ለምዕተ ዓመት የዘለቀ አገልግሎት

በኢትዮጵያ በአመሠራረታቸው ቀደምት ከሆኑና ለኢትዮጵያውያን ጉልህ አገልግሎት ከሰጡ የሕዝብ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው። የኢንስቲትዩት ምስረታ እና ታሪካዊ እድገትን ስንቃኝ እ.ኤ.አ. በ1922 አሜሪካዊው ሚስዮናዊ ዶክተር ቶማስ ላምቢ የበጎ ፈቃደኝነት የህክምና አገልግሎት ቡድን አማካኝነት የተመሠረተ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በመሥራቹ ላምቤ ስያሜውን ያገኘው ሆስፒታሉ የግንባታ የመሠረት ድንጋይ በ1922 ዓ.ም ተጣለ። በመቀጠልም በዶክተር ላምቤና በሚስዮናዊነት አብረውት በሄዱ አራት ዶክተሮች እና ስድስት ነርሶች አማካኝነት አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ይህ የሕክምና አገልግሎት እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ ማለትም እስከ እ.አ.አ 1935 ዓ.ም ቀጥሏል።

የጣሊያን መንግሥት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ በወቅቱ በሀገሪቱ ይሠሩ የነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ለቀው እንዲወጡ ተደርገው ካሳ ተሰጣቸው። በዚህም ምክንያት ዶክተር ቶማስ ላምቢ እና ባልደረቦቻቸው ወደ ሀገራቸው አሜሪካ ተመለሱ። ቀደም ሲል በቦታው ይሰጥ የነበረው የህክምና አገልግሎትም ተቋረጠ። ይልቁንም ቦታው በጣሊያን አስተዳደር ለአዲስ አበባ የንፅህና ቁጥጥር አገልግሎት መዋል ጀመረ።

የኢጣሊያ መንግሥት በመሥራቹ ዶክተር ላምቤ የተሰየመውን ላምቤ ሆስፒታል የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሻሻል መሞከሩ ይነገራል። በወቅቱ በሆስፒታሉ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን እና የራሱን ባለሙያዎች በመጨመር ተቋሙ ሚኒስትሮ ዴላ ሳኒታ ተብሎ ስሙ ተቀይሮ ቦታውም ወደ አራት ኪሎ አካባቢ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት ወደ ሚገኝበት ቦታ ተዘዋወረ።

በ1941ኢትዮጵያ ከጣሊያን ተላቃ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ኢንስቲትዩቱ ስያሜውን የኢምፔሪያል ህክምና ምርምር ኢንስቲትዩት በማለት በድጋሚ ካዛንቺስ ወደሚገኘው የቀድሞ ልዕልት ዘነበወርቅ ኃ/ስላሴ ትምህርት ቤት ተዘዋውሮ ቆየ። ከዚያም በ 1943 ዓ.ም ወደ “ካሳ ፖፑላሬ” በአሁኑ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በመሄድ ሰባት ዓመታት እንዲቆይ ተደረገ።

ጣሊያን ተሸንፋ ከኢትዮጵያ በወጣችበት ወቅት፣ ከጣሊያን ወረራ በፊት በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጡ የነበሩ ተቋማት ወደ ቤተ መንግሥት ይዞታ ተዛዋውረዋል። በዚህም ምክንያት የቀድሞው ላምቤ ሆስፒታል ተፈሪ መኮንን ሆስፒታል ተብሎ ተሰይሞ፤ ለንጉሣዊ ቤተሰብ መታከሚያ ሆኖ አገልግሎት መስጠት ቀጠለ።

በ1948 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአዋጅ ሲቋቋም በዘርፉ ይሰጥ የነበረው የህክምና አገልግሎት ተላልፎ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር እንዲተዳደር ተደርጓል። እ.ኤ.አ. በ 1952 የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በተለያዩ በሽታዎች ላይ ምርምር እና ጥናት ለማድረግና “ኢንስቲትዩት ፓስተር ዲ ኢትዮፒ” በሚል ስም የጤና የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት ለመስጠት ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር ስምምነት አደረገ። ከዚያም የተለያዩ ዲፓርትመንቶችን በማቋቋም ሥራውን ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሥራው በሁለቱም መንግሥታት ባለሙያዎች ይመራ ነበር።

ጥናት ለማካሄድ የተቋቋሙት ክፍሎች የባክቴሪዮሎጂ፣ ፓራሲቶሎጂ እና ሴሮሎጂ ክፍል፣ የኬሚካል ትንተና ክፍል፣ የአንቲባዮቲክ ክትባት ዝግጅት ክፍል፣ የቲፎይድ ክትባት ዝግጅት ዳይሬክተር፣ የቲቢ ቢሲጂ ክትባት ልማት መምሪያ፣ ራቢስ ክትባት ዝግጅት መምሪያ የሚባሉ ነበር ።

በወቅቱ በተለያየ መጠን ከተመረቱት ክትባቶች መካከልም የፀረ-ቫይረስ ክትባት፣ ፀረ-ታይፎይድ፣ የእብድ ውሻ ክትባት፣ የቲቢ ቢሲጂ ክትባት፣ የታይፎይድ ክትባት፣ ቢጫ ትኩሳት ክትባት እና የጉንፋን ክትባት ተካትተዋል። በየአመቱ የተወሰነ መጠን ያለው የክትባት መጠን ከመዘጋጀቱ በተጨማሪ፤ ለህብረተሰቡ በነጻ አገልግሎት ይሰጥ ነበር።

ከ1964 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በፈረንሳይ መንግሥት መካከል የተደረገው ስምምነት ከተቋረጠ በኋላ ተቋሙ በ1965 (ኢምፔሪያል) ሴንትራል ላብራቶሪ እና ምርምር ኢንስቲትዩት ተብሎ እንዲመሠረት ተደረገ እና አጠቃላይ አመራሩና ሠራተኞች በኢትዮጵያውያን እንዲተዳደሩ እና በጀቱ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲሸፈን ተደረገ።

ተቋሙ ቀደም ሲል ይሰጥ የነበረው አገልግሎት እስከ 1984 ድረስ በዚሁ ስም የቀጠለ ቢሆንም፣ የደርግ መንግሥት ከመጣ በኋላ ከእብድ ውሻ በሽታ መከላከያ ክትባት በስተቀር ሌሎች የክትባት አገልግሎቶች አልቀጠለም። ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ የኢንስቲትዩቱ ሥራ እየሰፋ ሲሄድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የጤና ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ተብሎ በአዲስ መልክ ተቋቁሟል።

ከ1968 እስከ 1973 ተቋሙ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የድርቅ ችግር ለመፍታት የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። የዶቤና እድገት በመባል የሚታወቁ ተጨማሪ መድሃኒቶችን ለማስተዋወቅም ግንባር ቀደም ነበር። ከ1973 ዓ.ም ጀምሮ ኢንስቲትዩቱ በዋናነት በምግብ ሳይንስ እና ሥነ-ምግብ ምርምር ላይ በማተኮር እንደ ዋና የላቦራቶሪ እና የምርምር ተቋም ሆኖ ማገልገሉን ቀጠለ።

ከጊዜ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የጤና ምርምር ሥራዎች የህብረተሰቡን የጤና ሁኔታ እና አጠቃላይ ደህንነት ለማሻሻል ለተሻለ የጤና አሠጣጥ ሥርዓት አስፈላጊ አካል ሆነው መታየት ጀመሩ። በመሆኑም የኢትዮጵያ ጤና እና ሥነ-ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት በሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 4/1996 እ.አ.አ በ1996 ራሱን የቻለ የመንግሥት አካል ሆኖ የራሱ የሕግ ሰውነት ያለው እና ተጠሪነቱ ለፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሆኖ ዳግም ተቋቋመ።

እንደገና የተቋቋመው የኢትዮጵያ ጤና እና ሥነ-ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት ተልዕኮ በቅድመ-ሕዝብ ጤና ጉዳዮች ላይ ችግር ፈቺ ምርምር ማካሄድ እና ለፖሊሲ ውሳኔ ሰጪዎች አስተማማኝ የጤና መረጃ መስጠት ነበር። ከፍተኛ ጥራት ያለው የሪፈራል የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት የመስጠት እና የእብድ ውሻ በሽታ መከላከያ ምርቶችን የማምረት ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። በ2000 ዓ.ም ኢንስቲትዩቱ የሥራ ሂደቶችን አሻሽሎ አዳዲስ ኃላፊነቶችን በመጨመር በሶስት ዋና ዋና የሥራ ሂደቶች ተደራጅቷል።

ተቋሙ እነዚህን አዳዲስ የአሠራር ሂደቶች እስከ 2013 ድረስ ቀጥሏል። ነገር ግን የሕግ ክፍተቶችን ለመፍታት እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ለማሳደግ ኢንስቲትዩቱ በ2013 “የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት” ተብሎ በአዲስ መልክ ተመሥርቷል።

አዲሱ ማቋቋሚያ ደንብ ሦስት ዋና ዋና ተግባራትንና ኃላፊነቶችን ዘርዝሯል። በብሔራዊ የሕዝብ ጤና ምርምር አጀንዳ ላይ በመመርኮዝ በጤና እና በአመጋገብ ችግሮች ላይ ምርምር ማካሄድ፣ የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ሳይንሳዊ እና ቴክኖሎጂያዊ እውቀቶችን ማመንጨት ፣ መቅሰም እና ማሰራጨት ናቸው።

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የዳሰሳ ጥናቶችን ለማካሄድ፣ የጤና አደጋዎችን አስቀድሞ በመለየት እና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዲሁም የጤና አደጋዎች ሲከሰቱ ተቋሙ ማንቂያዎችን፣ ማስጠንቀቂያዎችን እና ወቅታዊ መረጃዎችን የመስጠት፣ ፈጣን እና ብቁ ምላሽ ለመስጠት እና የተጎዳው ማህበረሰብ ከተፅዕኖው በፍጥነት እንዲያገግም የመርዳት ሃላፊነት እንዳለበት ተቀምጧል።

የኢንስቲትዩቱን ላብራቶሪዎች በሠለጠነ የሰው ሃይል እና የላቀ ቴክኖሎጂ በማጠናከር ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለማካሄድ፣ ለህብረተሰብ ጤና ስጋቶች ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት፣ የሪፈራል ምርመራ እና ትንተናዊ ሙከራዎችን በማድረግ፣ የጤና እና የምግብ ሳይንስ ላቦራቶሪዎችን አቅም በሀገር አቀፍ ደረጃ ማሳደግ እና አቅርቦቱን ማረጋገጥ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ከተሰጡት የሃላፊነት ተግባራት መካከል ናቸው።

የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ፤ እንደሚናገሩት ኢንስቲትዩቱ ላለፉት አንድ መቶ ዓመታት በርካታ የሕብረተስብ ጤናን የተመለከቱ ጥናትና ምርምሮችን፣ የላብራቶሪ አገልግሎቶችን፣ የማሕበረሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራዎችንና እና ሌሎች ተያያዥ ተልዕኮዎችን ሲወጣ ከመቆየቱም በላይ እየተወጣ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ የሥራ አድማሱን በማስፋት በሀገር አቀፍ ደረጃ ልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ጤና ነክ ሥራዎችን በስፋትና በጥራት እንዲሁም በቅንጅት እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ ተቋሙ በአፍሪካ ቀዳሚ የሕብረተሰብ ጤና ተቋም ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ላለፋት 100 ዓመታት ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቷ የሕብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ምሶሶና ማዕከል በመሆን የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ሲያበረክት እንደነበረ አውስተው፤ አሁንም ቢሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በመቆጣጠር፤ ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ አገልግሎት በመስጠት፣ በሕብረተሰብ ጤናና በሥነ-ምግብ ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ኢትዮጵያውያንን አገልግሏል ይላሉ።

በተጨማሪም በጤና ነክ መረጃዎች ትንተናና ቅመራ ዙሪያ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉን አቀፍ የአንድ ጤና እና የዓለም አቀፍ የጤና ደህንነት መርሐ ግብር በማስተባበርና በመምራት ብሎም የኢፒዲሞሎጂን ሥልጠናዎችን እና ሊሎች ተያያዥ የሕብረተሰብ ጤና ነክ የሆኑ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ያብራራሉ።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት መቶ ዓመታት በኢትዮጵያ በሽታን መከላከልና ከተከሰተም ለማህበረሰቡ ተገቢው ህክምና እንዲደርሰው ማድረግና የሚከሰቱ በሽታዎች ከምን አንፃር እንደተከሰቱ ጥናቶች በማከናወን የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ እንደቆየ ይናገራሉ።

እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ኢንስቲትዩቱ በሀገር ደረጃ የሚወጡ ፖሊሲዎች፣ ሕግና ደንቦች፣ አዋጆች በሚወጡበት ጊዜ የጥናት መረጃዎች ለሕግ አውጪ አካላት እየሰጠ የሚወጡ ፖሊሲዎች መረጃን መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ እያደረገ ቆይቷል ይላሉ። ለአብነት በቅርቡ ወጥቶ ተግባራዊ የሆነው የአልኮልና የትንባሆ ቁጥጥር አዋጅ በኢንስቲትዩቱ አማካኝነት ተዘጋጅተው የወጡ ሕጎች እንደነበሩ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ አማካኝነት ነፃነቷ ጠብቃ የቆየች ሀገር መሆኗ የራሴ የምትለው እንደዚህ አይነት ተቋም እንዲገነባ ምክንያት ሆኗል የሚሉት ዶክተር ጌታቸው፤ 100 ዓመት ያስቆጠረ ተቋም እንደመሆኑ በዚህ ቆይታው ያከማቸው ልምድና እውቀት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን ሁሉ የሚተርፍ እንደመሆኑ ይህንን አቅሙን ለአፍሪካውያን ጭምር በማጋራት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሆነ ይናገራሉ።

ዶክተር ጌታቸው እንደሚናገሩት፤ ኢንስቲትዩት ከጥናትና ምርምር ሥራው ቀጥሎ ስሙ የሚጠቀሰው የላብራቶሪ አገልግሎት ነው። በሀገሪቱ የሚገኙ ከአራት ሺህ በላይ የሚሆኑ ላብራቶሪዎችን የሚደግፍ የሚያበቃና ጠንካራ አቅም ያላቸው እንዲሆኑ ከመሥራት ባሻገር ለባለሙያዎች ሥልጠና ይሠጣል። ከዚህ ባሻገር ሌላ ቦታ የማይሰጡ የላብራቶሪ አገልግሎቶችን ይሰጣል ይላሉ።

በሶስተኛ ደረጃ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎችን በመከላከል በመቆጣጠርና መልሶ በማከም የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል። በዚህ እረገድ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሀገሪቱ በተከሰተበት ወቅት የሰራቸው የተለያዩ ሥራዎች እንደሚጠቀሱ ይናገራሉ።

እኛም በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ ከተመሠረተ 100 ዓመታትን ያስቆጠረውንና በተለያዩ ወቅቶች ለተከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች የመከላከል ሥራ በመሥራት ኢትዮጵያውያንን ለአንድ ምዕተ ዓመታት ያገለገለውን አንጋፋ ተቋም አመሰገንን። ሰላም!

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2016 ዓ.ም

 

Recommended For You