የተጠናከረው የኬንያና የአሜሪካ ግንኙነት

ኬንያ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ያለሆነች አጋር የሚል ማዕረግ አግኝታለች። ይህን ስያሜ የሰጠቻት ደግሞ ኃያሏ ሀገር ዩናይትድ ስቴትስ ናት።

የኬንያ ፖሊስ መኮንኖች ሰላም አስከባሪ ኃይል ሆነው ወደ ሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት-አው-ፕሪንስ ሊያቀኑ እየተጠባበቁ ይገኛል። ኬንያ በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ደህንነት ያላት ስም እየጎላ መምጣቱን እነዚህ ርምጃዎች ያሳያሉ።

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በዋሺንግተን ታሪካዊ የተባለ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ። ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሩቶ፣ ስለሄይቲ ጉዳይ እንዲሁም ስሌሎች የሁለቱ ሀገራት ግንኙነቶች ውይይት አካሂደዋል።

ኬንያ አባል ያልሆነች የኔቶ አጋር በመሆን አራተኛዋ የአፍሪካ ሀገር ስትሆን ከሰሀራ በታች አፍሪካ ደግሞ ብቸኛዋ ሆናለች። ይህ ማዕረግ ኬንያ በአፍሪካ የዩናይትድ ስቴትስ ሁነኛ ወዳጅ መሆኗን የሚያሳይ ሆኗል።

ዋሺንግተን በተባበሩት መንግሥታት ለሚታገዘው የሄይቲ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ የሚሆን 200 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብታለች። ኬንያ የቀጣናውን ሰላም በማስከበር ተነፃፃሪ ስኬት ያላት ሀገር ናት።

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በስምምነት የተረጋጋው በኬንያ መሪነት ነው። ከዚህ አልፎም ሩቶ በታላላቅ ሐይቆች (ግሬት ሌክስ) ቀጣና ያለውን መከፋፈል ለማርገብ እና በዲሞክራቲክ ኮንጎ የታየውን የአማፂያን መስፋፋት ለመግታት እየጣሩ ይገኛሉ።

በአውሮፓውያኑ ከ2001 ጀምሮ የኬንያ ጦር ሠራዊት በሶማሊያ አል-ሸባብ የተሰኘውን እስላማዊ ታጣቂ ቡድን እየመከተ ይገኛል። በኬንያዋ የላሙ ጠረፍ የሠፈረው የአሜሪካ ጦር ይህን ትግል እያገዘ ነው።

አሜሪካ የምትተማንበት አፍሪካዊ ሀገር ማግኘቷ እፎይታ ይሰጣታል። በተለይ ደግሞ በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የምዕራባውያን ሚና እየቀነሰ መምጣቱ እና የሩሲያና ቻይና ተጽእኖ መበርታቱ አሜሪካን እንቅልፍ የነሳት ይመስላል።

የምዕራባውያን የጦር ትብብር ማኅበር የሆነው ኔቶ አባል ያልሆነች አጋር የተባለችው ኬንያ፣ በጣም ዘመናዊ የሚባሉ የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም ፀጥታዋን ለማጠናከር ሥልጣና እና ብድር ልታገኝ ትችላለች።

ነገር ግን ይህ ማለት አሜሪካ ለኬንያ ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ የማድረግ ግዴታ አለባት ማለት አይደለም። ኬንያ በበኩሏ ለኔቶ ተልዕኮዎች ወታደር የመላክ ግዴታ አይኖርባትም።

ኬንያ በተደጋጋሚ ጥቃት ካደረሰባት አል-ሸባብ ቀጥተኛ አደጋ ቢደቀንባትም ከሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ጋር ሲነፃፀር ለወታደራዊው ኃይሏ የምትመድበው በጀት የጎላ የሚባል አይደለም።

ኬንያ እና ሶማሊያ በሚዋሰኑበት 680 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው ድንበር ላይ አነስተኛ የሚባሉ ጥቃቶች በደተጋጋሚ ይከሰታሉ።

አል-ሸባብ ኬንያ ውስጥ ገብቶ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶችን አድርሻለሁ በማለት ኃላፊነት ወስዶ ያውቃል። በአውሮፓውያኑ 2013 መዲናዋ ናይሮቢ በሚገኝ ዌስትጌት በተሰኘ የገበያ አዳራሽ የተፈፀመው እና 70 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ይታወሳል።

ካለንበት የአውሮፓውያኑ 2024 መባቻ ጀምሮ አል-ሸባብ በኬንያ 30 ጥቃቶች ፈፅሜያለሁ ማለቱን ቢቢሲ ሞኒተሪንግ ከቡድኑ መግለጫዎች ካሰባሰበው መረጃ ተገንዝቧል።

የቡድኑ አባላት ላሙ፣ ጋሪሳ፣ ዋጂር እና ማንዴራ በተባሉ የጠረፍ ከተሞች አካባቢ ይንቀሳቀሳል። በጥቃቶቹ አብዛኛውን ጊዜ ሰለባ የሚሆኑት የኬንያ ወታደሮች ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪዎች በዓመቱ መጨረሻ ሶማሊያን ለቀው ለመውጣት ማቀዳቸውን ተከትሎ በኬንያ ድንበር አካባቢ ያላትን እንቅስቃሴ እያጠናከረች ነው።

አሁን የተሰጣት ማዕረግ ለመረጃ ስብሰባ እና ስትራቴጂካዊ ስምሪት ለማድረግ ሊጠቅማት እንደሚችል ይታመናል።

ኬንያ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ተልዕኮ ውስጥ መሳተፏ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አካባቢያዊ ሠራዊት ወታደራዊ ጥንካሬ የሚፈተንበት ነው።

በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ተሰማርቶ የነበሩት ወታደሮች በዘጠኝ ወራት ለቀው መውጣታቸው እና አማጺያን እየተጠናከሩ መሄዳቸው የተልዕኮው ክሽፈት ማሳያ ነው ተብሎ ነበር።

ቢሆንም አሜሪካ ኬንያን ተጠቅማ በቀጣናው ያላትን ተደማጭነት ለማስፋፋት እና ግጭቶችን ለማብረድ የምታደርገውን ጥረት ቀጥላለች።

ምንም እንኳ አሜሪካ በቀጥታ ባትሳተፍም ፕሬዚዳንት ሩቶ 16 አሜሪካ ሠራሽ ሄሊኮፕተሮች እና 150 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ሊሰጣቸው እንደሚችል ተጠቁሟል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You