በኢትዮያ ለትርፍ ያለተቋቋሙና በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሰማሩ በርካታ ሀገር በቀል ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ድርጅቶች በአብዛኛው ድጋፍ የሚሹ ወጣቶችን፣ ሴቶችን፣ ወላጅ አልባ ህፃናትን፣ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማንን በተለያየ መንገድ ያግዛሉ። ይህንኑ ሥራቸውን ለማከናወን ደግሞ ቋሚ ገቢ የላቸውም። ለዛም ነው በተለያየ መልኩ ከህብረተሰቡ ድጋፍ እያሰባሰቡ ህልውናቸውን ለማስቀጠል የሚፍጨረጨሩት።
እንደ ሜቄዶንያ፣ ጌርጌሴኖን፣ የወደቁትን አንሱ፣ ሙዳይና ሌሎችም የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጎዳና ላይ የወደቁ አረጋውያንን፣ ህፃናትን፣ ሴቶችን፣ ወጣቶችንና የአእምሮ ህሙማንን ከጎዳና ላይ በማንሳት የበርካቶች ባለውለታ ለመሆን ችለዋል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ በእናቶችና ህፃናት ድጋፍና እንክብካቤ ዙሪያ እየሠራ ያለው ስለእናት የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።
አቶ ያሬድ አብዱ የስለእናት በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፣ ድርጅቱ በ1994 ዓ.ም በወይዘሮ ሃና እና ጓደኞቻቸው የተመሰረተ ሲሆን በግዜው በነበረው የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ህፃናት ወላጅ አልባ በመሆናቸው እነዚህ ህፃናት በመርዳት ነው ሥራውን የጀመረው። ላለፉት 22 ዓመታትም በሴቶችና ህፃናት ላይ ሲሠራ ቆይቷል። በተለያዩ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ያሉ ህፃናትን ተቀብሎ ይንከባከባል። ለወግ ማእረግ እንዲበቁ ያግዛል። የተለያዩ የድጋፍ አማራጮችን መሠረት አድርጎ ይሰራል።
ከዛሬ ሃያ ሁለት አመት በፊት የነበረው አስከፊ የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ በርካታ ህፃናትን ያለአሳዳጊ አስቀርቷል። ከዚህ እንፃር ድርጅቱ ወላጅ አልባ ህፃናት በጉዲፈቻ እንዲያድጉ ያመቻቻል። በስፖንሰርሺፕ ፕሮግራም ባሎቻቸውን ላጡ ሴቶች የኢኮኖሚ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። ሁሉም ድጋፍ የሚሹ ህፃናትና ሴቶች ወደ ድርጅቱ የሚመጡት በመንግሥት ተቋማት ምልመላ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ የከተማው ሴቶችና ማህራዊ ጉዳይ ቢሮ ድጋፍ የሚሹ ህፃናትና ሴቶችን በራሱ መስፈርት መልምሎ ለድርጅቱ ያቀርባል።
አሳዳጊ ወይም ቤተሰብ የሌላቸው ህፃናት ደግሞ በዚህ ጉዳይ ከሚሠራው የመንግሥት ቢሮ በሚሰጥ ደብዳቤ ድርጅቱ ተቀብሎ ድጋፍና እንክብካቤ ያደርጋል። ጠፍተው የተገኙ ህፃናት ቤተሰቦቻቸውን በማፈላለግ እንዲቀላቀሉ የማድርግ ሥራም ከዚሁ ጎን ለጎን ያከናውናል። በድርጅቱ በኩል ለህፃናትና ሴቶች የተለያዩ ድጋፎች ይቀርባሉ። እነዚህም የአልባሳት፣ መጠለያ፣ ሥነ ልቦና፣ በስፖንሰርሺፕ የገንዘብ ድጋፍ ናቸው።
የስፖንሰርሺፕ የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ልጆቹ ትምህርት የጀመሩ፣ እናት ወይም አባት ለብቻቸው ልጅ የሚያሳድጉ ወይም ሁለቱም ከሌሉ ልጆች በአያት ወይም በታላቅ እህት አልያም ወንድም ሚያድጉ መሆን አለባቸው።
አቶ ያሬድ እንደሚገልፁት፣ ከዚህ ቀደም ድርጅቱ ለህፃናትና ሴቶች ድጋፍና እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችለውን ገቢ የሚያገኘው በውጪ ሀገር ከሚገኙ ድርጅቶች ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ የዓለም ኢኮኖሚ በጥሩ ሁኔታ ላይ ባለመሆኑና የኮቪድ ወረርሽኝ ያስከተለው ሁለንተናዊ ቀውስ ድጋፉን እንዲቀንስና እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። ከዚህ አንፃር ድርጅቱ ወደ ሀገራዊ ድጋፍ ፊቱን በማዞር ተረጂዎች በኢትዮጵያውያን ድጋፍ የሚያገኙበትን ስልት ቀይሶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ድርጅቱ ራሱን ለማህበረሰቡ በማስተዋወቅ፣ የሚሠራቸው ሥራዎች እንዲጎበኙ በማድረግ፣ የተለያዩ ሁነቶችንና በግቢ ውስጥ የቡና ጠጡ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት፣ በዓለም አቀፋዊና ሕዝባዊ በአላት ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞች ቀርፆ በማቅረብና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል። አሁን ደግሞ ትናንት በተከፈተውና ታሜሶል ኮሚዩኒኬሽን ባዘጋጀው ኤግዚቢሽን ላይ ቦታ በነፃ ተረክቦ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎቹን ለማህበረሰቡ የማስተዋወቅና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየሠራ ይገኛል። የመፅሃፍትን፣ ሙዚቃዎችን ለገበያ በማቅረብ ሰዎች ሌሎች እቃዎችን እየገዙ ድርጅቱን እንዲያግዙ እየተደረገም ነው።
ድርጅቱ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ረጅም ዓመት አስቆጥሯል። ህብረተሰቡ ለሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች ያለው አመለካከት ጤናማ እንዲሆን ይጥራል። ከዚህ ቀደም በነበሩ አንዳንድ ኤግዚቢሽኖች ላይም ተሳትፏል። ነገር ግን ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች ከሌሎች የንግድ ተቋማት በኤግዚቢሽኑ እኩል ቦታ ባለማግኘታቸው ራሳቸውን በሚገባ ማስተዋወቅ ሳይችሉ ቀርተዋል። ይሁንና ታሜሶል ኮሚዩኒኬሽን ባዘጋጀው ባዛርና ኤግዚቢሽን ስለእናት በጎ አድራጎትን ጨምሮ ለሌሎች ድርጅቶች በነፃ የተሰጣቸው ቦታ እነርሱን የሚመጥን፣ ሰው ሊያያቸው የሚችልና ራሳቸውንም ለጎብኚዎች በማስተዋወቅ ድጋፍና እገዛ እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ ይህን ማህበራዊ ሃላፊነትን የመወጣት ተግባር ሌሎች ኤግዚቢሽን የሚያዘጋጁ አካላት በመልካም ተሞክሮ ሊወስዱት ይገባል።
በዚሁ አጋጣሚ ስለእናት የበጎ አድራጎት ድርጅት ዘንድሮ 22ኛ አመቱን ይዟልና በህብረተሰቡ ይበልጥ እየታወቀ መጥቷል። ሥራዎቹም ፍሬ እያፈሩ ነው። በድርጅቱ ያደጉ ልጆችም ለወግ ማእረግ በቅተዋል። ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ድርጅቱንም ወደ መደገፍ ተሸጋግረዋል። ስለዚህ ተቋሙ እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው በማህበረሰቡ ድጋፍ እንደመሆኑ ማህበረሰቡ ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት ስለእናትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተመሳሳይ የበጎ ሥራ የሚያከናውኑ ድርጅቶችን በሙያ፣ በእውቀት፣ በገንዘብና በሌሎችም መንገዶች ማገዝ ይኖርበታል።
በተለይ በርካታ ሀገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች በኤግዚቢሽን ማእከል ስለሚቀርቡ ኤግዚቢሽኑን ለመጎብኘት የሚመጡ ሰዎች በዚሁ አጋጣሚ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እያከናወነው ያሉትን ሥራ በማየት ድጋፍና ማበረታቻ ቢያደርጉ መልካም ነው። ድርጅቶቹ ባዘጋጇቸው ፎርሞች አማካኝነት አባል በመሆን የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረግም ይችላሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም