በቱሪዝሙ ዘርፍ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ ይገባል

አዲስ አበባ፡– የአዲስ አበባ ከተማ በቱሪዝሙ ዘርፍ ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ እንደሚገባ የከተማዋ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አዲስ አበባ በቱሪዝሙ ዘርፍ ያላትን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለይም የሆቴል እና መሰል አገልግሎቶችን ማሳደግ ይገባል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሆነ ከከተማዋ ውጭ የሚገኙ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች የመሰረተ ልማት እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ በሚጠበቀው መጠን እያደገ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ማህበሩም ቀደም ብለው ሥራ ለጀመሩት የጎደላቸውን በመለየት ማሟላት የሚችሉበትን መንገድ የማሳወቅ እንዲሁም አዲስ ለሚሰማሩትም የማማከር ሥራ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ አሸናፊ ገለጻ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ መስህቦች የሚገኙባት እና የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ እንደመሆኗ በከተማዋ የሚገኙ ባህላዊና ዘመናዊ ሆቴልና ሬስቶራንቶች ከተማዋን የሚመጥን አገልግሎትና መሰረተ ልማት ማሟላት አለባቸው፡፡

በመሆኑም ከትላልቅ ሆቴሎች ባለፈ በአብዛኛው የውጭ ጎብኚዎችና የሀገር ውስጥ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚያገኙባቸው መደበኛ ካፌና ሬስቶራንቶች ድረስ የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶችን ማሟላትና የአገልግሎት አሰጣጥ ማሳደግ ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአብዛኛው በከተማው በሚገኙ ሆቴሎች የእሳት አደጋ መውጫ የማያሟሉና የደንብ ልብስ አለባበስ ሥርዓት የሌላቸው መሆኑን አንስተው፤ ከመስተንግዶ ሠራተኞች የደንብ ልብስ አለባበስ ጀምሮ የሚጠቀሙት ቋንቋ እና መስተንግዶ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

እንዲሁም የእሳት አደጋ መውጫ፣ የመጸዳጃ ቤቶች ጥራት፣ የመኝታ እና ምግብ መስተንግዶዎች ወጥ እና ዓለም አቀፍ መስፈርት የሚያሟሉ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በከተማው ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥና መሰረተ ልማት በማሟላት ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ በመስጠት የከተማዋን ገጽታ መገንባትና ጎብኚዎች የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ ያደርጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ማህበሩ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ወደትልቅ ደረጃ ለማድረስ ዓላማ ይዞ ከተቋቋመ አንድ ዓመት ከአምስት ወር ጊዜ ብቻ ቢሆነውም ብዙ ተግባራትን ያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ከ500 በላይ አባላትን በማፍራት የባለሙያዎች ስልጠና፣ የሆቴልና ሬስቶራንቶች የገበያ ላይ ስልጠናና የማማከር ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አቶ አሸናፊ አስታውቀዋል፡፡

ማህሌት ብዙነህ

አዲስ ዘመን  ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You