት አበረታች የእቅድ አፈጻጸሞች ተመዝግበዋል›› ያሉት ዋና ኦዲተሯ፣ የመሥሪያ ቤቱ ተቋማዊ የኦዲት ተልእኮ ከተቋማት አልፎ ሀገራዊ የተጠያቂነት እና የግልጽነት አሠራር እንዲሰፍን እያስቻለ እንደሆነም ገልፀዋል። ተቋሙ እያከናወነ ያለው ሥራ ተጠያቂነትነና ግልጽነት ከምንጊዜምው በተሻለ ሁኔታ በአስተማማኝነት እንዲሰፍኑ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቀርበው የኦዲት ሪፖርት ተጠያቂነትና የሕግ ማስከበር ሥራ በተጨባጭም የማስተካከያ ርምጃዎች እየታዩ መሆኑን ወይዘሮ መሠረት ገልጸዋል።

‹‹የኦዲት ሠራተኛ ዛሬ ተቀጥሮ ነገ ብቁ አይሆንም›› ያሉት ዋና ኦዲተሯ፣ ኦዲተሮች ተቀጥረው ሲሰሩ አበልና ደሞዝ ዝቅተኛ በመሆኑ ከሥራ የሚለቁበት ሁኔታ ለተቋሙ ፈተና ነው። ችግሩን መንግሥት ተገንዝቦ ምላሽ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ የኦዲት ተጠያቂነት እየተረጋገጠና እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ወይዘሮ መሠረት፣ የሕዝብና የመንግሥት በጀት ለታሰበው ዓላማ እንዲውል ከፕላን፣ ገንዘብ ሚኒስቴር እና ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሞገስ ተስፋ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You