መስማት ለተሳናቸው ዜጎች ተስፋ የሰጠ ጅማሮ

በዓለማችን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሰዎች መስማት የተሳናቸው መኖራቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሀገራችን ደግሞ ከአራት ሚሊዮን በላይ መስማት የተሳናቸው ዜጎች እንዳሉ የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው ጥናታዊ መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማህበር ከተመሰረተ 50 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ሥራዎች ለመከወን ቢሞከርም በተለይ ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ ልዩ ፍላጎት ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች እገዛ የሚያደርግ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ከትምህርት ቤቶች ውጪ እምብዛም አልነበረም፡፡ በትምህርቱ ዘርፍም ቢሆን መስማት ለተሳናቸው ወጣቶች የሚያስተናግዱበት አገልግሎቶች ላይ ብዙ ክፍተት እንዳለ ይነሳል፡፡

መስማት የተሳናቸው ዜጎች በተለያዩ የፌዴራልና የክልል ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ፈልገው ሲቸገሩ ይስተዋላል። በዚህ ረገድ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ይበል የሚያሰኝ ጅማሮ አከናውኗል።

ተቋሙ መሠረታዊ የምልክት ቋንቋ ትምህርትን ለሠራተኞቹ በመስጠት ለሌሎች ተቋማት አርዓያ የሚሆን ተግባርን ማከናወን ችሏል። የተቋሙ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሀገሬ መኮንን፤ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መስማት የተሳናቸውን ዜጎች በተገቢው መንገድ ለማገልገል በተገቢው የምልክት ቋንቋ የሚያስረዳ ሠራተኛ እንደሚያስፈልጋቸው ያስረዳሉ፡፡

ልዩ ፍላጎት የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በተለይ በሕክምናው ዘርፍ ሴቶች በእርግዝና ወቅት ስሜታቸውን የሚጋራ ሐኪም እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ በሁሉም ተቋማት የሚያግዛቸው ሰው እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ። እንዲሁም ጉዳይ ለማስፈፀምና በቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ላይ የሚመጥናቸው ግብረ መልስ የሚሰጥን አገልጋይ የማግኘት መብት ሊከበርላቸው እንደሚገባ ነው የሚገልጹት፡፡

ተቋማቸው የምልክት ቋንቋን አስፈላጊነት በመረዳቱ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን አብሮ በመሥራት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን የብሔራዊ ቴያትር ሠራተኞች በትምህርቱ ያካተተ መሆኑን ነው ያነሱት። ወደ ፊት የተመረጡ ቴያትሮች በምልክት ቋንቋ እንዲተረጎሙ የሚረዱ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት መታቀዱን ያመላክታሉ።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ስምኦን (ዶ/ር) በበኩላቸው ፤ ማህበራቸው ስልጠናውን በመስጠትና መስማት ለተሳናቸው መፍትሔ በማመቻቸት እንደሚሠራ ነው የተናገሩት።

መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ለማካተት መጀመሪያ ከፍተኛ የአመለካከት ለውጥ ሊያመጣ እንደሚገባና በየተቋማቱ አድልዎ የሌለበት ተደራሽነት እንዲኖር መሥራት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

አካል ጉዳተኞች ከሌላው ኅብረተሰብ ሳይለዩ ተካተው ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል ሕግ እና ፖሊሲ በማስረፅ፤ውጤታማ ተሳትፎ እንዲያደርጉና የወጡትም ሕጎች ተግባራዊነታቸው እንዲረጋገጥ መንግሥት፣ ተቋማት እና ማህበረሰቡ ከፍተኛ ጥረት ሊያደርግ ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የቤተ ማዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎቱ ሠራተኞች ያገኙት ትምህርት በተቋሙ አካታች የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እና ባለሙያዎች መስማት ከተሳናቸው ተጠቃሚዎች ጋር በቀላሉ መረጃ እንዲለዋወጡ ያስችላል ይላሉ፡፡

ይህ ለሌሎች ተቋማት አርዓያ የሚሆን አካታችነትን የሚያሰፍን ተግባር በተቋሙም ሆነ በግለሰብ ደረጃ እንዲሳካ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን በማቅረብ፤የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አካታች እና አሳታፊ አሠራሮች፣ የሕግ ማዕቀፎች፣ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች ፣ የልማት ፕሮግራሞች እንዲቀረፁ እና እንዲተገበሩ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ይናገራሉ፡፡

አካል ጉዳተኞች የማህበረሰቡ አካል እንደመሆናቸው በቤተ መዛግብቱ የተጀመረውን መልካም ጅማሮ በመከተል በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች የፍትህ ተቋማት፣ በሕክምናው እንዲሁም እንደ ማህበረሰብ እያንዳንዱ ሰው መሠረታዊ የመግባቢያ ምልክቶች በተገኘው አጋጣሚ መማር እንዳለበት ይጠቁማሉ። ልዩ ፍላጎት ከሚያስፈልጋቸው ዜጎች ሀገር ልታገኘው የሚገባ ገቢ ለማሳደግ እና ለተግባቦት አብሮ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ነው ያስረዱት።

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2016 ዓ.ም

Recommended For You