አዲስ አበባ፡- ትውልዱ የጋራ ታሪክና ባህላዊ ዕሴቶችን ለአንድነትና ለሁለንተናዊ ዕድገት ማዋል ይጠበቅበታል ሲሉ የታሪክ ምሁሩ አየለ በከሬ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡
በመከላከያ ጦር ኮሌጅ የደህንነት፤ የስትራቴጂክ ዲፓርትመንት ኃላፊና የታሪክ ሙሁር አየለ በከሬ(ፕ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ትውልዱ የጋራ ታሪክን ለሕዝቦች አንድነትና ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ሊያውለው ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ በርካታ የጋራ ማንነት የሚገልጹ ታሪኮች፣ ቅርሶች እንዲሁም የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች አሉ ያሉት ፕሮፌሰር አየለ፤ ይህም ኢትዮጵያ የብዝሃነት ማዕከል መሆኗን የሚያሳይ እንጂ የልዩነት ምንጭ እንደማይሆኑ አስረድተዋል።
ሀገር በአንድነት መጽናቷንና የጋራ መሆኗን ለመረዳት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መዘጋጀት እንደሚገባ አንስተዋል።
ቅርሶች ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ሀብቶች መሆናቸውን አስረድተው፤ ቀደምት አባቶች በአንድነትና በጋራ እሳቤ ርተው ተጋድሎአቸውን የጻፉባቸውን ታሪኮች ጠቀሜታ መረዳት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ከታሪክና ከቅርስ እንዲሁም ከመልካም ባህላዊ እሴቶች በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ለመሆን ታሪኮችና ቅርሶች ለትውልዱ ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥ የመጀመሪያ ሥራ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ፕሮፌሰር አየለ እንዳመለከቱት፤ ታሪኩን መዘከር፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ መስጠት፣ በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ማካተት እንዲሁም በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ መልክ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ማካተት ታሪክን ከባለታሪኩ ለማስተዋወቅ ያግዛል።
የጋራ ትርክቶች እርስ በእርስ መግባባትና መከባበር እንዲሁም መረዳዳት እንዲቻል የሚያግዙ ናቸው ያሉት ምሁሩ፤ በተጨማሪም ታሪክን በትክክል ለማወቅና ለመረዳት መመርመር ከትውልዱ የሚጠበቅ ሆኑንም ነው የጠቆሙት።
በኢትዮጵያ አብዛኛው ታሪኮችና ቅርሶች የጋራና መገለጫዎች ቢሆኑም ሲጻፍ አልያም ሲነገር በወቅቱ በሚኖረው የመልካም አስተዳደር ችግሮችና በሌሎች ምክንያቶች ወደ አንዱ ሊያዘነብል የሚችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የትኛውም አይነት ታሪክም ሆነ ቅርስ የተዛባና አንዱን ወገን ደግፎ ሌላውን የሚያንኳስስ ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል ብለዋል።
በዓድዋ ድል ያደረጉ ቀደምት አባቶች በቋንቋ እንኳን መግባባት ባይችሉም በሃይማኖትና በብሔር አንድ ባይሆኑም ህብረብሔራዊነትን ስላስቀደሙና ለሀገራዊ አንድነት በመዋደቃቸው የማይፋቅ ታሪክ መጻፍ እንደቻሉ ገልጸዋል።
ቅርስን በአግባቡ ለትውልድ ማስተላለፍና የጋራ ታሪክን ማሳወቅ ለትውልድ ግንባታ ያለው ፋይዳ በቀላሉ ሊታይ አይገባም ሲሉ አስረድተዋል።
በመጨረሻም፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነትን በመስበክ በተለይ አሁን ላይ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጋፋት አሰፍስፈው ያሉ የውጭ ኃይሎች በጋራ መመከት እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2016 ዓ.ም