ለሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት

ኢትዮጵያ ባከናወነቻቸው በርካታ የልማት ሥራዎችና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ፈጣንና ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች፡፡ በአስር ዓመት የልማት ዕቅዱ (2013 እስከ 2022 ዓ.ም) ላይ እንደተገለጸው ከ2012 ዓ.ም በፊት የነበረው ተከታታይ እድገት ለዓመታት የዋጋ ግሽበት ያስከተለ ሲሆን፤ ዘላቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል በተፈለገው መጠን በቋሚነት አልፈጠረም። ወጪውም በከፍተኛ ብድር እና እርዳታ የተሸፈነ ስለነበር ከፍተኛ የብድር ጫና ፈጥሯል።

እንዲሁም የሸቀጦች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ሲታይ ከተወሰኑ የግብርና ምርቶች አቅርቦት ተላቅቆ፤ በአይነትና በጥራት በተሻለ መልኩ ምርቶችን በማብዛት ቀጣይና

አስተማማኝ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት ተስኖታል። የማህበራዊ አገልግሎቶችና የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችም ከፍተኛ የጥራትና ፍትሐዊነት ጉድለት እንዳለባቸው በእቅዱ ላይ ሰፍሯል።

እነዚህን ህጸጾች በማረም ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚያራምድ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ (2013 እስከ 2022 ዓ.ም) መዘጋጀቱ በሰነዱ ተጠቅሷል። ኢፕድ ያናገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም ፍትሐዊ የሆነ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የመፍትሄ አማራጭ ሃሳቦችን እና ማህበራዊ ፍላጎትን ለማሟላት የሚያስችሉ እሳቤዎችን ይጠቁማሉ።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ከ200ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ፤ እንደ ህዳሴው ግድብ፣ ግልገል ጊቤ፣ ኮይሻና ሌሎችም የኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ከ50 በላይ ዩኒቨርሲቲዎችንና በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመገንባት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን ለማሻሻል ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ይገልጻሉ።

እንደ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ገለጻ፤ የግብርና ዘርፉም በዘመናዊ መንገድ እየተተካና በኩታ ገጠም የስንዴ እርሻ አመርቂ ውጤት በመታየት ላይ ይገኛል። ቻይና፣ አሜሪካና ሌሎች ያደጉ ሀገራት ከዛሬ መቶ ዓመታት በፊት ከ50 በመቶ በላይ የነበራቸው የአርሶ አደር ምጣኔ አሁን ሁለት በመቶ እየሆነ ነው። በዚህም ሀገር ከመመገብ አልፈው ወደ ሌሎች ሀገራት በመላክ ላይ ይገኛሉ።

ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት መንግሥት ኢኮኖሚው በምን አይነት መልኩ መንቀሳቀስ እንዳለበት በመረዳት እንዳስፈላጊነቱ በየጊዜው የፖሊሲና የአሠራር ለውጦችን መተግበር፣ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ፣ ሙስናን መግታት፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ የሚጸድቁ ፖሊሲና አሰራሮች መተግበራቸውን መገምገም ይጠበቅበታል። እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አልሚዎች ለሀገርና ለሕዝብ የሚጠበቅባቸውን አበርክቶ እንዲያደርጉ ሚቹ የሥራ ምህዳር መፍጠር አለበት ሲሉ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

በተጨማሪም መንግሥት በየተቋማት የሚሾማቸውን አመራሮች የፓርቲ አባል ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ለማሳደግ ቁርጠኝነት እንዳላቸውም እያረጋገጠ መሆን መቻል አለበት ያሉት ባለሙያው፤ እንዲህ አይነት ለውጦችን ለማምጣት መንግሥት ከሕዝባዊ ድርጅቶች፣ ከሙያ ማህበራት፣ ከንግድ ምክክር ቤትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅርበት መስራት እንደሚጠበቅበት ይጠቁማሉ።

እንደ ባለሙያው ንግግር፤ የተመድ የልማት ፕሮግራም በየዓመቱ በሚያወጣው ሪፖርት በዜጎች እድገትና ደህንነት ማለትም በጤና፣ ትምህርት፣ የኑሮ እድሜና ባለው ደስተኛ ህይወት ኢትዮጵያ አነስተኛ አሀዝ እያስመዘገበች ነው። በኢትዮጵያ ጅማሮ ላይ ያለውን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በጤና፣ ትምህርትና በሌሎችም የአገልግሎት ዘርፎች ተግባራዊ በማድረግ ከእርዳታና ተረጂነት መንፈስ በመላቀቅ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ይቻላል።

የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ሰባት በመቶ እያደገ ነው፤ ነገር ግን ጂዲፒ የሀገርን የኢኮኖሚ እድገት ቢያሳይም የዜጎችን የኢኮኖሚያዊ ደህንነት በተጨባጭ አይገልጽም የሚሉት ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር)፤ ሁለቱን ጉዳዮች በማቀራረብ ከድህነት ነጻ የሆነ ሀገር መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።

ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት፣ ዘላቂ ልማት፣ የኑሮ ደረጃ መሻሻል፣ ጥራት ያለው ሕይወት መኖር ከሰው ልጆች ደስተኝነት ጋር የተገናኙ ከመሆናቸው አኳያ እነዚህን ለማሳካትም የገቢ መጨመር፣ የሶሻል ካፒታል መሻሻል፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል መኖር እና የመሳሰሉት ጉዳዮች አስፈላጊ መሆናቸውንም ይጠቁማሉ።

በምግብ እራስን ለመቻልና የጸና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማምጣት ኢትዮጵያ ያላትን የሰው ኃይልና ምቹ የአየር ንብረት እንደመልካም አጋጣሚ መጠቀም ይጠበቅባታል። እንዲሁም አብዛኛው ዜጋ በግብርና ላይ የተሰማራ መሆኑ በንጽጽርም ከሌሎች ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ይልቅ በግብርናው ዘርፍ ላይ ትልቅ ጥቅም እንድታገኝ ያስችላታል የሚሉት ደግሞ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ናቸው።

አቶ ሸዋፈራሁ እንደሚናገሩት፤ ግብርና ውጤታማ እንዲሆን የመሬት ፖሊሲን ማሻሻል፣ ዘመናዊ አስተራረስን መከተል፣ በገጠር የግብርና ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር በመመስረት አርሶ አደሩ፣ ባለሀብቱና መንግሥት በአንድ ላይ በሽርክና ያለውን ሀብት በአግባቡ የሚያለሙበት ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል።

እየተከናወኑ የሚገኙ አንዳንድ የልማት ስራዎች አስፈላጊና ጠቃሚ ቢሆኑም፤ እንኳን ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ቅደም ተከተል እንደሚጎድላቸው የሚገልጹት ተንታኙ፤ ኢትዮጵያ ፋታ የማይሰጡ በርካታ ችግሮች አሏት፤ የልማት ሥራዎችም ሆነ የተለያዩ የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ በተጨባጭ ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ባስገባና ቅደም ተከተልን በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት ይላሉ።

በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተመጣጣኝ እድገት ማምጣት ባለመቻሉ የዜጎች ያልተገባ ፍልሰት እየጨመረ መጥቷል፤ ይህን ማስቆም ለነገ የማይባል ተግባር ነው። የምጣኔ ሀብት እሳቤ የተፈጠረው፣ ገደብ አልባውን የሰው ልጅ ፍላጎት በውስን ሀብት በማርካት የዓለምን ሀብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማዳረስ ነው ይላሉ አቶ ሸዋፈራሁ።

እንደ ተንታኙ ገለጻ፤ በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘንድ የኢትዮጵያን ገጽታ የማበላሸት ሁኔታ ይታያል። በቢሊዮኖች ወጥቶባቸው በቱሪዝም መዳረሻነት የተገነቡ በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች ጎብኚዎችን አግኝተው ገቢ እንዲያስገኙ ከተፈለገ አሁን ላይ በዋናነት ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ እጅጉን አስፈላጊ ነው።

አያይዘውም፤ ግብጽ ፒራሚዶቿንና ሻርማልሼክ ከተማን በማስጎብኘት በዓመት እስከ 17 ቢሊዮን ዶላር ታገኛለች፤ እንዲሁም ኬንያና ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ብሄራዊ ፓርኮቻቸውን በማስጎብኘት ገቢ ያገኛሉ። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የሰላምና ደህንነት ችግር ያለባት በመሆኑ ጎብኚዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ አዳጋች ሆኖባታል ነው የሚሉት።

በህዳሴው ግድብ ላይ ትኩረት በማድረግ ከግድቡ በሚገኘው ገቢ የዋጋ ንረትን፣ ሥራ አጥነትን፣ ጫፍ የወጣውን ድህነትና ሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚ መናወጦችን ማርገብ እንደሚቻል የሚናገሩት ተንታኙ፤ ከዚሁ ጎን ለጎን በግብርና፣ ትምህርት፣ ዴሞክራሲ፣ ሰላምና ደህንነት ላይ በመስራት ሁሉን አቀፍ የሆነ ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ።

ይህን ማድረግ ሲቻልም ፍትሐዊ፣ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ የበለጸገች ኢትዮጵያ መፍጠሪያ ጊዜው ቅርብ ይሆናል ሲሉ ምሁራኑ ሃሳባቸውን ሰጥተውናል።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You