
ዜና ትንታኔ
የፖለቲካ ውዥንብርና አለመረጋጋት በሚታይበት ዓለም ሕግንና ሕገመንግሥታዊ ተቋማትን የማክ በር አስፈላጊነት አያጠያይቅም። ወደብጥብጥ ከተሸጋገሩ ሰላማዊ ተቃውሞዎች እስከ የዴሞክራሲ ተቋማት መሸርሸር፤ ሕግን አለማክበርና ችላ ማለት የሚያስከትለውን መዘዝ አጉልተው ያሳዩ በርካታ ክስተቶች አሉ።
የውጭ ኃይሎች ስውር ደባ ታክሎበት በሰሜን አፍሪካዋ ሊቢያ ሕግን ያለማክበርና ያለማስከበር ያስከተለው ውጥንቅጥ፣ ግብጽን ጨምሮ በተለያዩ የሰሜን አፍሪካ ሀገራትም ያጋጠሙ ሥርዓት አልበኝነቶች ያስከተሏቸው ቀውሶች የሚዘነጉ አይደሉም።
ከ14 ዓመታት በፊት በአይቮሪኮስት ሎራን ባግቦ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአላሳን ዋታራ መሸነፋቸውን አልቀበልም ካሉ በኋላ የተቀሰቀሰውን ብጥብጥና ሕግን አለማክበር ያደረሰውን ሰፊ ጉዳት ዳፋው ለበርካቶች ነበር የተረፈው።
ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ባለማክበር በተለይም በጉልበት ስልጣን ለመያዝ በሚልና በየአካባቢው በሚፈጠሩ በነፍጥ በታገዙ ግጭቶች ምክንያት የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ ጉዳትም ደርሷል።
በዚህ ረግድ ሕግንና ሕገመንግሥዊ ተቋማትን ያለማክበር መዘዙ እስከምን ድረስ ነው፤ ሥርዓት አልበኝነትን በዘላቂነት ማስወገድ ምን ጠቀሜታ አለው? ጠንካራ ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማትን የማቋቋሙ አስፈላጊነት እስከምን ድረስ ነው? በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የዘርፉን ምሁራን አነጋግረናል።
የሕዝብ አመራርና የፖሊሲ ጥናት ምሁር እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዋናነት በተጻፈ ሕግ የምትመራ ሀገር እንደመሆኗ ሕገ-መንግሥቱ በመሠረታዊነት ለሕግ አውጭ፣ ለሕግ አስፈፃሚና ለሕግ ተርጓሚ አካላት ስልጣን የሚሰጥ ሰነድ ነው። ይህም በዜጎችና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ይወስናል።
በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ከሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግሥት መሠረት ሁሉም አካላት የተሰጣቸውን ስልጣን ማክበርም ሆነ ማስከበር እንዳለባቸው አንስተው፤ ከዚህ አንፃር ሁሉም አካላት በተሰጣቸው ስልጣን ልክ ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ ያስረዳሉ።
ከዚህ አንፃር ሦስቱ የመንግሥት አካላት ማለትም ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈፃሚና ሕግ ተርጓሚ የተሰጣቸውን ስልጣንና ኃላፊነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚጠቀሙት ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ነው፤ እነዚህ ተቋማት ሕገ መንግሥቱን መሰረት አድርገው የሚቋቋሙ መሆናቸውን ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና ሌሎችም ተጠቃሽ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት መሆናቸውን ይገልጻሉ፤ የእነዚህ ተቋማት ስልጣንና ተግባር የሚመነጨውም ከሕገ መንግሥቱ መሆኑን ነው የተናገሩት።
እንደ እንዳለ (ዶ/ር) ገለጻ፤ ሕግን አለማክበርም ሆነ ተቋማቱን ሳያከብሩ መንቀሳቀስ እንደሀገር የሚፈጥረው ችግር እስከ መገዳደል ሊያደርስ ይችላል። ሕገ-መንግሥቱ ባልፈቀደ መልኩ የሚንቀሳቀስ ሁሉ ሥርዓት አልበኝነትን ያባብሳል፤ ሕገ መንግሥቱን ከሚያስከብረው አካል ጋር አላስፈላጊ ግጭቶችን ይፈጥራል።
ሕገ-መንግሥቱን ብቻ ሳይሆን መመሪያዎችና ደንቦችን በመጋፋት የሚፈጠሩ ችግሮች ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ግጭቶችን ሊያባብሱ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።
ሕግና ሥርዓት ሲጠፋ የደቦ ፍርድ የሚነግስበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸው፤ አሁን ላይ ሱዳንን ከዚህ ቀደም ደግሞ ሶማሊያና ሶሪያን ብንመለከት ሕገ መንግሥቱን መሰረት ያደረገ ርምጃ ባለመወሰዱ ሀገር የማፍረስ ደረጃ ደርሰዋል ይላሉ።
ከዚህ አንፃር ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማትን አለማክበር የሚያስከትለው ጉዳት ከባድ መሆኑን እያንዳንዱ ዜጋ መረዳት ይገባዋል፤ የሕግ አስፈጻሚ አካላትም ሕግ በሚፈቅደው ልክ ሥርዓት አልበኝነትን ከእንጭጩ በመከላከል የሀገርን ደህንነት በዘላቂነት ማስጠበቅ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ታሪክ በግጭት የተሞላ ነው ያሉት እንዳለ (ዶ/ር)፤ በዚህም በኢኮኖሚና በፖለቲካ ከኢትዮጵያ ኋላ የነበሩት ቻይና እና ደብቡ ኮሪያ አሁን ላይ በዓለም ትልቅ ቦታ ይዘዋል። የፖለቲካል ውይይት ባለመደረጉ የመጣው የሰሜኑ ጦርነት በበኩሉ ወደአልተፈለገ ችግር አስገብቶናል ይላሉ።
በመሆኑም የሠራነውን እንዳናፈርስ ብሎም የዕድገት ጅሟሯችንን ለማጠናከር ሕግ መከበርና ከሥርዓት አልበኝነትን መራቅ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
አብዛኛውን ጊዜ ተጠያቂነትና የግልጸኝነት ጥያቄ የሚነሳው ሕገ መንግሥቱን መሰረት በማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ፍትሐዊ ሆነው የሚያስተላልፉትን ውሳኔ አለማክበር እንዲሁም ሕግን እያወቁም ሆነ ሳያውቁ መጣስ ለተጠያቂነትን እንደሚያጋልጥ አውቆ መንቀሳቀስ ከማንኛውም አካል ይጠበቃል ሲሉ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ክብሯን የሚመጥን ቦታ ላይ እንድትገኝ ሕግና ሕገመንግሥታዊ ተቋማትን ማክበር የመጀመሪያው መስፈርት መሆኑን ገልጸው፤ ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመማር ነግበኔ የሚለውን ብሂል ይዞ ሕግና ሕገመንግሥታዊ አካሄድን ምንጊዜም ማስቀደም እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ሙራዶ አብዶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ሕግ ከማበጀት ባለፈ ጠንካራ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን ይቋቋማሉ።
ሥርዓት እንዲኖርና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ሕገመንግሥታዊ ተቋማት ያስፈልጉናል ብለው ዜጎች ያቋቋሟቸው ተቋማት በመሆናቸው ሥርዓት አልበኝነት እንዳይሰፍን፣ በምርጫና ፖለቲካ፣ በሰብዓዊ መብትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ መንገድ በመምራት እንዲሁም ጥፋቶችን በመቆጣጠር የሚሰሩ ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማትን አክብሮ መሥራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
እንደ ሕግ መምህሩ ገለጻ፤ ዜጎች ለተቋማቱ አስፈላጊውን ሁሉ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፤ አስተዋጽኦው የተሟላ የሚሆነው ደግሞ የሀገሪቷን ብሎም ዓለም አቀፍ ሕግጋትን አክብሮ በሰላም ለመኖር እያንዳንድ ዜጋ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሲወጣ ነው።
የሕግ የበላይነት አልሰፈነም ማለት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውዝግብ በሚነሳበት ወቅት ሰዎች በሥርዓት ከመመራትና ወደ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ከመሄድ ይልቅ እርስ በእርስ ግጭት እንዲፈጥሩ በር የሚከፍት ችግር ነው ያሉት መምህሩ፤ ዜጎች ኃይል በተቀላቀለበት ሁኔታ በራሳቸው ፍርድ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት የሚያደርጉበትን እኩል መንገድ ለመከላከል ሕግ ማክበርና ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማትን ማክበር ካሁኑ በትውልዱ ዘንድ ሊሰርጽ የሚገባው ጉዳይ ነው ይላሉ።
ሥርዓት አልበኝነት የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት እንዲበራከት ከማድረጉም በላይ ጉልበት ያለው ሁሉ እየተነሳ ወንጀል የሚፈጽምበት ሁኔታ ይፈጠራል ያሉት ሙራዶ አብዶ (ዶ/ር)፤ ይህም ቅቡልነት ያላቸው መብቶች እንዲሸረሸሩና ሀገር እንዲበተን ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።
በየመንና በሶማሊያ የተፈጠሩ ሀገር ያፈረሱ ግጭቶችንና የሰላም እጦቶችን አንስተው፤ በኢትዮጵያም ሊፈጠሩ የሚችል የተባባሱ ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል ሕግና ሕገ-መንግሥታዊ ተቋማትን ውሳኔዎች ማክበር ምንጊዜም ችላ ሊባል የማይገባው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ምሁራኑ እንዳስታወቁት፤ ሀገርን ከከፋ ቀውስ ለመከላከል፣ የደቦ ፍርድን ለማስቀረት፣ ፍትሐዊ ፍርድና ሰላማዊ ሕይወትን ለመምራት ሕግና ሕገመንግሥታዊ ተቋማትን አክብሮ መሥራት እንደሚገባ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። ሕግና ሥርዓትን ካለማክበር በመነጨ ግርግር የሰሜንና የምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም የተወሰኑ የአረብ ሀገራት የደረሰባቸውን ውጥንቅጥ በመረዳት ሥርዓት አልበኝነት እንዳይነግስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ማክበር የምንጊዜም ተግባር ሊሆን ይገባል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም