ቡና – ከኢኮኖሚ ባሻገር ያለው ማህበራዊ ፋይዳ

ሥፍራው አረንጓዴ ኩታውን ተከናንቧል። የኮረብታዎች እና የሸለቆዎች ልምላሜ የጠቢብ ቄንጠኛ የቀለም ቅብ ውጤቶች መስለው ተሰትረዋል። ተሻግሮ የሚታየው ጥቅጥቅ ያለው የክረምት ደመና መሬቱን ከሰማይ ጋር የተዋሃደ አስመስሎታል።

የወሎ ጭስ፣ ጨሶ ጨሶ ሀገር ምድሩን የሞላው መስሏል። ወሎ ጭሱ ሲታሰብ ቡናው፣ ቡናው ሲታሰብ ሥርዓቱ፣ ሥርዓቱ ሲታሰብ ባህሉ ተሰናስሎ እንደ ሃብል የሚመዘዝበት ሥፍራ ነው።

በተለይ በወሎ እምብርት ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ ውስጥ ቡና ከመጠጥ በላይ ነው። ቡና በወሎ ባህል፣ በረከት እና ትስስር ነው። የወሎ ሕዝብ የቡና ሥነ ሥርዓቱ እንደ ልዩ የአብሮነት ዕሴት ይዞት የቆየ ሲሆን፤ ይህም የሰላም፣ የጤና እና የብልጽግና ምርቃት በአዲስ የተፈላ ቡና መዓዛ ሲሸፈን ያሳያል።

የጉዟችን መዳረሻ በሆነው በዚህ ስፍራ የቡና ትሩፋት ዘርፈ ብዙ ነው። ሥነሥርዓቱና ባህሉ ለትውልዶች ተላልፏል። “ቡና ከመጠጥ በላይ የአንድነት ምልክት መሆኑን ታላላቆቻችን አስተምረውናል፤ እኛም የእነርሱን አርዓያ ተከትለን ባህሉን ጠብቀን እዚህ አድርሰነዋል።” ሲሉ የደቡብ ወሎ ወረባቦ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ካድራ እሸቱ ይናገራሉ።

ወይዘሮ ካድራ እንደሚሉት፤ በዚህ ስፍራ ቡና ሊፈላ ሲል ጽዱ ቦታ ይዘጋጃል። ይህ ደግሞ የቡና ሥርዓት ድባቡ ለበረከትና ለጸሎት እንዲውል ጭምር በማሰብ የሚከወን ነው።

ወይዘሮ ካድራ እንደ ብዙ የወሎ ሴቶች ሁሉ ቡናን እንደ ሰላም፣ አንድነት፣ አብሮነትና በረከት ድልድይ ነው የሚያዩት። ምክንያቱም ደግሞ የቡና ሥርዓቱ የአማራ፣ የኦሮሞ ወይም የትግራይ፣ የሙስሊምም ይሁን የክርስቲያን ሕዝቦችን የሚያገናኝ ነው ይላሉ።

“ወሎ ውስጥ ብዙ ማንነቶች አሉን፤ ነገር ግን ቡና ስንጠጣ አንድ ሰው ነን” ሲሉ በኩራት በተሞላ ድምጽ ይናገራሉ። የወሎ የቡና ሥነ ሥርዓቱ ሀገርን ቤተሰብን፣ ልጆችን፣ አጠቃላይ የወደ ፊት ህይወትን የሚመርቁበት ስለመሆኑ ነው የሚጠቅሱት።

በቅርቡ የደቡብ ወሎ ዞን ሕዝብ ይህንን ለዘመናት የቆየ ባህል ለማስቀጠልና ማህበረሰቡን ለማጠናከር የሚያስችል አዲስ ጉዞ ጀምሯል።

በክልሉ እየተካሄደ ያለውን የችግኝ ተከላ ፕሮጀክት ለመዘገብ በሄድንበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ የቡና ችግኞችን ተከላ ተመልክተናል። እናቶችና ሴት ልጆች እንደዛሬው ሁሉ በቡና ሥርዓቱ ልዩ ምርቃት የነገውንም የደስታ ዘር ለመዝራት ተሰብስበው የቡና ችግኝ ተክለዋል።ሌላኛዋ እናት ወይዘሮ እናኒ ሽፈራው፤ ብዙ ቤተሰቦች እንዳላቸው፤ ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ ከጎረቤት ጋር ተጠራርተው ቡና እንደሚጠጡና የቡና ድባቡም ልዩ እንደሆነ ይገልጻሉ።

ቡና ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እየጨመረ መምጣቱ ባህሉን እንዳያደበዝዘው ስጋት ፈጥሮባቸው እንደነበርና አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ምክንያት የቡና ተከላ መስፋፋቱ ተስፋቸውን ዳግም የጠገነው ስለመሆኑም ይናገራሉ።

የቡና ተክሉ እርሳቸው ነዋሪ በሆኑበት ደቡብ ወሎ ዞን በስፋት እየተተከለ መሆኑን ጠቅሰው፤ “በጥቂት ዓመታት ውስጥ የራሳችንን ቡና ማምረት የምንችለው ለቤተሰባችን ብቻ ሳይሆን ለገበያ ለመሸጥ ጭምር ነው” ብለዋል። ይህ ደግሞ የአካባቢውን የቡና ሥርዓት ባህሉን ጠብቆ እንዲቆይ ብሎም የአብሮነት መንፈስን ለሌላው ለማጋራት አስቻይ ነው ብለዋል።

ወይዘሮ እናኒ የቡና ዛፎችን መትከል ከግብርና ተነሳሽነት ባለፈ ባህሉን መልሶ ለማግኘት እና ህልውናውን ለማረጋገጥ የሚያስችል መንገድ ነው ሲሉ ገልጸዋል። “ይህ ገንዘብ ከማግኘት የበለጠ ነገር ነው። ባህላችንን መጠበቅ እና ለልጆቻችን ለማስተላለፍ ይረዳል” በማለትም ነው የተናገሩት።

ቡና በወሎ ያለው ፋይዳ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ያለፈ ነው። ከማህበረሰቡ የአንድነት ስሜት እና ከሰላም ምኞቱ ጋር በጥልቅ የተሳሰረ መሆኑን ወይዘሮ እናኒ ይጠቅሳሉ። “ቡና ስንጠራራ ለመጠጣት ብቻ ሳይሆን ሰላም እየፈጠርን ነው” በማለት በእያንዳንዱ የቡና ሥርዓት ውስጥ ለጎረቤት፣ ለልጆች እና ሀገር ጸሎት መኖሩን አውስተዋል።

ይህ የምርቃት በረከትም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይድረስ እርፎ መረባ፣ ሀገር አማን ይሁን፣ ልጆች ይደጉልን፣ መንግሥት ይጽናልን፣ የምንዘራውና የምንተክለው ለዘር ይብቃ በሚሉ የመልካም ምኞት ገላጭ ቃላት መመራረቅ የተለመደ ነው ብለዋል።

የቡና ሥነ-ሥርዓት የአስተሳሰብና የአንድነት ጊዜ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አይሻ ኢብራሂም ናቸው። “በወሎ ውስጥ ያለን ልዩነት ቢኖርም ለአብሮነት ሁሌም ዋጋ እንሰጣለን። ቡና አንድ ያደርገናል፤ በዚህም ለወደፊት ሰላም ያለንን ተስፋ እንጋራለን” ሲሉ ገልጸዋል።

የቡና ችግኝ እያደገ በሄደ ቁጥር በወሎ ሕዝብ መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያ እንድትሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ወይዘሮ አይሻ ገልጸዋል። ቡና ካለው ባህላዊ ፋይዳ አንጻር ችግኙን በመትከል ረገድ ሴቶች ያሳዩት ቁርጠኝነትና ጽናት ከምንም በላይ አንድነትን የሚያከብር ማህበረሰብ ጥንካሬን ያሳያል ነው ያሉት።

በወሎ ሴቶች ቡና በመትከል የተስፋ፣ የሰላምና የብልጽግና ዘር እየዘሩ ነው ያሉት ወይዘሮ አይሻ፤ በመጪው ጊዜ ባህሉ ተጠናክሮ ለሀገር አንድነትና ሰላም ተምሳሌት ይሆን ዘንድም ተመኝተዋል።

“አንድ ቀን ልጆቻችን ቡና ሊጠጡ ሲቀመጡ እናቶቻቸው እና አያቶቻቸው በተባረኩ እጆቻቸው እነዚህን ዛፎች እንደተከሉ ያስታውሳሉ” በማለት፤ ይህም ለእነርሱና ለኢትዮጵያ ሰላም የተከፈለ ዋጋ ስለመሆኑም ያውቃሉ ነው ያሉት።

የወሎ የቡና ሥነ ሥርዓት ታሪክ መጠጥ ብቻ አይደለም። የፅናት፣ የአንድነት እና የተስፋ ታሪክ ነው። ማህበረሰቡ በቡና ሥነ ሥርዓቱ እየተካፈለ፣ እያንዳንዱ ጸሎት ሲያደርግ ሀገሩን እያሰበ በመሆኑ ይህ የቡና ዘር በወሎ የበለፀገ አፈር ላይ መብቀሉ የሕዝቡን የአንድነት ታሪኩን ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን እናቶች ገልጸዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መስከረም 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You