ፒያሳ ከአፄ ምኒልክ አደባባይ ቁልቁል እየተንደረደርኩ አንገቴን ወደ መርካቶ አሻግሬ ጣል ሳደርግ የአንዋር መስጂድ ‹‹ሚናራ›› ከአካባቢው ሁሉ ጎላ ብሎ ይታያል። ወዲያ አንገቴን ጠረር ሳደርግ ደግሞ የመርካቶ ሌላኛው ውበት የራጉኤል ቤተክርስቲያን ጉልላት ከሚናሩ ጋር በአንድ ህንፃ ላይ ተገጣጥመው የተሰሩ እንጂ በተለያዩ ቤተ እምነቶች ከጣራው አናት የተሰቀሉ አይመስሉም።
ይህኔ የቴዎድሮስ ካሳሁን ግርማሞ ‹‹ተዋዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ›› የሚለው ሙዚቃን በዓይነ ህሊናዬ መጣ። እንዲህም እያሰብኩ ከሥፍራው ደረስኩ። መርካቶ ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ በሆነ አኳኋን ውስጥ ናት፤ አቤት ወከባ! አቤት ሩጫ! ሁሉም በየፊናው ውር ውር ይላል። በዚህ ወቅት የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ‹‹አይ መርካቶ!›› የሚለው የስንኝ ቋጠሮ ትዝ አለኝ።
መርካቶ ዕረፍት አልባ ናት። እኔም ግራ ቀኝ እየቃኘሁ ከአንዋር መስጂድ መግቢያው በር ላይ ደረስኩ። አይ መርካቶ! ተብሎ ስንኝ በተቋጠረላት፤ ብዙ አርቲስቶች በዘፈኑላት መርካቶ የአንዲት ጠንካራ እንስት አኗኗርና የሕይወት ተሞክሮ ለመዳሰስ። አዳነች ታዬ ትባላለች። ሰዎች ሥራ እንዴት ነው ብለው ይጠይቋታል።
ወላሂ! አሪፍ ነው ስትል ትመልሳለች። እኔም መርካቶ እንዴት ይዛሻለች አልኳት። ዋናው ነገር የሰው ፍቅር ይስጥህ፤ ፈጣሪ ጤና ከሰጠን ተንቀሳቅሰን እንገባለን አልሃምዱሊላህ! በቀረው ደግሞ ‹‹ዱዓ›› ማድረግ ነው ስትል ደስተኛ ስለመሆኗ ነገረችኝ።
የሐረር ቆንጆ
አዳነች የጀጎል ግንብ የታሪክ ምስክር በሆነላት፤ ጅብ ከሰው ተስማምቶ ከሚኖርባት ከተማ ነው እትብቷ የተቀበረው። አርቲስቶች የሐረር ብርቱካን ብለው ካዜሙላት የቆንጆዎች መፍለቂያ ከሆነችው ሐረር ብዙ ትዝታ እና ትውስታዎች አሏት። ከውልደት እስከ ዕድገት በሐረር ከተማ ከሱማሌዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ሐደሬዎች፣ አማራዎች፣ አርጎባዎች እና ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ተጨዋውታ፤ ተሳስቃ ነው በፍቅር ያደገችው። አዳነች ከውቧ ሐረር ውብ ትዝታዎች፤ አይረሴ ጊዜያቶችን አሳልፋለች።
የሐረሬዎች ሳቅ፤ ፈገግታ እና ጨዋታን በሙሉ እፍስ አድርጋ አዲስ አበባ ይዛ የመጣች ይመስላል። ከሁሉም ጋር መሳቅ፤ መጫዋት እና መቀለድ ትወዳለች። ፈገግ ብላ የጠቆረ ፊት ታፈካለች። ጨዋታ ጀምራ ዝምተኞችን የቀልደኞች ቀንድ ታደርጋለች፤ ምክንያቱም ልጅት ከሐረር ናትና!
አዳነች ከሐረር የወጣችው የኑሮ ውጣ ውረድ ፈትኗት፤ እንደ ገብስ ቆሎ ፈትጓት፤ እንደ አጓት ከአይቡ በላይ ቅርር አድርጎ ሲያንሳፍፋት ነው። በልጅነቷ ትምህርት እንድትማር ቢገፋፏትም ፈቃደኛ ሳትሆን ቀርታ ለውዝ ንግድ ጀምራ ከፊደል ጋር አልተዋወቀችም።የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ሐረር አዳነችን በጥሩ ሁኔታ ማስተናገድ አልቻለችም። አዳነችም ወሰነች፡፤ ከሐረር ወደ አዲስ አበባ አመራች-ሥራ ፍለጋ። ሐረር ውስጥ ሥራ ማጣቷ ብቻ አልነበረም ሆድ ያስባሳት።
የትዳር አጋሯንና የሁለት ልጆቿን አባት ከስምንት ዓመት በፊት ሞት ነጠቃት። በቀድሞ ኑሮዋ ባሏ ነጋዴ ስለነበር የተሻለ አኗኗር ነበራት። ከባሏ ሞት በኋላ ግን ነገሮች መስመራቸውን ሳቱ። በዚህን ጊዜ ብቸኝነት ተሰማት፤ ሆድ ባሳት። ጓዟን ሸክፋ አዲስ አበባ ከተመች። አዲስ አበባ እህትም ስለነበራት ሁለት ልጆቿን ከእርሷ ዘንድ አስቀምጣ ሥራ ልትሰራ ነበር ሃሳቧ። ግን አላደረገችውም።
ግራ ሲገባት ሰው ቤት ተመላላሽ ሰራተኛ ሆና በ500 ብር ተቀጠረች። ግን ብሩ ኑሮዋን መደጎም አልቻለም፤ ልጆች አስከትላ ስለምትሄድም አሰሪዎች ደስተኛ አልሆኑም።ከዚያም አንዋር መስጂድ አካባቢ ስትመጣ በርካታ ሰዎች በሶላት ሰዓት ውሃ እንደሚጠቀሙና የውሃ እጥረት በአካባቢው እንዳለ ተገነዘበች።
የራሷን ሥራ ለመፍጠር ወሰነች። በ25 ሊትር ውሃ ከሌላ አካባቢ ቀድታ ከዚያም በአንድ ሊትር ውሃ በሚይዙ ፕላስቲኮች በተለምዶ ‹‹ሃይላንድ›› በሚባለው ፕላስቲክ ቀናንሳ በአንድ ብር ትሸጥ ጀመር። ከ25 እስከ 30 ሊትር የሚይዘውን አንድ ጀሪካን ውሃ በሠባት ብር ትገዛ እና በ25 ብር ትሸጠዋለች።
በቀን እስከ 100 ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘት ጀመረች። በእርግጥ ቀደም ሲል እናቷ በዚሁ አካባቢ ተመሳሳይ ሥራ ይሠሩ ነበር። ግን አቅማቸው ስለደከመ ልጆቼ ይጦሩኛል ብለው የፍቅር ከተማ ወደሆነችው ሐረር ተመልሰዋል። አዳነች ደግሞ ሐረርን ትታ በእናቷ ስፍራ ተተክታለች።
ዳግም ወደ ትዳር
አዳነች ባለትዳርና የልጆች እናት ብትሆንም ሕይወት እንደፈለገችው ባለመሆኑ ከትውልድ መንደሯ ገፍቷታል። ግን ፈጣሪን አመስግና የሆነው ሁሉ ለበጎ ነው ብላ አዲስ ሕይወት ጀመረች። አዲስ ትዳር ጀመረች። ልጆችም ወለደች። አሁን ካለው ባሏ ጋር በመተሳሰብና በመተጋገዝ ይኖራሉ።
በተቻላቸው አቅም ሁሉን ነገር ይሸፍናሉ። ባሏ የተገኘውን ሥራ ሁሉ የሚሰራ፣ ጎበዝና ከሰው ተግባቢ ነው ትላለች። በአሁኑ ወቅት መኪና በማጠብ የራሱ ገቢ ለማግኘት ይጥራል። እርሷም ውሃ እየሸጠች በጋራ ቤታቸውን ይደጉማሉ፤ ልጆቻቸውን ያሳድጋሉ። አዳነች ለባሏ፤ ቧላም ለአዳነች እጅና ጓንት ሆነው ትዳራቸውን ይመራሉ።
ከሁለተኛ የትዳር አጋሯ አንድ ልጅ ወልዳለች። ሁለተኛ ደግሞ ነፍሰጡር ናት፤ አራት ወር ሞልቷል። ልጆችም የፈጣሪ ስጦታ ስለመሆናቸው ነው የምትናገረው። አሁን እኔም ሆንኩ ባለቤቴ እየኖርን ያለነው ለልጆቻችን ነው። በቀጣይ ልጆቻችን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርሱና እኛ የምንኖረውን ኑሮ እንዳይደግሙት እየለፋን ነው ባይ ናት። ለዚህም ተመካክረን፤ ተሳስበን የሚሆነውን እናደርጋለን ትላለች።
ገጠመኝ
በአንድ ወቅት በጠዋት ተነስታ ውሃዋን ቀዳድታ መደበኛ ሥራዋን ጀምራለች። የቀን ሶላት ‹‹ዙር›› ሰዓት ደረሰ። በተለመደው መንገድ አንድ ደንበኛ መጣ። አንድ ሊትር ውሃ ተጥቅሞ አምስት ብር ሰጥቶ አራት ብር መልስ ይጠብቃል። አዳነችም በሥራ ላይ ጥድፍድፍ እያለች ነበርና መልስ ሰጥታ ወደ ሥራዋ ተመለሰች። ሰውዬም ለጸሎት ሠዓት ቸኩሎ ነበርና ተጣድፎ ብሩን ወደ ኪሱ አስገብቶ ይሄዳል።
ግን አንድ ነገር ሆነ። አዳነች መልስ ብላ ከሰጠችው ውስጥ 100 ብር ድፍን ነበር። ሰውየውም ይህን አላስተዋለም። ግን አዳነች ማታ ላይ ውሎዋን ትገመግማለች፤ ሂሳቧን ትሠራለች። በዚህ ጊዜ 100 ብር ጎድሎ አገኘችው። ትንሽ ብስጨት ብላ ለበጎ ነው ብላ ነገሩን ረሳቸው።
ልክ አዳነች የቀን ገቢዋን እንደምታሠላው ሁሉ ደንበኛዋም ማታ ሂሳቡን ያሰላ ነበር። እርሱ ደግሞ በተራው የማያውቀው 100 ብር ከሂሳብ ውጪ ትርፍ ሆኖ አገኘው። በመጨረሻም ማሰላሰል ጀመረ። ከቀናት በኋላ አንዋር መስጂድ አካባቢ ሂዶ አዳነችን ይጠይቃታል። እርሷም ምልክቱን አክላ ነገረቸው። ከዚም 100 ብሩን መልሶላት ሄደ። እርሷም የሰው ሃቅ የማይበላ ቅን ሰው ስትል አመሰገነችው።
በመጨረሻም ተመሰጋግነው ተለያዩ። በብር ደረጃ የተጋነነ ባይሆንም መሰል ገጠመኞቿ በርካታ ስለመሆናቸው ታስታውሳለች። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የአንድ ብር ውሃ ተጠቅመው 100 ብር ሰጥተው፤ 99 ብር መልስ ልትሰጣቸው ስትል ያዥው በርቺ ብለው አስደምመዋት ይሄዳሉ። ጥቂቶች ደግሞ ውሃው የፈጣራ ስጦታ ስለሆነ አንከፍልም ብለው ገላምጠው ይሄዳሉ። ግን ለከፋ ጸብና ድብድብ የተጋበዘ አለመኖሩንና እርሷም ነገሮችን ቸል ብላ እንደምታሳልፍ ትናገራለች።
ከምንም በላይ ግን አንዳንድ ደንብ አስከባሪዎች የሚያደርጉትን ስትመለከት ታዝናለች። ድንገት መጥተው ከስንት ቦታ በጀርባዬ አዝዬ ያመጣሁትን ውሃ ይደፋሉ፣ ጀሪካኖቼን ይወስዳሉ፣ ሰዎች ሲታጠቡ ለመቀመጫ የገዛሁትን አግዳሚ ጣውላ ይወስዳሉ። ግን ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ረገብ ብለዋል ስትል ያሳለፈችው መጥፎ ጊዜ ታስታውሳለች።
ሰዎች ስለአዳነች
አዳነች ዋና ሥራዋ ፈገግታዋ ይመስል ሰዎችን ሁሉ በሳቅና በደስታ ነው የምታስተናግደው። በዚህም ፀባይዋ የሚደሰቱ በርካቶች ናቸው። በዚያው አካባቢ የሚሰሩ ሰዎችም ይህንን ይመሠክራሉ። ብዙ ሰዎች አዳነች በምትከውነው ውሃ የመሸጥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ቢሆንም፤ እጅግ በርካቶች ውሃ የሚገዙት እርሷን ፈልገው ነው። ይህም የሆነው ከመልካምነቷና ሀቀኛ ከመሆኗ የተነሳ ነው።
በተጨማሪም ፈገግታዋና ሰዎችን የምታስተናግድበት መንገድ ለየት ያለ መሆኑ በሰዎች ዘንድ አክብሮትና እውቅናን አትርፎላታል። ታሪኳን የሚያውቁ ሰዎችም ጥንካሬዋን በሚገባ ስለሚረዱ ለማበረታትም ጭምር ወደ እርሷ ይሄዳሉ። አንዋር መስጂድ አካባቢ አዳነችን የማያውቅ ሰው የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። ስሟ ቢጠፋቸው እንኳን ፈገግታዋ ምልክት ነው። ፈገግተኛዋ የሐረር ልጅ እያሉ ምልክት እስከመሆንም ደርሳለች። በዚህ ባህሪዋም በርካቶች ይወዷታል፤ ለሌሎችም አርዓያ የምትሆን ልጅ ሲሉ ያሞካሿታል።
አዳነች አኗኗርና ምክር
አዳነች በቀን ከምታገኘው ገቢ ላይ ከባሏ ጋር እየተመካከረች 10፣ 20 ብር እያሉ ይቆጥባሉ። አንድ ልጇን በየወሩ 350 ብር እየከፈለች ታስተምራለች፤ በዚህ ዓመት ከመዋዕለ ህጻናት አጠናቆ አንደኛ ክፍል ይገባል።
ሁለተኛ ልጇ ሁለተኛ ዓመት መዋዕለ ህጻናት ተማሪ ናት። ሦስተኛ ልጇ ህጻን ስለሆነች አጠገቧ ትውላለች። በአሁኑ ወቅት ኮልፌ አካባቢ በ700 ብር ቤት ተከራይተው ይኖራሉ። ባሏም ከአዳነች ጋር እየተመካከረ የነገ ሕይወታቸውን ለማሻሻል ደፋ ቀና ይላል። ባሏ ሰው አክባሪና ታዛዥ በመሆኑም አዳነችን ደስተኛ አድርጓታል። ምንም እንኳን እርሷና ባለቤቷ ጠንካራ ቢሆኑም በዚህ ሁኔታ ኑሮ እንዴት ሊገፋ ስትል ትጨነቃለች።
አዳነች ከባለቤቷ ጋር አምስት ቤተሰብ የሚተዳደረው በዚህ ሥራና በባሏ ጥረት ነው። ግን ይህ ከብዷቸዋል። ቢቻል እንደ ወጣቶች ተደራጅታ ሥራ ብትሠራና መንግስት ዕድሉን ቢያመቻችላት ደስተኛ ናት። ትንሽ ሱቅ ባገኝም እራሴንም ለውጬ ሌሎችን መለውጥ እና አርዓያ መሆን እችላለሁ። ሃሳቤም አንድ ቀን ይሳካ ይሆናል የሚል ተስፋ አላት። የሚመለከታቸው አካላት ችግሯን ቢረዷት ትመኛለች።
የቀበሌ ቤት ቢሰጣትም ፍላጓቷ ነው። ምክንያቱም ደግሞ እነዚህን ልጆቿን ለማስተዳደር በቀን በምታገኘው ገቢ ብቻ መደጎም ከብዷታልና። ሌሎች ሥራ ፈጣሪዎችና አማካሪዎች ደግሞ የተሻለ ቢዝነስ ወደምታገኝበት መስመር ቢወስዷት ወይንም ቢጠቁሟትም ፍላጎቷ ነው።
የሆነው ሆኖ ትላለች አዳነች፤ ከራሷ ተሞክሮ ተነስታ አንድ ምክር ለማስተላለፍ ትፈልጋለች። በርካታ ወጣት ሴቶች በአሁኑ ወቅት አልባሌ ቦታ ከመዋላቸውም በላይ ለአያሌ ችግሮች እየተጋለጡ መሆኑን ስትሰማ እና ስትመለከት በጣም ታዝናለች። እንዴት አንድ ሰው እራሱን ማሸነፍ ይሳነዋል የሚል ጥያቄ ይፈጥርባታል።
እኔን ተመልከቱኝ አገር አቆራርጬ፤ ተስፋ ሳልቆርጥ እራሴንም ልጆቼንም እያስተዳደርኩ ነው። ታዲያ! እናንተ ስለምን ስለራሳችሁ መሆን ያቅታችኋል፣ ስለምን የሰው ጥገኛ ትሆናላችሁ፣ ስለምንስ አልባሌ ቦታ ትውላላችሁ? ከነብሳችሁም ከሥጋችሁም ሳትሆኑ ስለምን በከንቱ ትቀራላችሁ ትላለች። የዝግጅት ክፍላችንም እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ሴቶች ለሚሊዮን እንስቶች ተምሳሌት ናቸውና ድጋፍ እና እገዛ ቢደረግላቸው ሲል መልዕክቱን ያስተላልፋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 15/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር