በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ባገኟቸው ዕድሎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ዕውቀት ለመቅሰምና የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የቻሉ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አሉ:: እነዚህ ኢትዮጵያውያን ያገኙትን ዕውቀት ለወገኖቻቸው ለማድረስና አዳዲስ አሠራርንና አስተሳሰብን በሕዝባችን መካከል ለማስረጽ አብዝተው የደከሙና ሕይወታቸውን አሳልፈው እስከ መስጠት የደረሱ ፋና ወጊ ግለሰቦች እንደሆኑም እንደነበሩም ይታወቃል::
ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪና ጠላት በመከላከል አኩሪ ታሪክ የሠሩ፣ የሕዝባቸው ደኅንነትና አንድነት እንዲጠበቅ ለማድረግ መስዋዕትነት የከፈሉና አንፀባራቂ ታሪክ የሠሩ ጥቂቶች አልነበሩም፤ አይደሉምም:: በደራሲነት፣ በሙዚቃ፣ በሥዕል፣ በስፖርት፣ በታሪክ፣ በሳይንስና በእምነት አስተምሮ፣ የኪነ ጥበብና የምርምር ሥራዎችም ኢትዮጵያን በዓለም የበለጠ እንድትታወቅ ያደረጉ ትናንትናም ዛሬም ደምቀው የሚታዩ ደማቅ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ብዙዎች ናቸው::
ከእነዚህ የሀገር ባለውለታ ግለሰቦች መካከል ኢትዮጵያ በስፋት በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት በተለይ በረዥም ርቀት አትሌክስ በርካታ ውድድሮችን በማሸነፍ ታሪክ መሥራት የቻሉ አንጋፋው አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ አንዱ ናቸው።
«ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለሀገሬ በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት ሬሳዬ የሚወጣው ከሩጫ ሜዳ ነው» የሚሉት አትሌት ዋሚ፣ የተወለዱት ጥር 11 ቀን 1907 ዓ.ም ነው:: የአቶ ቢራቱ በራቄ እና የወይዘሮ ወርቄ አያና ልጅ የሆኑት ዋሚ፣ የትውልድ ስፍራቸው ከአዲስ አበባ ከተማ በ21 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሱሉልታ ወረዳ አካኮና መነ አብቹ በተባለው ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነው::
ዋሚ የስድስት ወንዶችና የአምስት ሴት ልጆች አባት፣ ከ20 በላይ ልጆች አያትና ከ10 በላይ ልጆች ቅድመ አያት ናቸው:: በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ፈር – ቀዳጅ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት አትሌት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በራቄ፣ ዛሬ በ107ኛ ዓመት ዕድሜያቸው መጀመሪያ ላይ ናቸው::
ዋሚ፣ ጠንከር እያሉ ሲመጡ በመንደራቸው ላይ ቤተሰባቸውን ከብት በመጠበቅ እንዲሁም አንዳንድ የእርሻ ሥራዎችን በማከናወን ይረዱ ነበር። ተሮጦ ዝነኛ እንደሚኮን እንዲሁም ሰዎችን ሌሎች ተፎካካሪዎችን መብለጥ እንደሚችሉ ያወቁት ባጋጣሚ ነበር። በሩጫ ሀገር ማስጠራት እንደሚቻልም እንደዚሁ።
አጋጣሚውን የፈጠሩት ደግሞ እናታቸው ናቸው። ወይዘሮ ወርቄ፣ አንዳንድ ነገሮች ለመሸማመት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ። አስፈላጊውን ሁሉ ካከናወኑ በኋላም ወደ ቀዬአቸው ይመለሳሉ። ልጅ ዋሚ ደግሞ እናታቸው ሸክፈው የመጡትን እቃ ተቀብለው ወደ ቤት ይገባሉ። በዚህ እቃ ተጠቅልሎበት የመጣ ጋዜጣ እጃቸው ላይ ይገባል። ጋዜጣው የአንድ ሯጭ ምስልን ይዟል። ዋሚ ደግሞ በመንደራቸው ጋራ ተራራውን፣ ቁልቁለት ዳገቱን በሩጫ ሲቦርቁ ነው የሚውሉት። ሩጫ ስፖርት መሆኑን ተገንዝበውም እርሳቸው ጥሩ ሯጭ መሆን እንደሚችሉ በማመናቸው ልባቸው ይህን ማድረግ ይመኝ ጀመር።
ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ ወንድማቸውን ሊጠይቁ ወደ አዲስ አበባ ጎራ አሉ። የወንድማቸው መኖሪያ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ሲሆን፣ በዚያች ገጠመኝም አዲስ ወታደሮች ሲመለመሉ ተመለከቱ። ምልመላውን ቆመው ሲመለከቱ አንድ ሃምሳ አለቃም ዋሚን ለምን አትገባም ብሎ ጥያቄ አቀረቡላቸው። ከመስከረም 5 ቀን 1945 ዓ.ም ጀምሮ ወታደር ሆነው ተቀጠሩ።
ስልጠናቸው ሲጨርሱ ዋሚ ሁለተኛ ክፍለ ጦር ተመድበው ወደ አስመራ ሄዱ። በወቅቱ ምልመላ ወታደሮችና ነባሮች በህብረት ሩጫ ይወዳደሩ ነበር። በ10 ኪሎ ሜትር ዋሚ አንደኛ ሆነው ማሸነፍ ቻሉ። በዚህም ምክንያት ስፖርት ላይ በመደበኛነት ቆዩ። 1947 ዓ.ም ለዋሚም ሆነ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዩ ዓመት ነበር። ለሜልቦርን ኦሎምፒክ ማጣሪያ የሙሉ ማራቶን ውድድር ተዘጋጀ:: ከዚያ በፊት ማራቶን ተብሎ ይሮጥ የነበረው 15 ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር። በዚህ ዓመት ግን ማራቶኑ በመደበኛ 42 ኪሎ ሜትር ከ1950 ዓ.ም ሊሮጥ ተወሰነ።
እያንዳንዱ ክፍለ ጦር ሶስት ሶስት ተወዳዳሪ ተመርጦ ከ8ኛ ክፍለ ጦሮች 24 ተወዳዳሪ ተመረጠ። በኋላ ግን የጦር ኃላፊዎቹ የሚፈልግ ሁሉ ይሩጥ ብለው አዘዙ። የተወዳዳሪዎቹ ቁጥር 50 ደረሰ። ውድድሩ ተጀመረ፤ ዋሚ ያለ ምንም ችግር አንደኛ ሆነው አሸነፉ:: በቦታው የነበሩት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለሥላሴ ለአሸናፊዎቹ ዋንጫ እንዲሰጥ አዘዙ። ቀድሞ በአምስት ሺህ እና በ10 ሺህ አሸንፈው የነበሩት ዋሚ ሶስት ዋንጫ ተሸለሙ።
በማራቶኑ ውድድር ዋሚን ተከትለው ሁለተኛ እና ሶስተኛ የሆኑት ነጋሽ ቤኛ እንዲሁም ገብሬ ብርቄ አንድ አንድ ዋንጫ ተሸለሙ። የመጀመሪያው የማራቶን ውድድር በዋሚ ቢራቱ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በተዘጋጀው የማራቶን ውድድር አሸናፊ የሆኑት አትሌት ሻለቃ ዋሚ ቢራቱ ናቸው። ከዚያን በኋላ እነ አበበ ቢቂላ ማሞ ወልዴ መድረኩን ነግሰውበታል።
ይሁንና የዋሚ እና የመጀመሪያው መሥሪያ ቤታቸው ጦር ኃይሎች ጋር ብዙም መቆየት አልቻሉም ነበር። በአጋጣሚ ከቀዬአቸው ወጥተው የጦር ኃይሎች አባል የሆኑት ዋሚ፣ ቤተሰቦቻቸውን ለማየት ፈቃድ ጠየቁ። የፈቃድ ጥያቄው ግን ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ዋሚና ጦር ኃይሎች ተኳረፉ። በዚህ የተነሳ በ1948 ዓ.ም ዋሚ ክብር ዘበኛ ተቀጠሩ።
1949 ዓ.ም በልዑል መኮንን ሞት እንዲሰረዙ ተደረገ። ከ1950 እስከ 1952 ዓ.ም በአምስት ሺህ በ10 ሺህ እና በማራቶን ዋሚን የሚረታ ጠፋ። በተለይ በ1952 ዓ.ም ዋሚ፣ የማራቶን አንደኛነቱን ሲይዙ አበበ በቂላ 2ኛ ሆኖ ጨረሰ። ስለዚህም ዋሚ ቢራቱ እና አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን እንዲወክሉ ተመረጡ። በወቅቱ ይህንን ሁሉ ስኬት ሲያስመዘግቡ ፌዴሬሽንም ሆነ አሰልጣኝ አልነበራቸውም። የስፖርት ትጥቅ የሚባል ነገርም እንደዚሁ። ይሁንና ዋሚ ራሳቸውንም ሆነ አበበ ቢቂላን እያሰለጠኑ አዲስ ታሪክ መስራቱን ቀጠሉ::
በወቅቱ በኦሎምፒክ ሕግ መሠረት አንድ ሰው አሰልጣኝም ተወዳዳሪም መሆን ስለማይችል አሰልጣኝ መቅጠር ግድ ሆነ። ስለዚህም ስዊዲናዊው ሜጆሮኒ ስካና አበበን እና ዋሚን ለማሰልጠን ተቀጠሩ። ስዊዲናዊው አሰልጣኝ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የዓለም ምርጥ አትሌቶች የሚሆኑ ብላቴናዎችን እያሰለጠኑ መሆንን ለመረዳት ጊዜ አልወሰደባቸውም።
እኚህ የባህር ማዶ አሰልጣኝ፣ በአበበ እና በዋሚ ኢትዮጵያ አማካኝነት በረጅም ርቀት ሩጫ ድል እንደምታስመዘግብ ርግጠኛ ሆነው ነበር። ይህንንም ለንጉሡ በወቅቱ ቀርበው ተናግረው ነበር። ይሁንና ያን ሁሉ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩት ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ በድንገት ታመሙ። የሮም ኦሎምፒክ ውድድር ስድስት ቀን ሲቀረው ኢትዮጵያ የተማመነችባቸው ጀግና 19 ቦታ ብጉንጅ ወጣባቸው። አሰልጣኙ ሁለተኛውን ምርጥ አትሌታቸውን አበበ ቢቂላን ለማሳለፍ ተገደዱ። ስለዚህም አበበ በሮም ጎዳናዎች ታላቁን ተልእኮ ለመሸከም እና ለመፈፀም ተገደደ። አበበ ኢትዮጵያን ሮም ላይ ወክሎ ሮጠ። ኢትዮጵያውያንን አላሳፈረም ባለድል ሆነ።
በዋሚ መንገድ አበበ ቢቂላ ፣ማሞ ወልዴ ፣ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣ ስለሺ ስህን፣ ገንዘቤ ዲባባ የመሳሰሉ ጀግኖች መፍራታቸውን ብዙዎች ይናገራሉ።
ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ፣ በተለያዩ የሩጫ መድረክ ላይ ሀገራቸውን ያስጠሩበት ድል አስመዝግበዋል። ከነዚህ መካከል በአንድ ሺ500፣ ሶስት ሺ፣ አምስት ሺ፣ 10ሺ፣ 21ኪሎ ሜትር፣ 25 ኪሎ ሜትር፣ በ32 ኪሎ ሜትር በሀገር አቋራጭ እና የተለያዩ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ 51 የወርቅ፣ 44 የብር እና 30 የነሀስ ሜዳሊያዎችን ማገኘት ችለዋል። ከዚህም ሌላ 21 ሰርተፍኬት፣ አራት ዲፕሎማ እና ከ40 በላይ ዋንጫዎችን ወስደዋል። በተለያየ ወቅትም የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ አስችለዋል። የሶምሶማ ሩጫ በሀገራችን እንዲለመድ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል።
ሻለቃ ባሻ ዋሚ ቢራቱ፣ በጃፓን ቶኪዮ ማራቶን ተሳትፎ አድርገው ከአበበ ቢቂላ በመቀጠል 2ኛ ሲወጡ ያጋጠማቸው ሁኔታ በግላዊ የሕይወት ታሪካቸው ውስጥ ጉልህ ሥፍራ አለው:: 42 ኪሎ ሜትር ከ190 ሜትር ይሸፍን የነበረውን ርቀት እስከ 40ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ሲመሩ ቆዩ። ነገር ግን ከነበረው ሙቀት የተነሣ እግራቸው መላላጥ ጀመረ:: የሚሮጡት ባዶ እግራቸውን ነበርና ይፈስ የነበረው ደም የሚሮጡበትን መንገድ አቀለመው:: ሆኖም መሮጣቸውን ቀጠሉ፤ አበበን አሳልፈው ሁለተኛ ወጡ። በመላላጥ ለተጐዳው እግራቸውም የጃፓን ሐኪሞች ወደ ሆስፒታል ወስደው የሕክምና ርዳታ አደረጉላቸው:: ይህንን የተመለከቱ የሀገሪቱ ጋዜጠኞችም፣ «የኢትዮጵያዊው አትሌት የዋሚ ቢራቱ እግር የሰው አይደለም» ብለው ጻፉ::
ይህም ከረጅም ዓመታት በፊት ገጥሟቸው ለነበረውና እርሳቸውም ለሰጡት ምላሽ ሌላ ትውስታን ይጭራል፦ እኚህ ፋና ወጊ አትሌት በእግራቸው ሲጓዙ፣ ጎረቤታቸው የሆኑት አንድ ኮሎኔል ያገኟቸውና፣ “ዋሚ ና በመኪና ልሸኝህ..” ቢሏቸው፣ «የለም እቸኩላለሁ፤ ከእርስዎ ኮሣሣ መኪና ይልቅ የእኔ እግር ይሻላል …» በማለት የሰጡት ምላሽ እስከ ዛሬም ድረስ የሚወሳ የታሪካቸው አካል ሆኗል::
ጊዜው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1960 ሮም ፣ አበበ ቢቂላ የሮም ማራቶንን አሸነፈ። በመግቢያው ጫፍ ያገኘው ጋዜጠኛ – ‘’በማሸነፍህ ምን ተሰማህ?’’አበበ – ‘’እኔ አይደለሁም አሸናፊ፤ አሸናፊው ቤቱ ታሞ ተኝቷል’’ ሲል መመለሱ ይታወሳል:: በወቅቱ ለኦሎምፒክ የተደረገውን የሀገር ውስጥ ማጣሪያ ዋሚ ቢራቱ በባዶ እግር ሮጦ አንደኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም በህመም በሮም ኦሎምፒክ መሳተፍ አልቻለም ነበር።
አበበ ቢቂላ፣ ለጓደኛው ያለውን ክብር እና አድናቆት በሌለበት ለግሷል። ጀግና እያንዳንዱ ድርጊቱ ከራስ ወዳድነት የተሻገረ ነው። እንዲህ የተባለላቸው የኢትዮጵያ የማራቶን አባት ጋሽ ዋሚ ቢራቱ፣ ዛሬ 107 ዓመት ሞልቷቸዋል። አንደበታቸው አሁንም አይጠገብም ዛሬም አመስጋኝ የሀገራቸው እና አህጉራቸውን ድል ናፋቂ ናቸው።
በ1896 እኤአ ላይ የግሪኳ አቴንስ ከተማ ካስተናገደችው የመጀሪያው ኦሎምፒድ አንስቶ ባለፉት 128 ዓመታት ውስጥ በተካሄዱት 32 ኦሎምፒያዶች ኢትዮጵያ በ14 ተሳትፋለች:: በኦሎምፒክ መድረክ ሁሉንም ሜዳልያዎችን የሰበሰበችው በአትሌቲክስ ስፖርት ብቻ ሲሆን፣ በከፍተኛ የውጤት ታሪካቸው ከሚጠቀሱ ስምንት ሀገራት አንዷ ናት። አፍሪካን በመወከል ደግሞ ከኬንያ ቀጥሎ ከፍተኛውን ስኬት አስመዝግባለች::
ኦሎምፒክ የዓለም ሀገራትና ሕዝቦቻቸውን በአንድ መንፈስ የሚያስተባብር መድረክ ነው:: በስፖርት መድረኩ በድህነት የተጎሳቆሉ፤ በበቂ የስፖርት መሠረተ ልማት ዝግጅታቸውን ያላከናወኑ፤ በየሀገራቸው ባሉ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የተረበሹ፤ በጦርነት እና በኢኮኖሚ ቀውስ የሚገኙ ሀገሮቻቸውን የወከሉ ኦሎምፒያኖች ሲሳተፉ ሁሉም አንድ ዓላማ ይኖራቸዋል:: ይህ ዓላማ በሜዳልያ ክብር ሀገራቸውን ማኩራትና ሰንደቅ አላማቸውን ማውለብለብ ነው:: የኦሎምፒክ የሜዳልያ ክብር መጎናፀፍ ደግሞ የየትኛውም የዓለም ስፖርተኛ ህልም እንደሆነ ይታወቃል።
ባሳለፍነው ሳምንት በተጀመረው በፓሪስ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በ800 ሜትር ሴቶች፣ በአንድ ሺህ 500 ሜትር ወንዶች፣ በአንድ ሺህ 500 ሜትር ሴቶች፣ በአምስት ሺህ ሜትር ወንዶች፣ በአምስት ሺህ ሜትር ሴቶች፣ በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች፣ በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች፣ በሶስት ሺህ ሜትር የወንዶች መሰናክል፣ በሶስት ሺህ ሜትር የሴቶች መሰናክል፣ በሴቶች ማራቶን፣ በወንዶች ማራቶን እና በ20 ኪሎ ሜትር የወንዶች የርምጃ ውድድር የምትካፈል ይሆናል። እኛም መልካም ዕድል ለኢትዮጵያ እንመኛለን።
እኛም በዚህ የሀገርና የሕዝብ ባለውለታ የሆኑ ግለሰቦች በሚመሰገኑበት ዓምዳችን ወቅቱን በማስታወስ በአትሌቲክስ ስፖርት ዘርፍ ለኢትዮጵያ አርአያ በመሆን ከሮም ኦሎምፒክ ጀግናው አበበ ቢቂላ ዘመን ጀምሮ ለበርካታ አትሌቶች የጽናት ምልክት በመሆን የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን ባሻ ዋሚ ቢራቱን አመሰገንን::. ሰላም!
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም