ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የውጪ ምርቶችን በስፋት ለማምረት በያዘችው አቅጣጫ መሠረት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ላይ በትኩረት እየሰራች ነው፤ ይህን ተከትሎም ምርትና ምርታማነቱ እየጨመረ መጥቷል።
ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ዜጎች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ማድረግ ላይም መሥራት ተጀምሯል። ለእዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተጀመረው የሌማት ቱሩፋት መርሀ ግብር በዋናነት ይጠቀሳል። መርሀ ግብሩ በዶሮና እንቁላል፣ በወተት ሀብት ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ በስፋት መሥራት ያስችላል።
መርሀ ግብሩ ሥራ በገባ በጥቂት ጊዜ ውስጥም በተለይ በዶሮና እንቁላል ምርትና ምርታማነት እና ዋጋ ላይ እንዲሁም ገበያ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል። በልማቱ በሚሳተፉ ዜጎች የአመጋገብ ሥርዓትና ገቢ ላይም እንዲሁ ለውጦችን ማሳየት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ የሚያመለክተውም ይህንኑ ነው። በ2014 ዓ.ም 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን እንቁላል የተመረተ ሲሆን፤ ይህ አሀዝ በ2016 ላይ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ደርሷል። ዘንድሮ ለማምረት ታቅዶ የነበረው 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን የነበረ ቢሆ ንም ከእንቁላል ዋጋ ጋር በተያያዘ የእቅዱን ያህል ማም ረት ሳይቻል ቀርቷል ።
በዶሮ ስጋ ምርት ረገድም እንደሀገር እስከ 90 ሺ ቶን ይደርስ የነበረውን የማምረት አቅም ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምርትና ምርታማነት ማሻሻል ላይ በተደረገው ርብርብ በ2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ 205 ሺ ቶን የዶሮ ስጋ ማቅረብ ተችሏል።
ልማቱ እዚህ ለውጥ ላይ የደረሰው ነገሮች ሁሉ አልጋ ባልጋ ሆነውለትም አይደለም። በተለይ ከዶሮና እንቁላል ምርትና ምርታማነት ማደግ ጋር ተያይዞ ገበያ መፈጠር አስፈላጊ ስለመሆኑ ሲጠቆም የነበረው ሁኔታም ይህንኑ ይጠቁማል፤ ምርቱ እየጨመረ ሲመጣ ገበያው ካልተገኘ በምርታማነቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳርፍ ይችላል የሚል ስጋትም በአምራቾቹ በኩል ይሰ ማ ነበር።
የመኖ አቅርቦት እጥረትና ወላጅ ዶሮ እንደ ልብ ማግኘት አለመቻልም ሌሎች የልማቱ ደንቃራ እስከመሆን የደረሱበት ሁኔታ እንደነበረም አምራቾችም፣ ልማቱን የሚመሩ አካላትም ሲገልጹ ቆይተዋል። እነዚህ ችግሮች ልማቱ ከእስከ አሁኑም በላይ ብዙ ርቀት እንዳይጓዝ የሚያደርጉ መሆናቸውን መገመት አይከብድም።
መንግሥት እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ሲሠራ ቆይቷል። ከመኖ አቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዘውን ችግር መፍታት የሚያስችል ሥራ ተሠርቷል። በእዚህም በየክልሉ ከተሞች የዶሮ መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል። በሀዋሳና ቢሾፍቱ ደግሞ በርካታ ማቀነባበሪያዎች ተከፍተዋል። አዳዲስ ፋብሪካዎችን ከመትከል በተጨማሪ ነባሮቹም በሙሉ አቅማቸው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው።
የእነዚህ ማቀነባበሪያዎች በስፋት መከፈት አልሚዎቹ መኖ ለመግዛት ብዙ ርቀት ሲሄዱ የነበረበትን ሁኔታ ያስቀራል፤ በዚህ ጉዞ ወቅት ሊከሰት የሚችለውን ወጪ ታሳቢ በማድረግ በማምረቻ ላይ የሚኖረውን ወጪን ከመጨመር ያወጣዋል።
የቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን በሚፈለገው መጠን ለማግኘትም እንዲሁ መንግሥት የቅድመ ወላጅ ዶሮዎችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ በማስገባት ለአርቢዎች ሲያከፋፍል ቆይቷል፤ ይሁንና ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ ይህም በምርትና ምርታማነትን የማሳደጉ ሥራ በታሰበው ልክ እንዳይሄድ ቀፍድዶ ይዞት እንደነበርም ይገለጻል።
በቅርቡ የሚድሮክ ቢዝነስ ግሩፕና አንድ የውጭ የቅድመ ወላጅ ዶሮ አምራች ኩባንያ በመተባበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የቅድመ ወላጅ ስቶክ ፋርም ገንብቶ ማስመረቁ ይህን ችግር እንደሚፈታ ታምኖበታል።
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንዳመለከተው፤ ይህ ፋብሪካ በአንድ ጊዜ ወደ ስድስት መቶ ሺ ጫጩቶችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል። እያንዳንዳቸው ከሚጥሉት እንቁላል ጋር ሲደመር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶሮዎችን ለማምረት እንዲሁም ይህም ከሀገር ውስጥ ፍላጎት አልፎ ለውጭ ገበያም ለማቅረብ ያስችላል።
ይህም ሌላው በዶሮ ልማቱ ላይ ይታይ የነበረውን ትልቅ ደንቃራ የሚያስወገድና ልማቱን ወደ ፊት ማስፈንጠር ያ ነው። ወላጅ ዶሮዎች ከውጭ ይመጡ የነበረበትን ሁኔታ ያስቀራል። ከዚህ በተጨማሪም ዶሮዎቹን ለውጭ ገበያ ለማቅረብም የሚያስችል እንደመሆኑም ልማቱ ሌላ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኝ ያደርጋል።
በቀጣይ ደግሞ ከገበያ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት መሥራት ያስፈልጋል። አምራቾች በመደበኛው መንገድ ከሚፈጥሩት የገበያ ትስስር በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ ገበያዎች ሊፈጠሩላቸው ይገባል። አግሮ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት አለባቸው። በዶሮ አመጋገብ ባህል ላይ ለውጥ ለማምጣት መሥራትም ያስፈልጋል።
አሁን ባለው የአመጋገብ ባህል ዶሮ እርባታው በዋናነት ማእከል የሚያደርገው ዓመት በዓላትን ብቻ ነው። ይህ አካሄድ ከምግብ ሥርዓት አኳያም ትክክል ነው ተብሎ የሚወሰድ አይደለም። በመሆኑም የሚመለከታቸው የምግብ ሳይንስ ባለሙያዎች ዶሮን በተለያየ መንገድ የመመገብን ፋይዳ አስመልክተው ግንዛቤ ማስጨበጥና የመሳሰሉት ላይ ሊሠሩ ይገባል። ይህ ሲሆን ልማቱም የምግብ ሥርዓቱም ገበያውም ተያይዘው ይጓዛሉ። በምግብ ዋስትናና የምግብ ሥርዓት ላይ የሚከናወኑ ተግባሮችም ይበልጥ ውጤታማ ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 /2016 ዓ.ም