ዲላ:- የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት በጌዲኦ ዞን ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ለሕዝብ ቤተ መጽሐፍትና ለማረሚያ ተቋም ከሦስት ሺህ 800 በላይ መጽሐፍትን አበርክቷል።
አገልግሎቱ መጽሐፍቱን ያበረከተው “የንባብ ባሕል ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ሀሳብ በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማና ይርጋጨፌ እየተካሄደ ባለው የንባብ ሳምንት ሲሆን በዚህም የንባብ ክበባት ምሥረታ መድረክ ተካሂዷል።
የተበረከተው የመጽሐፍ ስጦታው ወደ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መሆኑን ተገልጾ፤ ለዲላ ማረሚያ ተቋም ብቻ ወደ ሁለት መቶ የሚጠጋ መጽሐፍት ተበርክቷል። ይህም 70 ሺህ ብር የሚያወጡ መሆኑን በወቅቱ ተገልጿል።
የመጽሐፍት ስጦታውን ያበረከቱት የአገልግሎቱ የአብያተ መጽሐፍትና መረጃ ሃብቶች አስተዳደር መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ስለሺ ሽፈራው ናቸው።
የዲላ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ትዕግስት ሮቤ ለተቋሙ ውስጥ ለሚገኙ ታራሚዎች የሚሆን መጽሐፍትን በሥጦታ ያበረከቱትን አካላት አመስግነው፤ ታራሚዎች በተቋሙ ቆይታቸው የማንበብ ባሕላቸውን እንዲያዳብሩና እውቀትን እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባተ ካሠው የንባብ ሳምንት በዲላ፣ በይርጋጨፌ እና አካባቢው መዘጋጀቱ የንባብ ባሕልን እንዲዳብር ብሎም የንባብ መጽሐፍትን የማግኘት እና አማራጮችን የሚያሰፋ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት አገልግሎት ከጌዲኦ ዞን ትምህርት መምሪያ እና ዲላ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ በተዘጋጀው ሳምንታዊ የንባብ ሳምንት አንዱ አካል ነው።
በዚህም በዲላ ከተማ የንባብ ክበባት የተመሠረቱ ሲሆን በይርጋጨፌ ደግሞ ዛሬ ይመሠረታል ተብሏል። ይህም ተማሪዎች እውቀት እና ጥልቅ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደርጋል ነው የተባለው።
በንባብ ሳምንቱ የንባብ ክበባት ምንነት፣ አደረጃጀትና ተግባራት እና ለንባብ ባሕል መዳበር ያላቸው ጠቀሜታ ላይ እና ለንባብ ባሕል መዳበር የትምህርት ቤቶች እና የቤተሰብ ሚና ላይ ገለፃ የተደረገ ሲሆን በንባብ ላይ አነቃቂ ንግግር እንዲሁም የደራሲዎች ተሞክሮ ቀርቧል፡፡
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም