ድርብ በደል

ወርቂቱ ሸመና ትባላለች :: ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ ገና የ17 ዓመት ታዳጊ ልጅ ነበረች :: ወርቂቱ በዳውሮ ዞን ተርጫ ወረዳ ከሌሎች ሁለት ታናናሽ ወንድሞቿ ጋር እና ከታላቅ ወንድሟ ጋር አብረው ይኖራሉ :: ወላጅ አባታቸውን በልጅነታቸው ያጡት ወርዊቱ እና ወንድሞቿ አቅመ ደካማ ከሆኑ እናቷ ጋር በመሆን አብረው ይኖራሉ ::

ወርቂቱ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እና ፍልቅልቅ እና ተጫዋች የምትባል ስትሆን ፤ በቤት ውስጥ እንዲሁ ብቸኛ ሴት በመሆኗ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የምትሰራው እራሷ ናት :: ምንም እንኳን ፍልቅልቅ እና ደስተኛ ብትሆንም ግን የወላጆቿ ኑሮ ያሳስባታል:: አድጋ የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሳ እናቷን ለመጦር እና ወንድሞቿን ለማስተማር ትፈልጋለች ::

የወርቂቱ ታላቅ ወንድም ታሪኩ የ12ተኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቋል:: ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያልመጣለት በመሆኑ በሰፈር ውስጥ አብዛኛውን ጊዜውን ከጓደኞቹ ጋር እና አንዳንድ ጥቃቅን ሥራዎችን እየሰራ ይውላል :: ነገር ግን የሚሰራበትን ብር በአግባቡ የማይዝ እና ወደቤት ይዞ የማይገባ በመሆኑ ከወርቂቱ ጋር በተደጋጋሚ በዚህ ጉዳይ ይጨቃጨቃሉ :: እናትም ልጄን እንዳይመታብኝ በማለት ሁልጊዜ ለማስታረቅ በሁለቱ መሀል ይገባሉ ::

የእናቷ ደካማ መሆን የሚያሳስባት ወርቂቱ እናታቸው የሚሸጡትን አነስተኛ የጉሊት ሥራ በዛው በሰፈር ውስጥ በምትገኝ አንድ የመንገድ ጥርጊያ ላይ ቁጭ ብላ በመሸጥ እናቷ እንዲያርፉ በማድረግ ሥራውን ለማሳደግ ትሞክራለች :: እናቷ ወይዘሮ አይናለም የልጆቻቸውን መጎዳት እና ማጣት ላለማየት ቤታቸውን ለማሟላት በብዙ መንገድ የሚጥሩ ሲሆን ነገር ግን ልጃቸው ብቻዋን ሆና በገበያው ሥፍራ ተቀምጣ እንድትሸጥ አይፈልጉም :: ሰው እንዳይተናኮልባቸው ይሰጋሉ ::

 

ወርቂቱ ምንም እንኳን ልጅ ብትሆንም ሥራዎችን ስትሰራ ግን እጅግ ፈጣን እና ሰው አይን ውስጥ በቶሎ የምትገባ ናት :: የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ብታልፍም የቤተሰቦቿ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ተደላድላ ትምህርቷን እንድትማር አላደረጋትም :: በመሆኑም ሥራ ሰርቶ ገንዘብ ወደማምጣቱ ማዘንበል እና ይህንንም ፍንጭ ለእናቷ ማሳየት ጀመረች :: ወይዘሮ አይናለም ይህ ሀሳብ ፍጹም የሚስማሙበት አይደለም:: የልጃቸው የወደፊት እጣፋንታ በዚህ ትንሽ ከተማ ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አይፈልጉም :: የልጃቸውን የነገ ስኬት እና በትምህርት ውጤታማ መሆን አለባቸው የሚለው ሀሳብ ለድርድር የሚያስቀምጡት አይደለም ::

ታዲያ የልጃቸው በትምህርት ወደ ኋላ ማለት ያልጣማቸው እናት አንድ መላ ዘየዱ :: አዲስ አበባ ሄዳ እዛ ጥቂት ጊዜ ተምራ ሌሎች የተሻሉ ሥራዎችን መስራት እንደምትችል በማመን በዚያ የምትኖር እህታቸውን አሰቡ:: በቅድሚያ ግን ከእህታቸው ጋር ማውራት ነበረባቸው እና ደውለው ያሉበትን ሁኔታ እና ያሳሰባቸውን የልጃቸው ጉዳይ አጫወቷት ::

የወይዘሮ አይናለም እህት በልጅነቷ አዲስ አበባ መትታ መኖር የጀመረች ሲሆን በአሁን ሰዓት የራሷን ቤተሰብ መስርታ እና በአንድ ተቋም ውስጥ ተቀጥራ ትሰራለች :: የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ዓለምጸሀይ ጉዳዩን ከባለቤቷ ጋር ተማክራበት እንደምትወስን ተስፋ ሰጥታት የስልክ ልውውጣቸው አበቃ ::

ወይዘሮ አይናለም የእህታቸው ንግግር ተስፋ ሰጥቷቸዋል:: እህታቸውንም በማመን ለልጃቸው አስቀድመው ጉዳዩን እንድታምንበት የማሳመን ሥራቸውን መስራት ጀመሩ :: ወርቂቱ የተሻለ ቦታ ነው ብላ ስላላሰበች መሄዱን አልጠላችውም :: በከተማው ብዙ ሥራ አለ እንደሚባል ስለምትሰማ ጥሩ ሰርታ ገንዘብ እንደምታገኝ እና እናቷን እና ወንድሞቿን እንደምትረዳ እያሰበች በእናቷ ሀሳብ ተስማምታ የአክስቷ ምላሽ ምን ሊሆን እንደሚችል በማሰብ የተወሰኑ ቀናት እንዲሁም ሳምንታት አለፉ ::

የቁርጥ ቀን

ወላጆች ለልጆቻቸው ምንጊዜም ቢሆን የተሻለ ሕይወት መመኘታቸው አይቀሬ ነው:: ታዲያ ወይዘሮ አይናለም አንድ ሴት ልጃቸው ከሥራቸው ተለይታ ልትሄድ መሆኑ በፍጹም የሚዋጥላቸው ጉዳይ አልሆነም:: ነገር ግን ግድ ነውና አደራውን ለእናታቸው ልጅ ለእህታቸው አደራ ሰጥተው የእናትነታቸውን መክረው ሸኟት :: ወርቂቱ ብዙ መልካም ነገሮችን ተስፋ አድርጋ አብራት ወደ አዲስ አበባ እንድትሄድ አደራ ከሰጠቻት ሴት ጋር ጉዟቸውን አደረጉ ::

ከረጅም ጉዞ በኋላ አዲስ አበባ ሲገቡ ምንም እንኳ ስልክ ባይኖራትም ከጎኗ ከተቀመጠችው ሴት ተውሳ እየደወለች በአየር ጤና መነኸርያ ስትደርስ አክስቷን አገኘቻት :: አክስቷ የደረሰች ነፍሰጡር እንደሆነች ታስታውቃለች :: ወርቂቱ እሷ መሆኗን ከስልኳ ካረጋገጠች በኋላ ሰላም ብላት አብረው ወደ አዲሱ ቤቷ ጉዞ ጀመሩ ::

አዲስ ሕይወት

ወርቂቱ በፍጥነት ከሰዎች ጋር የመግባባት ልምድ ያላት በመሆኗ በሰፈሩ ውስጥ ካሉ የአክስቷ ጎረቤቶችም ሆነ ከአከባቢው ሰው ጋር ለመላመድ ጊዜ አልፈጀባትም :: ድረስ ነፍሰጡር የነበረችው አክስቷ የልጅ እናት ሆናለች፤ የእህቷ ልጅም ቤቱን ቀጥ አድርጋ የምቲዝላት አጋዥ ሆናላታለች:: ወርቂቱ በቤት ውስጥ ያሉ ሥራዎችን መስራት ላይ ቅሬታ የሌላት ቢሆንም ነገር ግን የተሻለ ትምህርት አስባ ብትመጣም እንዳሰበችው ግን አልሆነላትም :: ምክንያቱም የመጣችበት ወቅት ትምህርት የተጀመረበት ሰዓት በመሆኑ አክስቷ ዘግይተሻል በሚል ለአንድ ዓመት ያክል የማታ ትምህርት እንድትገባ አደረገቻት :: ይህ ወርቂቱ ቅር የተሰኘችበት ጉዳይ ነው :: ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ትምህርት አይኖርም ከትምህርት ቤት የምትቀርባቸው ጊዜያትም እየበዛ መምጣቱ ቅር አሰኝቷታል:: ወርቂቱ የማታ ተማሪ በመሆኗ አብዛኛውን ጊዜ ትምህርት ቤት ልትሄድ ካልሆነ በስተቀር ከቤት እምብዛም አትወጣም:: ታዲያ በትምህርትቤት ያፈራቻቸው የራሷ ጓደኞች አሏት ::

በቶሎ አይን ውስጥ የምትገባ በመሆኗም ወደድኩሽ የሚሏት ጎረምሶች መብዛት ጀምረዋል :: ከሁሉም ግን ከምትማርበት ትምህርትቤት አጠገብ ያለው የጋራዥ ሰራተኛ ከድር ወርቂቱ የምትግባባው እና ከሌሎቹ በተለየ የምትቀርበው ነው:: እሷም እንደወደዳት ካወቀች በኋላ የፍቅር ጥያቄውን የተቀበለችው ትመስላለች ፤ ትምህርት በምትሄድባቸው ቀናት ሁልጊዜም ቀድማ ወጥታ ከከድር ጋር ጥቂት ማውራትን ትፈልጋለች ::

ግንኙነታቸው ከከድር ጋር ጥሩ ቢሆንም ነገር ግን ፍቅረኛዋ አንድ ባህሪ አለበት :: አብረዋት ከሚማሩ ወንዶች ጋር ሲያያትም ሆነ ስትስቅ ከተመለከታት ከየት መጣ የማይባል ንዴት ሁለመናው ይቆጣጠረዋል:: ብዙውን ጊዜ ልታስረዳው ብትሞክርም ንዴቱን መቆጣጠር የማይችል በመሆኑ ከአንዴም ሁለት ጊዜ በሰዎች ፊት መትቷት ያውቃል ::

በቤት ውስጥ በጉዳዩ ጥርጣሬ ያደረባት አክስቷ ግንኙነቱን እንድትተው ካልሆነ ግን ለእናቷ የምትነግራት መሆኑን አስጠንቅቃታለች:: ወርቂቱ ይህንን ሀሳብ ትስማማበታለች ነገር ግን ደግሞ ጓደኛዋ ከድርን ትፈራዋለች :: ፈራተባ እያለችም ቢሆን የንዴት ተግባሩን እንዲያቆም ብትነግረውም ሊያቆም ባለመቻሉ አክስቷ ባለቻት ሀሳብ በመስማማት የአንደኛ መንፈቅ ዓመት የትምህርት ዘመን ማብቂያ ላይ ፈተና ውጤቷን ለመውሰድ በምትሄድበት ወቅት ግንኙነቱ እንዲቀጥል እንደማትፈልግ በመናገር ወደቤቷ ተመለሰች:: ጊዜው የእረፍት በመሆኑ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ከቤት

አትወጣም:: በሰላሙ ጊዜ ከትምህርትቤት ስትወጣ ቤቷ አቅራቢያ ይሸኛት የነበረው ከድር አልፎ አልፎ እየመጣ ወርቂቱ እቃ ለመግዛት በምትወጣበት ጊዜ እየጠበቀ ይዝትባታል:: ወርቂቱ ይህንን ከልብ አልወሰደችውም፤ ለሌላ ሰውም አልተናገረችም ::

ያልታሰበ ቀን

የትምህርት ቤት የሁለት ሳምንት እረፍት አብቅቶ የመጀመርያ መንፈቅ ዓመት የካርድ ውጤቷን ወስዳ ወደቤቷ በምትመለስበት ወቅት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሰፈራ ቀርሳ ቢላ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ብቻዋን ስትመጣ ሲያገኛት ‹‹ከእኔ ጋር ያለሽን የፍቅር ግንኙነት እንዴት አልፈልግም ትያለሽ›› በማለት መንገድ ላይ ጠብቆ አንገቷን አንቆ በመያዝ በአካባቢው ወደሚገኝ ሰዋራ እና ጸጥ ያለ ስፍራ ወሰዳት:: ምላሽ ለመስጠት እና ላለመሄድ ብትታገለውም በለበሰችው ቀሚስ ልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ ድንገት ከወገቧ ላይ ፈቶ አንገትዋን አንቆ መሬት ላይ በመጣል በወደቀችበት የግብረ-ስጋ ግንኙነት ሊፈጽምባት ሲል ወርቂቱ ያልገመተችው ነገር በመሆኑ በጩኸት ሰዎች እንዲደርሱላት መማጸን ጀመረች :: ድምጽ ስታሰማ ንዴቱን መቆጣጠር የተሳነው ይህ ጨካኝ ሰውም በድጋሚ በልብስ ማሰሪያው ጨርቅ አንገቷን አጥብቆ በመያዝና እራስዋን እንዳትከላከል በማድረግ የግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈጸመባት እና አንገቷን በእጅ እና በልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ በማነቅ ሕይወቷ እንዲያልፍ አደረገ:: ወርቂቱም ሆነች ተስፋዋ የእናቷም ሕልም እና የልጃቸው ነገር በአንድ አረመኔ ጭካኔያዊ ተግባር በዚያ ሰዋራ ቦታ አለፈ ::

የወንጀሉ ዝርዝር

እንደወጣች የቀረችውን የ17 ዓመቷን ወርቂቱ ጉዳይ መረጃ የደረሰው ፖሊስ ጉዳዩን ተጠርጣሪውን ከአክስቷ ባገኘው መረጃ መሰረት እና በቦታው የሰው ሕይወት አጥፍቶ ሊያመልጥ ሲል በድንገት እማኝ በነበሩ ሰዎች አማካኝነተ በቁጥጥር ስር አውሎታል ::

ከድር ዩሱፍ የተባለ ተከሳሽ በጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡30 ሰዓት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሰፈራ ቀርሳ ቢላ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የ17 ዓመት የሆነችውን የግል ተበዳይ ከእኔ ጋር በፍቅር ጓደኝነት ለመቀጠል ፈቃደኛ አልሆነችም በሚል ምክንያት መንገድ ላይ ጠብቆ አንገቷን አንቆ በመያዝ በአካባቢው ወደሚገኝ ካባ በሚወስዳት ጊዜ ላለመሄድ ስትታገለው በለበሰችው ልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ አንገትዋን አንቆ መሬት ላይ በመጣል በወደቀችበት የግብረ-ስጋ ግንኙነት ሊፈጽምባት ሲል የግል ተበዳይ ጩኸት ስታሰማ በድጋሚ በልብስ ማሰሪያው ጨርቅ አንገቷን አጥብቆ በመያዝና እራስዋን እንዳትከላከል በማድረግ የግብረ-ስጋ ግንኙነት የፈጸመባት እና አንገቷን በእጅ እና በልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ በማነቅ ሕይወቷ እንዲያልፍ በማድረጉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶበት በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወንጀል ሕግ አንቀጽ 620 (2)(ሀ) እና (3) መሰረት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲያደርግ ቆይቷል ::

በክርክሩ ሂደትም በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲያደርግ ቆይቶ የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ እንደሌለው በመግለጹ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ አስገድዶ በመድፈር እና በሰው መግደል ወንጀል የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You