አትሌቲክሳችንን ከህመሙ ማን  ይፈውሰው ይሆን?

ኢትዮጵያ በዓለም ከምትታወቅባቸው መካከል አንዱና ግንባር ቀደሙ የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። ጀግኖች አትሌቶች አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ በሮም፣ በቶኪዮና ሜክሲኮ ኦሎምፒኮች በማራቶን በተከታታይ በማሸነፋቸው እስከ አሁን የኢትዮጵያ ስም በኦሎምፒክ መዝገብ በክብር በወርቅ ተጽፎ ይገኛል።

እንዲሁም በሞስኮ፣ በባርሴሎና፣ በአትላንታ፣ በሲድኒ በአቴንስ፣ በቤጂንግ፣ በለንደን፣ በሪዮና በቶኪዮ አደባባዮች ስመጥር አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ድል ማድረጋቸው የአበበና ማሞ ወልዴን ጀግንነት ደጋግሞ አሳይቶናል። የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከበለጸጉት ሀገራት ሰንደቅ ዓላማ በላይ ከፍ ብላ እንድትውለበለብና መዝሙሯም ከዳር እስከ ዳር የዓለም ሕዝብ ጆሮ እንዲገባ አድርገዋል። ብሔራዊ መዝሙሯም ሲዘመርና ሰንደቅዋ ሲውለበለብ ባለታሪኮቹ አትሌቶች በሀገር ፍቅር ስሜት አንብተዋል።

በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን የድሉ ተካፋይ በመሆን ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በሆታና በጭፈራ ደስታቸውን በአደባባይ ገልፀዋል። የድሉ ባለቤት የሆኑት አትሌቶቻችን፣ አሰልጣኞችን የቡድን መሪዎች ጋር በመሆን ወደ ሀገራቸው በድል ሲመለሱ ወገን በሙሉ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ይፋዊ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት የሚካሄድባቸው ቤተመንግሥትና ስታዲየም አጅበዋቸዋል።

መንግሥታትም በየዘመናቱ በድል ለሚመለሱ ጀግኖች አትሌቶቻችን ሹመትና ሽልማት አበርክቷል። ሕዝቡም በየክልሉ ጥሪ በማድረግ እነዚህን ከአብራኩ የወጡትን ጀግኖች ልጆቹን በክብር ተቀብሎ የተለያዩ ሽልማቶችን አበርክቶላቸዋል። መንግሥታት ከሹመትና ሽልማት ባሻገር የእነዚህ ጀግኖች ስምና የታሪክ ገድል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በስማቸው አደባባይ፣ ስታዲየም፣ አካዳሚዎች፣ ሆስፒታል መንገድና ት/ቤት እንዲሰየም አድርገዋል።

እነዚህ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በማሸነፍ የሀገራችንን ስም በክብር ያስጠሩት አትሌቶቻችን በላባቸውና በደማቸው ያገኙትን ሀብት ዛሬ በሀገራቸው ሥራ ላይ በማዋል ከስፖርቱ ባሻገር በልማት (ኢንቨስትመንት) መስክ በመሰማራት ሀገራቸውን፣ ሕዝባቸውንና መንግሥታቸውን በማገዝ እጥፍ ድርብ ውለታ በመክፈል ላይ ይገኛሉ። ከዚህም ባለፈ በይፋ ባይታወቅም እነሱን የሚተኩ አትሌቶች በያሉበት ሥፍራ በገንዘብ፣ ከቁሳቁስና በሞራል ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በከፈቱት የሥራ መስክም በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ወገኖቻችን የሥራ ዕድል በመክፈት ተሰማርቶ ከራሳቸው አልፎ ለቤተሰቦቻቸው ብሎ ለሀገር ጭምር እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

የዚህ የአትሌቲክስ ስፖርት አካል የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላ አፍሪካ፣ ብሎ በዓለም እንዲታወቅ በር የከፈተውና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የዓለማችን ምርጥ አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በትውልድ ዘንድ ዘለዓለማዊ ስሙን ተክሎ የሚያልፍ ድንቅ ታሪክና ተግባር እየፈጸመ ይገኛል። ይህ ታላቅ ሰው የዚሁ ባለድል አትሌቲክሳችን ውጤት ነው።

የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ እስከ አሁን እንደ ኦሎምፒክ ችቦ የቅብብሎሽና የመተካካት ወቅቶች ነበሩት። የእነ ዋሚ ቢራቱ፣ ባሻዬ ፈለቀ፣ አበበ በቂላ፣ አበበ ዋቅጅራ ዘመን ለእነ ማሞ ወልዴ ዘመን ተሸጋገረ። ከዚያ ወደ እነ ምሩፅ ይፍጠር የአረንጓዴ ጎርፎቹ መሐመድ ከድር፣ ብርሃኑ ግርማ፣ እሸቱ ቱራ፣ ግርማ ወልደ ሃና፣ ከበደ ባልቻ ደረጀ ነዲና ቶለሳ ቆቱ ተላለፈ። እንዲሁም መገርሣ ቱሉ ትዕዛዙ ውብሸት፣ ተክሌ ፈንቲሳ፣ ገብሬ ጉርመ፣ ሁንዴ ጦሬ የመሳሰሉት እያለ ቀጠለ።

ይህ ወርቃማው ዘመን በዚህ ሳያበቃ እነ አበበ መኮንን ወደ ጀቡልቲ፣ ሐጂ ቡልቡላ፣ በቀለ ደበሌ፣ እነ ወልደ ሥላሴ ሚልኬሳ፣ የኃይሌ ገ/ሥላሴ ታላቅ ወንድም ተክዬ ገብረ ሥላሴ መሰሎቹ ተላለፈ። ከዚያ ወደ ጀግኖቹ የዓለምና ኦሎምፒክ ባለ ድሉ ፊጣ ባይሳ፣ ጠና ነገሬ፣ ወርቁ በቂላ፣ ወንድማማቾቹ ሃብቴና ተስፋዬ ጅፋር፣ አሰፋ መዝገቡና ወንድሙ አየለ መዝገቡ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ሐዱሽ አበበና አብርሃም አሰፋ ስምረቱ ዓለማየሁና ሌሎች የወቅቱ ጀግኖች ቀጠለ።

ከዚያም በተሳተፈባቸው የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ሪከርድ ጭምር በመስበር ወደሚታውቀው ጀግናው ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ የማራቶኑ ጀግና ገዛኸኝ አበራና ተስፋዮ ቶላ፣ ማርቆስ ገነቴ፣ ግርማ ቶላና ኃይሉ መኮንን እያለ ከዚህ ትውልድ በትረ ስልጣኑን የድል ባንዲራ የተቀበለው የኦሎምፒክ፣ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና የሀገር አቋራጭ ንጉስ ቀነኒሳ በቀለና ታሪኩ በቀለ ፣ ስለሽ ስህንና እነ ገብረ እግዚአብሔር ገብረማሪያም አሊ አብዶሽ፣ አብዮት አባተ፣ ፀጋዬ ከበደ፣ ኢብራሂም ጀይላን አርበኛው የሪዮ ኦሎምፒክ ጀግና ፈይሳ ሌሊሳ እያለ የዛሬ ትውልድ ደርሷል።

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ታሪክ በወንዶች ብቻ ሳትወሰን ከሀገር አልፎ ለአፍሪካም ጭምር ጀግንነት ሰርተው በክብር ያስጠሩን ድንቅ ሴት የአትሌቲክስ ጀግኖች የፈጠረች ሀገር መሆንዋን በመላው ዓለም የስፖርት መድረክ አስመስክራለች። የሞስኮ ኦሎምፒክ ፈር ቀዳጆቹና ተሳታፊዎቹ ፋንታዬ ሲራጅና ኢትዮጵያ ገብረ እግዚአብሔር፣ እነ ፅጌ ገብረመስቀል፣ ጌጤነሽ ኡርጌ፣ ሉቺያ ይስሀቅ፣ ዘውዴ ኃይለማርያም፣ አየለች ወርቁ፣ ቁጥሬ ዱለቻን የመሳሰሉትን አፍርታለች። ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ በኦሎምፒክ በ10 ሺ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችውን የባርሴሎና ኦሎምፒክ ጀግኒት ደራርቱ ቱሉን ያፈራች ሀገር ናት።

ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ ሴት ጀግኖች አትሌቶች እነ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ የኦሎምፒክ ማራቶን ጀግናዋ ፋጡማ ሮባ፣ ቲኪ ገላናን፣ እልፍነሽ ዓለሙ፣ መስታወት ቱፋ፣ መሪማ ደንቦባና መሬማ ሐሺም፣ ገለቴ ቡርቃን የመሳሰሉትን ከኋላዋ አሰልፋ በየውድድሩ ሜዳዎች ብቅ ስትል በፍቅርና በደስታ ተመልካች ከዳር እስከ ዳር ስታዲየሙን በጭብጨባና በፉጨት ያናውጣል።

አበባዋ ደራርቱ በአትሌቲክስ ስፖርት ፈር ቀዳጅነት ዛሬ መላውን ዓለም በማራቶን በአሥር ሺ፣ በአምስት ሺ፣ በሶስት ሺ መሰናክል፣ በ1500 በመካከለኛ ርቀትና በአጭር ርቀቶች ጭምር የተቆጣጠሩ አፍሪካውያን ሴት ጀግኖች እንደ አሸን መፍለቅ እንዲችሉ የመድረኩ መሪ ተዋናይ ሆና ለዘላለም ስምዋ በታሪክ በክብር እንዲነሳ አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ስፖርት አባት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የአትሌቲክስ ስፖርት በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ የተጫወቱት ሚና ቀላል አልነበረም። አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ንጉሴ ሮባን በአትሌቲክስ ስፖርት የፈጠሩ ታላቅ ሰው ናቸው። አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ደግሞ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ፣ ዶ/ር ይልማ በርታን፣ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱን አበቁ። ከዚያ የብሔራዊ ክለቦች አሰልጣኞች እነ ሻምበል እሸቱ ቱራ፣ መሐመድ ከድር፣ ዮሐንስ መሐመድ፣ ብርሃኑ ግርማ፣ ግርማ ወ/ሃና፣ ካሱ ዓለማየሁ ትዕዛዙ ውብሸት በዚህ ውስጥ ደግ የተለያዩ አትሌቶችን በማደራጀት ያሰለጥኑ የነበሩ ታላቁ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፈር ቀዳጅ ዋሚ ቢራቱን ሳንረሳ እነዚህ እንከን የማይወጣላቸው አሰልጣኞች ተገኙ።

እነሱም ሀገርን የበለጠ ለኩራት ያበቁ ድንቅ አትሌቶች ከማብቃት አልፎ ወጣት አትሌቶችን ከሥር በመተካት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ናቸው። ለአብነት የአትላንታ፣ ሲዲኒ፣ አቴንስ፣ ቤጂንግ፣ ለንደን ኦሊምፒክ እና የዓለም አሌቲክስ ሻምፒዮና በተለይም በሔልሲንኪና ኤድመንተን ሻምፒዮናዎች የዶ/ር ወልደመስቀልና ኮስትሬና የሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ውጤት ቢሆንም የክለብ አሰልጣኞች ሚናና አጋርነትም በቀላሉ የሚታይ አልነበረም።

ጀግኖቹ የኦሊምፒክ፣ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናና ሀገር አቋራጭ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች እነ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ቀነኒሳና ጥሩዬ የመሳሰሉ ውለታ ሳይረሳ ወደ የዛሬዎቹ ታሪክ ሠሪዎች ታምራት ቶላ፣ ትዕግሥት አሰፋ፣ በሪሁ አረጋዊና ሲንቦ ዓለማየሁ ለሀገር የሰሩት ውለታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ከ1956 የፈረንጆች አቆጣጠር የጀመረ ነበር። ኢትዮጵያ በመጀመሪያ ተሳትፎዋ እንደተባለው በተሳትፎ ብቻ ነበር የተመለሰችው። ወርቅ፣ ብርም፣ ነሐስም አልተገኘም። ነገር ግን ከሮም እስከ ፓሪስ በ14 ኦሎምፒኮች አንድም ጊዜ ከሜዳሊያ ውጪ ሆና አታውቅም፣ 24 ወርቅ፣ 15 ብር እና 23 ነሐስ በድምሩ 62 ሜዳሊያ አግኝታለች።

እውነታው ይሄ ቢሆንም ታዲያ ምን ያደርጋል ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከተው የመተካካቱ ጉዳይ ያበቃ ይመስላል። ከአበበ በቂላ ጀምሮ እስከ ታምራት ቶላ ያለው ትውልድ አደራ ጠብቆ እዚህ አድርሶናል። ከንጉሴ ሮባ ጀምሮ ዘመናዊ ስልጠናን በሚገባ ጠብቆ እስከ ወልደመስቀል ኮስትሬና ቶለሳ ቆቱ አድርሶናል። ከእንግዲህ ወዲህ ግን ማን ይሆን የአደራውን ሰንደቅ ዓላማ የሚረከበው የሚለው ጥያቄ የብዙ ኢትዮጵያውያን ስፖርት አፍቃሪዎች ጥያቄ እየሆነ መጥቷል።

ሰሞኑን 33ኛው የፓሪስ ኦሎምፒክ የባሰውኑ ገመናችንን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል። ተተኪን የሚፈጥር አመራር ሳይሆን ስፖርቱን የሚያሸብር አመራር መፈጠሩን፣ ጠንካራ የአትሌቲክስ አሰልጣኝ በተለይም የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ከመፍጠር የቤተሰብ አሰልጣኝ መፈጠሩ፣ ለሀገርና ለወገን እንዲሁም ለውጤት የሚሮጥ አትሌት ከመፍጠር ይልቅ ገንዘብ አግኝቶ አሰልጣኞችን የሚያበለጽግ አትሌት መፈጠሩን አመላክቶን አልፏል።

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከሪዮ መልስ ውጤታችን አሽቆልቁሏል በማለት አፈርሳታ ወጥቶ አዲስ አመራር እንዲፈጠር ሲባል በተደረገው ጥያቄና ንቅናቄ የአዲሱን አመራር መምጣት ተቀብለው ከተደሰቱት አንዱ ነበርኩ። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ይነሳ የነበረው ጥያቄ በየዘመኑ የሚመረጡ የፌዴራሽን አመራሮች በስፖርት ውስጥ አላለፉም፣ ስለ አትሌቶች ድካምና ጉዳት በደንብ አያውቁም ወይም አልተረዱም በማለት በየጊዜው በአትሌቶች የሚነሱ እሮሮና ጥያቄ መልስ ያገኛል የሚል ተስፋን በመሰነቅ ነበር።

አዲሶቹ አመራሮች በተለይም በዓለም የአትሌቲክስ መድረክ ሀገርን ያኮሩ፣ በሕዝባቸው፣ በመንግሥትና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ የተከበሩና ተቀባይነት ያላቸው እነ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያም፣ ገዛኸኝ አበራ ማርቆስ ገነቲ፣ መሰለች መልካሙ ታላቁ አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ፣ አበበ መኮንን በኋላ ረ/ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከአትሌቶች መሃል የወጡና የአትሌትክሱን ችግር ቀምሰው ያለፉ፣ ለአትሌቱ ዕድገት የሚጥሩና ከፍ የሚያደርጉ አውቀው የሚያሳውቁ መስሎኝም ነበር።

ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና ከውጤቱ ይልቅ ንትርክና ጭቅጭቅ፣ ከጽ/ቤቱ ወደ አደባባይ በመውጣት ገመናችንን አጋለጡ። በሪዮ ኦሎምፒክ የታየው ድክመታችን ምንም ሳይታረም በቶኪዮ ተደገመ፣ ይባስ ብሎ በፓሪስ ቀደም ሲል በምንታወቅባቸው ውድድሮች በተለይም 10 ሺ እና 5 ሺ ሜትር ሜዳልያ ከእጃችን ወጣ።

ትናንትና እኛ አፍሪካን በምናስተዋውቅበትና በምንታወቅበት 10 ሺ ሜትር ውጤታችንን ለሌሎች ሀገሮች አሳልፈን እንድንሰጥ ተገደናል። ትናንትና የኢትዮጵያ ጀግኖች በድል አድራጊነት በሜዳሊያ ሲታጀቡ በአድናቆት እያጨበጨቡ የሚደግፉን ሀገሮች፣ ዛሬ የኛን ውጤት ነጥቀውን እኛ ደግሞ በተራችን ቁጭ ብለን እያጨበጨብን እንድናደንቃቸው ተደርገናል። ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአትሌቲክስና በቡና ነው ይባል ነበር። ዛሬ ግን አትሌቲክሱን ለሌላ ሀገር አሳልፈን ሰጥተን ቁዘማ ታቅፈን ቀርተናል የሚሉ ወገኖች ብዙዎች ሆነዋል።

ስለሆነም አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም እንደሚባለው መኩሪያችን የሆነው አትሌቲክሳችን ይበልጥ አሽቆልቁሎ የሀገራችን ዝናና ኩራት የበለጠ ዝቅ እንዳይል የሚመለከተን ሁሉ በጋራ የምንሥራበት ጊዜ አሁን ነው እላለሁ!

ተሾመ ቀዲዳ (ከበሪሳ ጋዜጣ)

አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You