“ተጠያቂነትን ከኋላ ኪስ በማድረግ የምንሠራው ሥራ ለሀገር አደጋ ነው”-የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- በፍትህ ሥርዓቱ ተጠያቂነትን ከኋላ ኪስ በማድረግ ነፃነትን ብቻ በማውለብለብ የሚሠራ ሥራ ለሀገር አደጋ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ  ኤርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር) አስታወቁ። ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ የሕዝቡን የፍትሕ ጥማት ለማርካት እና የሕግ የበላይነትን ለመረጋገጥ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመለከቱ።

ኤርሚያስ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፤ በፍትህ ሥርዓቱ በተለይም ዳኞች ተጠያቂነትን በመተው ነፃነት ላይ ብቻ አትኩረው የሚሰጡት ፍትህ ለሀገር አደጋ በመሆኑ ቀጣይነት እንዳይኖረው የሪፎርም ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የሕዝቡን የፍትሕ ጥማት ለማርካት እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያመለከቱት ሚኒስትሩ ፤ ሪፎርሙ ለሀገረ-መንግሥት ቀጣይነት ፤ ለልማት ፤ ለሕዝቦች አብሮነት ፤ መዋቅራዊ በደል እንዳይኖር ከማድረግ አንፃር የሚሠራ እንደሆነ አመልክተዋል። ፍትህ በሌለበት ልማትን ማስቀጠል የማይቻል መሆኑን ጠቁመዋል።

አንዳንድ ቦታዎች ላይ ነፃነት በዝቶ አጉራዘለልነት የሚታይበት ሁኔታ እንደነበር ጠቁመው ፤ እጅግ አማራሪ የሆኑ ዳኝነትን በገንዘብ ለመሸጥ የሚደረጉ ሙከራዎች እንደነበሩ አስታውቀዋል። ይህ ማለት ግን መዋቅራዊ የሆነ ችግር አለ ማለት እንዳልሆነም አመልክተዋል።

ሕገ-መንግሥቱ ተጠያቂነት ሊሰፍን እንደሚገባ የሚደነግግ በመሆኑ ፤ ዳኞችን የማጥራት ሥራ እየተሠራ ነው። ይህም ሲባል ሙያዊ ብቃታቸውን፤ ሥነ-ምግባራቸውና ገቢያቸውንም ጭምር የሚፈትሽ ሥራ ማለት ነው ብለዋል።

እንደሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/ 2021 በማውጣት የዳኝነት ሥርዓቱ ገለልተኛ ተዓማኒ ፣ ሕግን መሠረት አድርጎ ብቻ እንዲሠራ ይበልጡንም ተቋማዊና የፋይናንስ ነፃነቱ ተጠብቆ እንዲሠራ ለማድረግ ተችሏል።

በፍትህ አካላት እና በፍርድ ቤቶች መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር በፍትሕ ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት የፍትሕ ሚኒስትሩ፣ የዳኝነት አካሉ እንደ ፍትህ አካሉ የራሱን የትራንስፎርሜሽን እቅድ አውጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በፍትህ ዘርፉ ሕዝብ ከፍተኛ ሁኔታ ይማረርባቸው የነበሩ ችግሮችን በመሠረታዊነት ለመፍታት አሳሪ የነበሩ፣ የዜጎችን ሠብዓዊ መብት የሚጥሱ ሕጎችን የማሻሻልና የፍትህ ተቋማትን አቅም በማጠናከር የሕዝብ ጥያቄ የነበሩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ማሻሻያ ከተደረገባቸው ሕጎች መካከል በዋናነት የዜጎች መብትና ነፃነት ላይ አሉታዊ ተጥዕኖ ያሳድር የነበረው የፀረ ሽብር አዋጁ ለአብነት ተጠቃሽ መሆኑን አስታውሰው፤ የሕግ ማሻሻያ ሥራዎች በተቋማት ግንባታ ካልዳበሩ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ስለማይቻል፣ የተቋም ግንባታና ሪፎርም ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን እቅድ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ፍኖተ ካርታው ከፀደቀበት እለት ጀምሮ የተሻሻሉትን ሕጎች በአግባቡ በመተግበር፤ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ፍትሕን ለማስፈን፤ የህብረተሰቡን የፍትሕ ጥያቄ በዘላቂነት በመመለስ የፍትህ አገልግሎቱን ቀልጣፋ ፣ ውጤታማ እና ተአማኒ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

‹በሶስት ዓመት የፍትህ ዘርፉ ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሠረት የባለሙያውን ብቃትና ሥነምግባር ለማሳደግና የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን አመልክተው ፤ በተለይ ሥነ ምግባርና አመለካከት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል።

በቅድሚያ ለውጥ ማምጣት ያስችል ዘንድ በፍኖተ ካርታው የተካተቱ ባለሙያዎችንና አመራሮችን ለማጥራት የሚያስችል የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ኤርሚያስ (ዶ/ር) አመልክተዋል።

ኤርሚያስ (ዶ/ር)፤ ከለውጡ በፊት ዳኞች የሚሾሙበት ሁኔታ በአብዛኛው በፖለቲካ ተፅዕኖ እንደነበር አስታውሰው፤ በሪፎርሙ የዳኞች ሹመት፣ ምልመላ፤ ዝውውር ሥርዓት ባለው መልኩ ለመምራት ይቻል ዘንድ በአዋጅ ደረጃ ፀድቆ እንዲተገበር መደረጉን ጠቁመዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You