
መኪና ማሽከርከር ይበልጥ ጥንቃቄን ከሚሹ ሙያዎች መካከል ይመደባል:: በሥልጠና የሚገኝና በልምድ የሚዳብር ሙያም ነው:: መኪና ለማሽከርከር በቅድሚያ የመንጃ ፈቃድ ትምህርትና ሥልጠናን መከታተል የግድ ይላል:: ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የተዓማኒነት ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ አንድ ሰው መንጃ ፈቃድ የሚያገኘው የሚጠበቅበትን ፈተና አልፎ እንደሆነም ዕሙን ነው::
መንጃ ፈቃዱን ቢያገኝም፣ ለወራት አሊያም ለዓመታት መኪና የማሽከርከር እድል ሳያገኝ ሊቆይ እንደሚችል ደግሞ ማሰብ ይገባል። በሀገሪቷ ሕግ መሠረት ደግሞ መንጃ ፈቃድ ያለው ሰው መኪና ያሽከርክርም አያሽከርክርም በየሁለት ዓመቱ ፈቃዱን የማሳደስ ግዴታ ተጥሎበታል።
አንድ ሰው የመንጃ ፈቃዱን ለማሳደስ ሲፈለግ በሁለት ዓመታት ውስጥ ምንም አይነት አደጋ አድርሶ እንደማያውቅ ከሁሉም የትራፊክ ጽህፈት ቤት ቅርንጫፎች ከተጣራ በኋላ ፈቃዱ እንዲታደስለት ይደረጋል:: አደጋ አድርሶ እንደማያውቅ ማጣራቱ ተገቢና ትክክለኛ አሠራር መሆኑ ቢታመንም፣ አንድ ሰው የመንጃ ፈቃድ ስላለው ብቻ መኪና ሲያሽከረክር መቆየቱ ሳይጣራ ፈቃዱን እንዲያድስ መፈቀዱ ተገቢ እንዳልሆነ ያነሳሉ።
ይህ አይነቱ አሠራር ሰዎች መንጃ ፈቃድ ስላላቸው ብቻ በየትኛውም ጊዜ መሪ እንዲጨብጡ ስለሚያበረታታ ለትራፊክ አደጋ መባባስ አንዱ ሰበብ ይሆናል የሚል ሃሳብ ይሰነዝራል::
መንጃ ፈቃድ ካወጣ ስድስት ዓመታትን ያስቆጠረት ወጣት ሱራፌል አራጌ፣ እስካሁን ድረስ መንጃ ፈቃዴን ከማሳደስ ውጪ መኪና አሽከርክሬ አላውቅም ይላል:: መንጃ ፈቃድ ያለው ሁሉ መኪና ያሽከረክራል ማለት አይደለም የሚለው ወጣቱ፤ በእድሳቱ ወቅት የመንጃ ፈቃዱ ባለቤት መጠነኛ የሙያ ፈተና የሚፈተንበት አሠራር ቢኖር መልካም እንደሆነ ያስረዳል።
መንጃ ፈቃድ ማሳደሻው ጊዜ ካለፈ ግን ግዴታ ለሰዓታት የተግባር ፈተና መውሰድ ይጠይቃል ያለው ወጣቱ፤ የመኪና ማሽከርከር ቴክኒካል እውቀት እንደመሆኑ ከሥራው ጋር መቆየትን የሚጠይቅ በመሆኑ አሠራሩ የማሳደሻ ጊዜ ላለፈበት ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉንም የሚያካትት ሊሆን ይገባል ይላል። ይህን አሠራር በአጭር ጊዜ መተግባር ከባድ ቢሆን እንኳ፣ መንጃ ፈቃድ ይዞ ሲያሽከረክር የቆየውን ሳያሽከረክር ከቆየው የሚለይበት የመረጃ ሥርዓት ቢኖር ጥሩ ይሆናል ሲል ያስረዳል።
“መኪና የምይዝበት አጋጣሚ ቢፈጠር በቅድሚያ ማሽከርከር ከሚችል ሰው ጋር ልምምድ አደርጋለሁ እንጂ መንጃ ፈቃድ ስላለኝ ብቻ መሪ ይዤ ከተማ አልወጣም” ያለው ወጣቱ፤ የሥራ ስፍራዬ የታክሲ መናኸሪያ አካባቢ እንደመሆኑ መንጃ ፈቃድ ያላቸው ወጣቶች ድንገት መኪና የሚይዙበት አጋጣሚ ሲፈጠር ተሳፋሪን ጭነው ከተማ ውስጥ ለማሽከርከር ወደኋላ እአይሉም ሲል ይናገራል:: በዚህ ሳቢያ ገና ከመናኸሪያ ሳይወጡ ግጭት የሚፈጥሩ ልምድ ያላዳበሩ ሹፌሮችን ተመልክቶ እንደሚያውቅም ተናግሯል::
ሌላው ያነጋገርነው አቶ ትንሳዔ ሳምሶን በማሽከርከር ሙያ ረጅም ዓመታትን አስቆጥሯል:: የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር የተወሰኑ ዓመታትን አብሮ እንደሠራ ይገልጻል። ከመንጃ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ፈቃዱን ለሚያሳድሱ መጠነኛና መሠረታዊ የማሽከርከር ሙያ እውቀት ላይ የተመሠረተ ፈተና ሊኖር ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥቷል:: አቶ ትንሳዔ፣ ፈተናው ብቻ ሳይሆን ፈተና የሚሰጥባቸው ተሽከርካሪዎችም ጊዜውን ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ ይገባል ይላል::
እርሱ እንደሚለው፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ መኪኖች እየበዙ፤ የቤንዚን መኪኖችም በኤሌክትሪክ በሚሠሩ መኪኖች እየተተኩ ናቸው:: መኪኖቹ የተለያየ አሠራር ያላቸው እንደመሆቸው መጠን የሚፈልጉት እውቀትም የመኪኖቹን የቴክኒክ አቋም መሠረት ያደረገ ሊሆን ይገባል:: ከዚህ አንጻር፣ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤቶች በአሁኑ ወቅት ተማሪዎቻቸውን የሚያሰለጥኑባቸው መኪኖች ግን ብዙ ዘመን ያስቆጠሩና የቴክኒክ አቋማቸውም ከዘመናዊ መኪኖች የራቁ መሆናቸውን ያስረዳል። ስለሆነም ትምህርት ቤቶቹ መኪኖቻቸውን ዘመኑ እንደሚጠይቀው ማዘመን ይኖርባቸዋል፤ የመንጃ ፈቃድ እድሳት በሚደረግበት ጊዜም በዘመናችን ጥቅም ላይ እየዋሉ ባሉ መኪኖች ሊሆን ይገባል የሚል አስተያየቱን ሰጥቷል::
ለመንጃ ፈቃድ እድሳት የሚመጡ ሰዎች መኪና ሲያሽከረክሩ ነበረ ወይ የሚለውን ማጣራቱ እጅግ ተገቢ መሆኑ ላይ እስማማለሁ ያሉት በአዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ተረፈ (ኢ/ር) ናቸው።
የመረጃ ሥርዓታችን ለዚህ የሚበቃ ስላልሆነ ስታሽከረክር ነበረ ወይ ብሎ ከመጠየቅ ውጪ ለጊዜው ሌላ አሠራር አለመዘርጋቱን ይናገራሉ::
“መንጃ ፈቃድ ሲታደስ ፈተና ይኑረው” የሚለውም ሃሳብ ተግባራዊ ቢደረግ በተለይም የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አኳያ በጎ ሚና እንዳለው የሚጠቁሙት ዳይሬክተሩ፤ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በቂ የመለማመጃ ቦታ፣ ባሉት 12 ቅርንጫፎች፣ በሁሉም የመንጃ ፈቃድ ዘርፎች አስፈላጊ የሆኑ ተሽከርካሪዎችና በቂ የሰው ኃይል ማዘጋጀትን እንደሚጠይቅ ያስረዳሉ:: ይህም ከፍተኛ የመሠረተ ልማት፣ የፋይናንስና የአተገባበር መመሪያን እንደሚሻም ነው ያነሱት::
ዳይሬክተሩ እንዳስታወቁት፣ ከመንጃ ፈቃድ እድሳት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን በቋሚነት መፍታት የሚቻልበት አሠራር እስኪዘረጋ ድረስ፣ ባለሥልጣኑ ድንገተኛ የተሽክርካሪ ምርመራ እንደሚደረገው ሁሉ ድንገተኛ የመንጃ ፈቃድ ምርመራ ለማካሄድ በጅምር ላይ ይገኛል:: ይህም አንድ መንጃ ፈቃድ የያዘ ሰው በሥልጠና ያገኘው ክህሎት አብሮት አለወይ? የሚለውን ለማጥራት ያግዛል:: የመንጃ ፈቃድ ድንገተኛ ምርመራ መንጃ ፈቃድ ኖሯቸው ሥልጠናውን ከወሰዱ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ሰዎች መንጃ ፈቃድ ስላለ ብቻ መሪ መያዝ እንዳይቻል የሚያስተምር ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ነው ያመላከቱት::
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም