ዩኒማስ ኢንጂነሪንግ – የሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች ተምሳሌት

ዜና ሐተታ

መንግሥት የሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች በጥራትና በብቃት አምርተው የሀገር ውስጥ ፍጆታን እንዲያሟሉ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ከማሻሻል ጀምሮ በርካታ እገዛዎችን እያደረገ ነው።

ከውጭ ለሚገቡ ምርቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ መቀነስ፣ ወደ ውጭ የሚላከውን ደግሞ በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ በመንግሥት ከተያዙ ሀገራዊ እቅዶች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው።

በኢትዮጵያ ካሉ ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎች መካከል ኃይል ቆጣቢ መብራቶች፣ ብሬከሮች፣ ኤክስቴንሽን ሶኬቶች፣ ቮልቴጅ መቆጣጠሪያዎችና ሌሎችን የኤሌክትሪክ ውጤቶችን የሚያመርተው ዩኒማስ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተጠቃሽ ነው።

ዩኒማስ በ2005 ዓ.ም በመንግሥት የተመዘገበ ድርጅት ነው። ከውጭ ይገቡ የነበሩ በርካታ የኤሌክትሪክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን የመተካት ሥራ እየሠራ ይገኛል። የዓመቱ ለኤሌክትሪክ ግዥ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ መቀነስ አስችሏል፡፡

የዩኒማስ ኢንጅነሪንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ሙዘይን እንደሚገልጹት፤ ዩኒማስ የተለያዩ የኤሌክትሪክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ለ10 ዓመታት የቤት ውስጥና የኢንዱስትሪ የመገልገያ እቃዎችን እያቀረበ ይገኛል። በዚህም ለ97 ቋሚና ለ22 ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡

ወደፊት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የጀመረውን ማስፋፊያ ሥራ ሲጀምር 300 የሚደርሱ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ፡፡

ምርቶች በኢትዮጵያ የደረጃዎች ባለስልጣን ባወጣው ደረጃ መሠረት እንደሚመረቱ ጠቅሰው፤ በሀገር ውስጥ ደረጃ ያልተቀመጠላቸውን ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ መሠረት እየተመረቱ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ ጥሬ እቃዎች ቀደም ብለው የገቡ በመሆኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ማሻሻያ አልተደረገም ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ወደፊትም ቢሆን የኅብረተሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ ለገበያ ማቅረባችንን እንቀጥላለን ይላሉ፡፡

ድርጅቱ ወደ ሥራ ከገባ ጀምሮ በውጭ ምንዛሪ ይገቡ የነበሩ የኤሌክትሪክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመሸፈን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማሳደግ ተችሏል ሲሉ ይገልጻሉ።

ዩኒማስ በቀጣይ ለጐረቤት ሀገሮች የኤሌክትሪክ ምርቶችን ለመላክ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አንስተው፤ አሁን ላይ ለኢንዱስትሪዎች፣ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለንግድ ተቋማት የሚሆኑ እቃዎችን ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች እያቀረበ እንደሚገኝ ያመላክታሉ።

የኤሌክትሪክ ምርቶች በሙሉ አቅሙ በሀገር ውስጥ ለማምረት 11 ሺህ 647 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ መረከቡንም ያስታውቃሉ። ምርቶችን በስፋትና በጥራት ወደ ገበያ ለማቅረብ ከታዋቂ ኩባንያዎች ማሽኖችን ለማስመጣት ቅድመ ዝግጁት ማጠናቀቁን ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፣ ማሰራጫና ማከፋፈያ ፕሬዚዳንት አቶ ወንዶሰን በላይ በበኩላቸው፤ ዩኒማስ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ማስቀረት ችሏል፡፡ ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን ይጠቁማሉ።

በጥራት ላይ የተመሠረት አምራች ኢንዱስትሪ በመሆኑ ለሀገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። እንዲሁም ዩኒማስ የሚያመርታቸው የኤሌክትሪክ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እያቀረበ ነው ይላሉ።

በርካታ የኤሌክትሪክ እቃዎች ጥራታቸውን ሳይጠብቁ በገበያ ላይ ይገኛሉ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህም ለመንግሥትና ለኅብረተሰቡ ፈተና ደቅኗል፤ ኅብረተሰቡም ከፍተኛ ጉዳትን እያስተናገደ ነው፡፡ እንዲሁም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ የኤሌክትሪክ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

ዩኒማስ ተደራሽነቱን ለማስፋት የጀመረው የማስፋፊያ ሥራ ተጠናክሮ እንዲሄድ፣ ጥራት ያላቸው ምርቶች ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች እንዲቀርቡ ለማድረግ መንግሥት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲሠራ ቦታ መስጠቱ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ነው የተናገሩት።

ይህም በቀጣይ ለተለያዩ የኤሌክትሪክ ምርቶች የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ሁኔታ ለማስቀረት እንደሚረዳ አንስተው፤ ወደፊት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በሻገር ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት እንደሚያግዝ ይገልጻሉ።

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You