በተሽከርካሪ ለሚደርስ ሞትና የአካል ጉዳት የሚፈጸመው የሦስተኛ ወገን መድን ክፍያ ተሻሻለ

አዲስ አበባ:- በተሽከርካሪ አደጋ ለሞት እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለአስቸኳይ ሕክምና ይከፈል የነበረውን የገንዘብ መጠን ያሻሻለ ደንብ ተግባራዊ መሆኑን የመንገድ ደኅንነት እና መንገድ ፈንድ ገለጸ።

በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ አደጋ የመድን ፖሊሲ የሚከፈለውን የአረቦን ተመን የካሳ መጠን ክፍያ ለመወሰን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣው ደንብ ቁጥር 554/2016 ተግባር ላይ ውሏል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ደንቡ በተሽከርካሪ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለአስቸኳይ ሕክምና ሁለት ሺህ ብር ይከፈል የነበረውን ወደ15 ሺህ ብር አሳድጓል።

በተሽከርካሪ ጉዳት ለሞት ይከፈል የነበረው ካሳ 40 ሺ ብር እንደነበር በማስታወስም፤ ለሞት የሚከፈለውን የገንዘብ መጠን ወደ 250 ሺህ ብር ማደጉንም ነው የገለጹት።

ውሳኔው የብር ግሽበትና ሌሎች ጉዳዮችን ግምት ውስጥ በማስገባት የተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል። የተሽከርካሪ አደጋ ለደረሰበት ሰው ሕክምና ይመደብ የነበረው ሁለት ሺህ ብር አነስተኛ ነው በሚል ሰፊ ቅሬታ ሲነሳበት የቆየ መሆኑን አመልክተዋል።

የተሽከርካሪ አደጋ የደረሰበት ማንኛውም ሰው በየትኛውም ሆስፒታል በሀገር አቀፍ ደረጃ የነፃ ሕክምና አገልግሎት እንደሚያገኝም ነው የገለጹት።

ይህንን ገንዘብ ለመሸፈን ኢንሹራንስ ፕሪሚየም፣ ማለትም የሦስተኛ ወገን የኃላፊነት ክፍያዎች ላይም ተሽከርካሪዎች በየዓመቱ የሚከፍሉት ግብር ጭማሪ እንዲደረግ ውሳኔ መተላለፉን ተናግረዋል።

በአዲሱ የሦስተኛ ወገን የኃላፊነት መመሪያ መሠረት ለአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት በፊት ተቀምጦ የነበረው ሁለት ሺህ ብር ወደ 15 ሺህ ብር ከፍ ማለቱን ተከትሎ በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ አደጋ የመድን ፖሊሲ የሚከፈለው የአረቦን ተመን የካሳ መጠን ላይ መጠነኛ ጭማሪ ተደርጓል ነው ያሉት።

በተሽከርካሪዎች ላይ የሦስተኛ ወገን ተለጣፊ አስገዳጅ ሕግ፣ በየዓመቱ ይከፈል በነበረው ላይ ጭማሪ ተደርጎ እንደሚከፈልም ጠቁመዋል።

እንደሲሲያቸው መጠን ተሽከርካሪዎች የሚከፍሉት ገንዘብ የሚለያይ ሆኖ፤ አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር አካባቢ፤ ከባድ ተሽከርካሪዎች ደግሞ እስከ 11 ሺህ ብር ገደማ የሚደርስ ፕሪሚየም የዓመት ክፍያ ሽፋን እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You