‹‹በቃል ያለ ይረሳል፣ በጽሑፍ ያለ ይወረሳል›› እንዲሉ አበው ከትናንት እስከ ዛሬ ያሉ ታሪኮች በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ተሰንደው እስካሁኑ ትውልድ ድረስ ለመሸጋገር በቅተዋል። በጋዜጣው በተስተናገዱት አንዳንድ ታሪኮች ‹‹እንዲህም ነበር ለካ?›› የሚሉ ጥያቄዎችን ያጭራሉ። አንዳንድ ታሪኮች ደግሞ ምንም እንኳን በወቅቱ ለነበረው ባለታሪክ እውነታ ይሁን እንጂ ዛሬ ላለው አንባቢ ግን የሚፈጥረው ፈገግ የሚያደርግ ስሜት አለው። በጋዜጣው ከአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት ብዙዎች ትዝብታቸውን፣ ጥያቄዎቻቸውን እንዲሁም ምስጋናቸውን አቅርበውበታል። እነሆ ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን ለማየት ለዛሬ እነዚህን ታሪኮች መርጠናል።
ቁማር
እንዲህ ነኝ እኔ ብዙ ቁማር
አደባድብና አጋድል ጀመር።
ብዙ ሰዎች ናቸው በኔ የከበሩት።
ቁጥራቸውም አይታወቅ ደግሞም የከሰሩት።
ይኸኛው የሞተው ይህም የሚጣላው።
በመሸነፉና በመናደዱ ነው።
ሰው ራሱ ፈጥሮኝ ብቃወመውም
በኃላፊነቱ አልጠየቅም።
ስለዚህም እኔ እንዳልኖር ባንድ አገር ።
ቁጥጥር ቢደረግ ምናለበት በአገር።
-አየለ ኪዳኔ
(አዲስ ዘመን መጋቢት 6 ቀን 1957 ዓ.ም)
ዕድገቴን ሊያስከለክለኝ ይችላልን?
የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ። ብዙ ቤተሰብ አለኝ። ችግር ደረሰብኝ። የተበደርኩትን ገንዘብ ለመክፈል ባለመቻሌ በፍትሐ ብሔር ተከስሼ ከደሞዜ እየተቆረጠ ለፍርድ ባለመብቱ እንዲከፈል የተወሰነበት ከግል
ማህደሬ ጋር ተያይዟል። መሥሪያ ቤታችን ውስጥ ካሉት ሠራተኞች ጋር ለእድገት ተወዳድሬ ለማሸነፍ ስችል ይህ በፍትሐ ብሔር ተከስሼ የተወሰነብኝ የብድር ዕዳ ከማህደሬ ውስጥ በመያያዙ ብቻ የእድገት ኮሚቴው ለሌላ ሰው ሰጥቷል።
ቸግሮኝ ተበድሬ ለመክፈል ባለመቻሌ ይህ በቂ ምክንያት ሆኖ እድገቴን ሊያስከለክለኝ ይችላልን? ሁኔታውን አብራራልኝ።
-ኢሳይያስ አበበ፤
ከአዘጋጁ፡- የተቸገረ ሰው መበደሩ ያለና ወደፊትም የሚኖር ነው። አንድ ሰው ተበድሮ ካልከፈለም ይከሰሳል። ተከሶም እንዲከፍል መወሰኑ ወንጀል አይደለም።
አንድ የመንግሥት ሠራተኛ እድገት ሊያገኝ አይገባውም የሚባለው መጥፎ ሥነ ምግባር ሲኖረው፣ ሥራውን ሳያከብር፣ በሥራውም ደካማ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ለእድገት የሚያበቁትን መመዘኛዎች ሳያሟላ ሲቀር ነው። የሥራ ዲሲፒሊን የማያከበር እንኳንስ እድገት ቀርቶ ከሥራም ሊሰናበት ይችላል። ይህም በሕግ የተደገፈ ነው። እንደሁኔታው እየታየ ከዚህ ውጪ ግን እርስዎ እንደጠየቁት ለችግርዎ ገንዘብ ተበድረው ለመክፈል ባለመቻልዎ ብቻ ከደሞዝዎ ተቆርጦ እንዲከፈል ለመሥሪያ ቤትዎ የተላለፈውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ እድገትዎ ቀርቶ ከሆነ አግባብ ስላልሆነ አቤቱታዎን ለመሥሪያ ቤቱ የበላይ ባለሥልጣን አመልክቱ።
በዚያ በኩል አቤቱታዎ ተቀባይነት ያለገኘም ከሆነ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን አመልክተው ሕጋዊ መብትዎን ሊያስከብሩ ሰፊ ዕድል አለዎት።
(አዲስ ዘመን መጋቢት 01 ቀን 1974 ዓ.ም)
መቱ
በኢሊባቡር ክፍለ ሀገር የኪ ወረዳ ውስጥ በድብቅ አንድ የነብር ቆዳ ሲሸጡ የተገኙ ግለሰቦች በአንዳንድ ዓመት እሥራት እንዲቀጡ የሞቻ አውራጃ ፍርድ ቤት ሰሞኑን ፈረደባቸው።
ብርሃኑ ኃይለ ማርያም እና ኢብራሂም አባገሮ በተባሉት በእነዚህ ኮንትሮባንዲስቶች ላይ ይኸው የእሥራት ቅጣት ሊወሰንባቸው የቻለው የነብሩን ቆዳ ለአንድ ግለሰብ ለመሸጥ በሚዘጋጁበት ጊዜ በቀበሌው የጥበቃ ጓዶች እጅ ከፍንጅ ከመያዛቸውም በላይ በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው መሆኑን ጓድ ግዛው አመንቴ የሞቻ አውራጃ ፍርድ ቤት ተጠሪ ዳኛ አስረድተዋል።
(አዲስ ዘመን መጋቢት 4 ቀን 1974 ዓ.ም)
እንዳያስገድዱን
በደሴ ከተማ ለሕዝብ ከፍተኛ አገልግሎት የሚሠጥ ‹‹የኢትዮጵያ ንግድና ችርቻሮ ኮርፖሬሽን ›› አለ። ይህም ድርጅት ለሕዝብ መሠረታዊ ዕቃዎችን ሲያከፋፍል ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለሕዝቡ መሠረታዊ ዕቃዎች ሲመጡ አንድን ተፈላጊ ዕቃ ከሌላ ዕቃ ጋር እያጣመርን እንድገዛ እንገደዳለን። ከዚህ የተነሳ ኅብረተሰቡን ለአትራፊ ነጋዴዎች ያጋልጣል። በመሆኑም የሚመለከተው ክፍል አስቸኳይ የሆነ መፍትሄ ይፈልግለት ዘንድ ጥቆማችንን እናስተላልፋለን።
ግርማ ያዕቆብ እና አሸናፊ ተስፋዬ
(ከደሴ)
የሻሸመኔው ሲኒማ ቤት
በሻሸመኔ ከተማ የሚገኘው ሲኒማ ቤት አንዳንዴ የሚያመጣው ፊልም ጥራት የጎደለው በመሆኑ፤ ለዓይን ብዥ እያለ ያጭበረብራል። ረዘም ያለ ፊልም ሲያመጣ የተለመደው ሦስት ሰዓት ሲደርስ ከፊልም ቤት ሠራተኞች አንዱ ‹‹ሞተሩ ስለተበላሸ ይቅርታ አድርጉልን›› በማለት ተመልካቹን ያሰናብታል። ተመልካቹም እየተበሳጨ ከፊልም ቤቱ ይወጣል። ስለዚህም የሲኒማ ቤቱ ኃላፊ ይህንን ያልተስተካከለ አሠራር እንዲታረም ጥረት እንዲያደርጉ እናሳስባለን።
(አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 1974 ዓ.ም)
የሸዋ ክብደት ማንሳት ውድድር ይደረጋል
የሸዋ ክብደት ማንሳትና የሰውነት ቅርጽ ውድድር የፊታችን ሚያዝያ 2 ቀን የሚደረግ መሆኑን የክብደት ማንሳትና የሰውነት ቅርጽ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ውድድሩ የሚደረገው በአምስት የከነማ ክለቦች መካከል ሲሆን፤ በዘንድሮው ወድድር በክብደት ማንሳት የሚወዳደሩት በሦስት ካታጎሪ ማለትም በታዳጊዎች፣ በመካከለኛ እና በከፍተኛ ተወዳዳሪዎች መካከል የሚደረግ መሆኑ ታውቋል። በተጨማሪም የሰውነት ቅርጽ ውድድር ይደረጋል። በተለይ በክብደት ማንሳት ውድድር ከዚህ በፊት የነበረው የኪሎ መበላለጥ ችግር የዘንድሮው ውድድር በሦስት ደረጃ ወይም ፈርጅ ስለተመደበ ችግር እንደማይኖር ለማወቅ ተችሏል። ለዚህ ውድድር ተወዳዳሪዎች በአሁኑ ጊዜ በመመዝገብ ላይ ሲሆኑ፤ ተወዳዳሪዎቻቸውን ያላስመዘገቡ ክለቦች እስከ ፊታችን ረቡዕ ድረስ እንዲያስመዘግቡ ፌዴሬሽኑ አሳስቧል። የሸዋ ሻምፒዮና ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላ ሰኔ አምስት ደግሞ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚደረግ መሆኑ በተጨማሪነት ተገልጿል።
ባለፈው በአዲስ አበባ ሻምፒዮና ውድድር በክብደት ማንሳት ውድድር ከፍተኛ 14 ታደሰ ጥላሁን ፤ በሰውነት ቅርጽ ደግሞ ብርሃኑ አክርሰው ከከፍተኛ 05 ሻምፒዮን መሆናቸው ይታወሳል።
(አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 1974)
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም