በእርቀ-ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ሰነድ እንደተገለጸው፤ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በህዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም እውነትና ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገ እርቅ ማውረድ አስፈላጊ ነው፡፡
እንደ ሰነዱ ማብራሪያ፣ በተለያዩ ጊዜዎች እና የታሪክ አጋጣሚዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሌላ በደል ተጠቂዎች የሆኑ ወይም ተጠቂዎች ነን ብለው የሚያምኑ ዜጎች በደላቸውን የሚናገሩበትና በደል ያደረሱ ዜጎች ላደረሱት በደል በግልፅ በማውጣት የሚፀፀቱበትና ይቅርታ የሚጠይቁበት መንገድ በማበጀትና እርቀ-ሰላም በማውረድ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል፡፡
የኮሚሽኑ ዓላማም በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ሰላም፣ ፍትህ፣ ብሄራዊ አንድነትና መግባባት፣ እንዲሁም እርቅ እንዲሰፍን መስራት ነው፡፡
የህግ ባለሙያዎችም በፍርድ ቤት ከሚሰጥ ፍትህ ይልቅ በእርቅ የሚያልቅ ጉዳይ በጠላትነት ላለመተያየት ትልቅ አማራጭ እና የሚያስገኘው እርካታም ከፍተኛ ነው ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ ሚሊዮን አሰፋ፣ እርቅና ፍትህ የሚያገናኛቸው የየራሳቸው ባህሪ እንዳላቸው ያመለክታሉ፡፡ በፍርድ ቤት በሚገኝ ፍትህ እና በእርቅ በሚገኝ ስምምነት መካከል ካሳ ሊኖር እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡
በህዝብ ላይ ምንም አይነት የሞራል ጉዳት የማያስከትል ከሆነ ሰዎች ጉዳያቸውን በእርቅና በግልግል እንዲጨርሱ ማድረግ በፍትሃብሄር ህጉም መመልከቱን ጠቅሰው፣እርቀ-ሰላም እንደሚበረታታም ይገልጻሉ፡፡
‹‹በህግ የተያዘ ጉዳይ ውሳኔ የሚያገኘው በፍርድ ቤት ዳኛው አማካይነት ነው፡፡ ግልግልንና እርቅን ግን ሰዎች በመረጡት ሰው አማካይነት ያደርጋሉ››የሚሉት አቶ ሚሊዮን፣ ለተመረጠው ሰው ተገዢ እንደሚሆኑም ይናገራሉ፡፡አስታራቂዎቹ ሽማግሌዎች የሚያሳልፉት ውሳኔ እንደ ፍርድ ውሳኔ እንደሚቆጠርም ይገልጻሉ፡፡
አንድ ተበዳይ፣ በዳይ ላይ ሲያስፈርድ የተፈረደበት አካል የጠላትነት ስሜት ሊያድርበት እንደሚችል በመጥቀስ፤በእርቀ-ሰላም ግን ‹አንተም ተው አንተም ተው› በሚል እሳቤ ሽማግሌዎች ሁለቱም ወገን እንዳይጎዳ አስማምተው እንደሚያስታረቁና የተሻለ ውሳኔ መሆኑን ያብራራሉ፡፡‹‹በዕርቅ የሚያልቁ ጉዳዮች የሰዎችን ግንኙነት አያሻክሩም፡፡ በፍርድ ቤት ግን አሸናፊና ተሸናፊ ስላለ ቂም መያያዝን ሊያስከትል ይችላል›› በማለት ያብራራሉ፡፡
አቶ ሚሊዮን፣ ‹‹ሊሂቃን በፈጠሩት ችግር ምክንያት ምንም የማያውቀው የኅብረተሰብ ክፍል እርስ በእርሱ መጠራጠር ላይ ነው፤ ቅሬታም አለው፡፡ እንዲህ አይነቱም ቅሬታ ሊሽር የሚችለው በእርቀ-ሰላም ነው›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡
የወንጀል ቅጣት ‹‹እኔን ያየ ይቀጣ›› የሚል ዓላማ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌላው ከዚህ ግንዛቤ ወስዶ ጥፋት ውስጥ እንዳይገባ የሚያደርግ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
የአፈናቃዮችንና ተፈናቃዮችን ጉዳይ በአብነት በመጥቀስ የአገር ሽማግሌዎች ‹‹ይቅር ለፈጣሪ›› እንዲባባሉ አድርገው ቢያስታርቋቸው እርቁ በጣም የሻከረውንና ቁርሾ የተያዘበትን ጉዳይ የመለወጥ ኃይል እንደሚኖረውም ይጠቁማሉ፡፡
አፈናቃዩን ‹‹ማፈናቀል አትችልም›› በሚል የፍርድ ቤት ውሳኔ ለተፈናቀለው ማኅበረሰብ ተፈርዶ ወደተፈ ናቀሉበት ቦታ እንዲመለሱ ቢደረግ የጠላትነት ስሜት እንደሚኖር ያመለክታሉ፡፡‹‹ሰላምን ይበልጥ ለማረጋገጥ እርቀ-ሰላም መፍጠርን የመሰለ ነገር የለም›› የሚሉት የህግ ባለሙያው፣እርቅ ለሁሉም እረፍት እንደሚሰጥም ያስገነዝባሉ፡፡
የህግና የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ አቶ ሙልዬ ወለላው እንደሚናገሩት፤ የጎረበጠ፣ የተጎዳ፣ የተነጠቀ ነገር በመኖሩ በዳይና ተበዳይ አለ ማለት ነው፡፡ ረቂቅ ማቋቋሚያ አዋጁ የወጣውም ‹‹አንተም ተው አንተም ተው›› ለማለትና የተበደለን ለመካስ፣የተነጠቀን ለመመለስ ነው ሲሉ ያብራራሉ፡፡
በዚህ አካሄድ ፍትህ የሚገኘው በሽማግሌዎች መሆኑን ጠቅሰው፤ እርቀ-ሰላም መካሄድ ያለበት ግን አድልዎ በማያደርጉ ሰዎችና በህዝቡ ዘንድ ይሁንታ በሚያገኙ አካላት መሆን ይኖርበታል ይላሉ፡፡
‹‹ይህ ወገን በድሏል፤ አሊያም አንተ በድለሃል የሚለውን ካልተቀበለ ግን ወደ ፍትህ መሄድ አይቀርም፡፡ወደ ፍትህ ከተሄደ ደግሞ አሸናፊና ተሸናፊው በፍትህ ይረጋገጣል፡፡በዚህ ውስጥ ተጠያቂነት ይመጣል›› የሚሉት አቶ ሙልዬ፣ ጉዳዩን በባህላዊ መንገድ ለመፍታትና እርግፍ አድርጎ ለመተው ወደ እርቀ-ሰላም መሄዱ የተሻለ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡ በደልን እርግፍ አድርጎ መተው አንድ የጋራ አገርና ህዝብ እንዲኖር እንዲሁም ያለውን ልዩነት አቻችሎ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚያስችልም ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ሙልዬ ገለጻ፤ፍትህና እርቀ-ሰላም የሚገናኙበት ሁኔታ አለ፡፡በሁለቱም ውስጥ ተበዳይ ሊካስ ይችላል፤ ከሁለቱ የሚገኝ እርካታ ይለያይ እንጂ ሁለቱም መግባባትን መፍጠር ይችላሉ፡፡
እርቀ-ሰላምና ፍትህ የሚያለያዩባቸው ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ፍትህ ሰፊ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡በሦስት ደረጃ ተከፍሎ የሚታይ ሲሆን፣ይኸውም ፍትህ በፍርድ፣ ፍትህ በአስተዳደር እና ፍትህ በሽምግልና እንዴት ይተዳደራል የሚለው ነው፡፡
ስለሽምግልና ፍትህ ሲያብራሩም ፍትህ የሚገኘው በባህላዊ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡በዚህም ለባህል ተብሎ የሚተው ነገር እንደሚኖር፣የጉዳቱ መካሻ የሚሆን ነገር ከማግኘት በተጨማሪ በሽምግልና ምክንያት ወደቀድሞ ሰላማዊ ህይወት የሚመጣበትም ሂደት እንደሚኖር ያብራራሉ፡፡ይህም የተነጠቀውና የተዘረፈው የሚመለስበት፣ የተጎዳው የሚካስበት እንዲሁም ብሶቱን፣ ጭንቀቱንና ስጋቱን ሊቀንስለት የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፣ይህ ማለት ደግሞ ሁሉቱም ወገን በማይሸናነፉበት ይልቁንም ሁለቱም አሸናፊ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ያመለክታሉ፡፡
በአገሪቱ ለዓመታት ብሄራዊ እርቅ እንዲደረግ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ለጥያቄው ‹‹ምን ሆነን? ማን ከማን ጋር ተጣልቶ ነው? የሚል ምላሽ በጥያቄ መልኩ ሲሰጥ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያስገነዝበው ደግሞ አለመግባባቶችን ለዘለቄታው ለመፍታት የእርቀ-ሰላም መንገድ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡በዚህም ሰላምን መፍጠር ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር ደቡብ አፍሪካ የነጭ የበላይነት፣ሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ያሳረፉትን ቀውስ ለመፍታት የመረጡት መንገድ እርቀ-ሰላም እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ለዚህም የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቷል፤አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ እንደሚጸድቅም ይጠበቃል፡፡
የህግ ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ፤ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች አገር እንደመሆኗ በመካከላቸው ምንም አይነት ቅሬታ የለም ማለት አያስችልም፡፡ የተበደለም፣ የበደለም አካል መኖሩ እሙን ነው፡፡መጎዳዳት እንዳይኖር እርቀ-ሰላም ወሳኝ ነው፤ መከናወን የሚኖርበት ግን በገለልተኛ ወገኖችና የሁሉንም ህዝብ ይሁንታ ባገኙ አካላት መሆን ይኖርበታል፡፡
ለታሪክ የሚቀመጥና ወደኋላ የማይመለስ ለአንዴና ለመጨረሻ የሚሆን ሥራ መሰራት እንዳለበት፣ እንደ አገር ለመቀጠልና እጅ ለእጅ ተያይዞ ልማትን ለማሳደግ ትንንሽም ይሁኑ ትልልቅ ቁርሾዎችን ማስወገዱ ጠቃሚ እንደሆነም ያመለክታሉ፡፡ለዚህም የረቂቅ አዋጁ መጽደቅ ወሳኝና የሚደገፍ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡ ኅብረተሰቡ መልሶ አብሮ ለመኖር የሚመረጠው በህግ ከሚገኝ ፍትህ ይልቅ ዕርቀ-ሰላምን ነው ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
ኢትዮጵያ የእርቅና የፍትህ ውሳኔዎች በአንድ ላይ ተጣጥመው መሄድ የሚችሉበት ባህል ባለቤት መሆኗ ይታወቃል፡፡በይቅርታና በእርቀ-ሰላም በዳዩን ከመቅጣት ይልቅ ተበዳዩን በመካስ ሰላም ማምጣትን ያበረታታል።
ብሄራዊ መግባባትና እርቀ-ሰላም ማድረግ ከአገሪቱ ባህል ጋር አብሮ ይሄዳል፡፡‹‹ብሄራዊ እርቅ›› ለዓመታት ሲጠየቅ የኖረ እንደመሆኑ መንግሥት አሁን የደረሰበት ውሳኔ ትክክል የሚባል ነው፡፡ እርቀ-ሰላም አስፈላጊና ወቅታዊም ነው፡፡
አስቴር ኤልያስ