አለባብሰው ቢያርሱ …

እነሆ ሰኔ ግም ብሏል፡፡ አይቀሬው ዝናብ ሊያመር፣ ጎርፍ ጭቃው ሊከተል ነው። ደመናው መጥቆር፣ ነጎድጓዱ ማስገምገም ጀምሯል፡፡ በሚያዝያና ግንቦት ሲመላለስ የከረመው ሙቀት አሁን ተንፈስ እያለ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ክረምት ይሉት ጊዜ በራሱ ድንቅ ውበት አለው፡፡ ሁሌም ቢሆን ጭቃና ዝናቡን ፣ ብርድና ቆፈኑን በውዴታ ተቀብለን እናልፈዋለንና፡፡

ክረምት በተለይ ለእኛ ለአበሾቹ ብዙ ጉዳያችን ነው፡፡ ገጠር ካለው በረከት ባለፈ ተፈጥሯዊ ስጦታው ተናፋቂና ተወዳጅ ሆኖ በመስከረም ወር ይተካል፡፡ እንዲህ በሆነ ጊዜ የክረምቱን ገብቶ መውጣት በጥላቻ አናስታውስም፡፡ ‹‹እሰይ ጎሽ፣ ተገላገልን›› እያልን አናጥላላም፣አናማርርም፡፡ይልቁንም ለአንዳንዶቻችን ክረምት ሲገባ ጉዳያችን በእኩል ይታቀዳል፡፡ ዕቅዳችን በወግ ይከወናል፡፡

ክረምት በተለይ ጤናማ ሆኖ ከከረመ በትዝታ ታጅቦ ፣በነበር ታውሶ የሚያልፍ ነው፡፡ የክረምት በረከቶች ብዙ ናቸውና ወቅቱን በበጎ አስታውሶ ፣ ‹‹እንዲህ ነበር ›› ብሎ ማውጋቱ ብርቅ አይደለም፡፡ ጊዜው በደረሰ ጊዜ ከእሸት በቆሎው፣ከትኩስ ድንቹ፣ ከሚፋጀው የኩባያ ሻይ ጋር የሚኖር ቁርኝት ይበረታል፡፡እነዚህ ትንሽ የሚመስሉ፣ እንደአጋጣሚ የሚታዩ ሁነቶች ግን ሁሌም ቢሆን አብሮነትን ያሳምራሉ፡፡ ማህበራዊ አንድነትን ይጠብቃሉ፡፡ይህ እውነት ደግሞ የነባሩ ማንነታችን ማሳመሪያ ውበት ነው፡፡

ስለ ክረምቱ በጎነት ብዙ እያነሱ ማውጋት ይቻላል፡፡ ስላለፉትና ወደፊት ስለሚሆኑ በረከቶችም እንዲሁ፡፡ የዛሬው ትዝብቴ ግን በክረምቱ ጸጋ ላይ ብቻ የሚያተኩር አልሆነም፡፡ ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ እየሆኑ ያሉ እውነታዎችን ማንሳት ግድ ብሎኛል፡፡

ሰሞኑን በከተማችን አዲስ አበባ አንዳንድ የመንገድ ዳርቻዎች ተከማችተው የሚታዩ የቆሻሻ ክምሮች ለዓይን ይከብዳሉ፡፡ በተወሰነ ሜትር ርቀት ቁጭ ቁጭ ያሉት ቁልሎች ጠጋ ብለው ካዩዋቸው የማይቆጠሩት፣ የማይታዘቡት ጉድ የለም፡፡ ሁሉም በሚባል መልኩ በጭቃ አዋዜ ተለውሰዋል ፡፡

ጫማው፣ የላስቲክ ኮዳው፣ ፌስታል ላስቲኩ፣ ጨርቃጨርቁ፣አሮጌ ቁሳቁስና እርጥበት የማያሸንፋቸው ቁሶች ሁሉ በአይነትና በብዛት ይታያሉ፡፡እነዚህ እንደ መንገድ ገበያ ተዘርግተው የሚቆጠሩ ነውሮች በተአምር የመጡ አይደሉም፡፡ በአካባቢው የውሃ መውረጃ ቱቦዎች ላንቃ በብዙ ልፋት ተሰርስረው የወጡ እንጂ፡፡

እነዚህ ክምሮች በተለያዩ አጋጣሚዎች በአንዳንድ ሰዎች ግዴለሽነት የተወረወሩ ናቸው፡፡ ይህን አድራጊዎቹ እንደዋዛ የሚጥሏቸው ቁሶች ርቀው የሚሄዱ ባለመሆናቸው በቱቦዎቹ ሆድ ተከማችተው የመኖራቸው ጉዳይ ሁሌም ቢሆን ተለምዷል፡፡

በየመንገዱ የተሰሩት ቱቦዎች አስቀድመው መሠራታቸው ለተለየ ዓላማ ነበር፡፡ የውሃ መውረጃዎች ናቸውና ፍሳሽን በወጉ ያስተናግዳሉ፡፡ ስሪታቸው ደረቅ ቆሻሻንና የሚወገዱ ቁሶችን ለመቀበል አይደለም፡፡ በመንገድ ዳርቻ ላይ ውሃ እንዳይጠራቀምና መሄጃ እንዳያጣ በአግባቡ ተቀብለው ወደሚፈለገው አቅጣጫ የሚመሩ መስመሮች እንጂ፡፡

በተለምዶ የምናየው እውነታ ግን ከዚህ ዓላማ ፍጹም ተቃራኒ ሆኗል፡፡ እንዲህ እንደአሁኑ ክረምት በደረሰ ጊዜ የተጣሉትን ቅራቅንቦዎች እንደአገባባቸው መልሶ ለማውጣት የዋዛ አይሆንም፡፡ በቀላሉ ከቱቦው ደረት ተሰንቅረዋልና ቦታውን ጽዱ ለማድረግ ብዙ ስልትና ጉልበት ሊጠይቅ ግድ ይላል፡፡

አስቸጋሪውና አስደንጋጩ ጉዳይ ደግሞ ድንገቴው ዝናብ በመጣ ጊዜ የሚፈጠረው ችግር ነው፡፡ ከዝናብ በኋላ መንገዱ በጎርፍ ሲጥለቀለቅ፣ወሃው መሄጃ መድረሻ አጥቶ መራመጃ ሲጠፋ ማየት እየተለመደ ነው፡፡ይህ በዋዛ የሚታይ ውጤቱ ግን አደገኛ የሆነ አጋጣሚ ብዙዎችን ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡

ክረምት በገባ የመጀመሪያው ሳምንት በአንዳንድ አካባቢዎች ተሽከርካሪዎች በጎርፍ ተጥለቅልቀው ሲጨነቁ አይተናል፡፡ የገበያ ቦታዎችም በውሃ ተውጠው ዓይናቸው እያየ ሸቀጦቻቸው በጎርፍ መወሰዳቸውን እየሰማን ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተከሰተው ዝናብ ጎርፉ በቀላሉ ሄዶ የሚያበቃ አይሆንም፡፡ ከስፍራው ለቀናት ተኝቶ የሚከርመው ውሃ ተጨማሪ ኃይል እያከለ ሰፊ ባህር ሆኖ ይከርማል፡፡

ለዚህ ባህር መሰል ይዞታ ምክንያቱ የአካባቢው የውሃ መውረጃ ቱቦዎች በበርካታ ቁሶች መሞላታቸው ነው፡፡ ውሃውን ከቦታው አስወግዶ የተደፈኑ ቱቦዎችን ለማጽዳት ደግሞ ቀናትን መጠበቅ፣ፀሐይን መናፈቅ ግድ ይላል፡፡ አንዳንዴ በአንዳንድ ስፍራዎች ቦታውን በፍጥነት ለማጽዳት የውሃ መምጠጫ ፓምፖች ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ውሃው አረንጓዴ ምንጣፉን እንደለበሰ መስከረምን ይሻገራል፡፡

ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነቶቹ ክስተቶች ከዓላማ ያዘናጋሉ፡፡ ከስፍራ ያሰድዳሉ፡፡ለዚህ እንደማሳያ የቅዳሜና ዕሁድ የገበያ ቦታዎችን መፈናቀል መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዛሬ ላይ ለጀሞና አካባቢው ለዓመታት ሲያገለግል የቆየው የድንኳን ገበያ ወደሌላ ቦታ ለመሰደድ ተገዷል፡፡

ዛሬ የተለመደው ሰፊ መገበያያ ቦታ በስፍራው አይታይም፡፡ ክረምቱ ከመግባቱ አስቀድሞ መለስ ቀለስ ባለው ድንገቴ ዝናብ ሳቢያ ታሪኩ ተቀይሯል፡፡ አካባቢው በስፋት በጎርፍ መጥለቅለቁ የገበያውን ህልውና አላስቀጠለም፡፡ ገበያተኞችና ነጋዴው ስፍራውን ለቀው ወደሌላው ደረቅ ስፍራ ተሻግረዋል፡፡

በጣም የሚገርመው ጉዳይ ግን ዛሬም ገበያው በቆመበት ስፍራ የሚታየው የቆሻሻ አወጋገድ ነው፡፡ አሁንም ከገበያው የሚወገዱ አትክልቶች ፣ የሞቱ ዶሮዎች፣ ደረቅ ቁሶችና የማይበሰብሱ ዕቃዎች ወደ ቱቦዎች ይወረወራሉ፡፡ይህ ድርጊት ሲካሄድ የአካባቢው ደንብ አስከባሪዎችም ሆኑ ከሚመለከታቸው አካላት አንዳች እርምጃ አይወስዱም፡፡ ሁሉንም በይሁንታ እያስተዋሉ ዝምታን አማራጭ አድርገዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናችን አዲስአበባ መካሄድ በጀመረው የኮሪደር ልማት መልከ ብዙ ለወጦችን ማስተዋል ጀምረናል፡፡ይህ አዲስ እንቅስቃሴ ፈጣን የሥራ ባህልን ጨምሮ የከተማ ጽዳት ወሳኝነትን አስተምሮናል፡፡ ዛሬ ቀድሞ ቆሻሻ ይጣልባቸው የነበሩ ቦታዎች ወደ ድንቅ መናፈሻነት ተቀይረዋል፡፡

ከተማዋ እንደ ስያሜዋ አበባ ሆና እንድትኖር ጉልበቶች ኃይል ሆነው ለውጧን እያፋጠኑት ነው፡፡ የቆሻሻን ነውርነት በሚያሳይ መልኩ ጽዳት በወጉ ተተግብሮ ለዓይን ውበትና ለሀገር ዕድገት እየተሠራ ነው፡፡ይህ መልካም ጅማሬ ሀገራችን ይዛው የኖረችውን ክፉ ስያሜ የሚፍቅ ለሌሎች አቻ ከተሞች ጭምር ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡

ከዚሁ የከተማ ኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ በስፍራው የተቀመጡ የቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራዎች በግልጽ ይስተዋላሉ፡፡ የእነሱ በስፍራው መቀመጥ ዋና ምክንያት ደግሞ ቆሻሻን በወጉ ለማስወገድና አብሮን የቆየውን ክፉ ባህል ለመቀየር ነው፡፡

ዛሬ ላይ የምናስተውለው ድርጊት ግን በተቃራኒው እየሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ማስወገጃዎቹን በግልጽ እያስተዋሉት እንኳን በአግባቡ መጠቀምን አይሹም፡፡እንደቀድሞው ልማዳቸው የእጃቸውን ሶፍትና ወረቀት የያዙትን የውሃ ፕላስቲክ ባሻቸው ቦታ ይወረውራሉ፡፡ እዚህ ላይ ችግሩ የአንድ ወገን ብቻ አይመስልም፡፡ይህን ክፍተት መጋራት ያለበት ቢኖር የሚመለከተው አካል ጭምር ይሆናል፡፡

መቼም ቢሆን ለሀገርና ማህበረሰብ ዕድገት የሚኖረውን ጉዳይ ተግብሮ ማሳየት የሚደነቅ ነው፡፡ይህን ለውጥ ገሀድ ማድረጉ አንድ ነገር ሆኖ የተሰራበትን ዓላማና ሂደት ጭምር በሚገባ ማስገንዘብና ማሳወቅም ተገቢ ይሆናል፡፡

ይህ ሙከራ በአግባቡ የማይተገበር ከሆነ ደግሞ ለጥፋቱ ተመጣጣኝ ማስጠንቀቂያና ርምጃ በመወሰድ ጽዳትን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብን መፍጠር የግድ ይላል፡፡ችግሮችን እንደዋዛ ማለፍ ግን ውሎ አድሮ ዋጋ የሚያስከፍለው ለሁሉም ነው፡፡ ይህ ችግር እንዳይደጋገም ደግሞ ኃላፊነቱ የሁላችንም ሊሆን ይገባል፡፡ ጉዳዩ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› እንዳይሆን ፡፡

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You